ሁለት ዓይነት ስሜት ነበር የተፈጠረብኝ፡፡ በሰሞንኛው የበዓል ድባብ በመዲናዋ ዋና ዋና መንገዶችና የገበያ ማዕከላት ላይ የማየው ሁሉ የውጭ አገር መገለጫ የሆነ ነበር፡፡ ይህንን ሳይ ‹‹እኛ እኮ የምዕራባውያን የሸቀጥ ማራገፊያ ነን›› የሚሉ ወገኖች ሀሳብ ትዝ አለኝ፡፡ በየመንገዱ የማየው ሁሉ ይሄን እውነት የሚያረጋግጥ ሆነብኝ፡፡
በዚህ ትዝብት ውስጥ ሆኜ ግን ይህን የሚቃረን ደግሞ አንድ ሌላ ገጠመኝ አገኘሁ፡፡ ይሄኔ ነበር ሁለተኛው ስሜት የተፈጠረብኝ፡፡ ባለፈው ሐሙስ ነው፡፡ በአጋጣሚ የዚያን ዕለት ቀደም ብዬ ከወትሮው በተለየ በማለዳ ነበር የተነሳሁት፡፡ የምግብና የመጠጥ ንግድ ቤቶች ገና ዝግ ሲሆኑ የገበያ ሰሞን ነውና የሸቀጣሸቀጥ ሱቆች እየተከፈቱ ነው፡፡ ለካ ቀን ቀን በጣም ወከባ ስለሚበዛ ብዙ ልብ የማንላቸው ነገሮች አሉ፡፡ እናም ከሲ ኤም ሲ ሚካኤል ወደ መገናኛ እየመጣሁ ጉርድ ሾላ አካባቢ አንድ አነስተኛ ሱቅ ቀልቤን ያዘችው፡፡
ሰውየው ዋና ዋናዎቹን ዕቃዎች ከማውጣቱ በፊት የበር ላይ ጌጦችን ነው እየሰራ ያለው፡፡ የባህል የሙዚቃ መሳሪያዎች ያሉበት ‹‹ፖስተር›› ሰቀለ፣ ሌላኛው ፖስተር ላይም የጠጅ ብርሌና ባህላዊው ገና ይታያል፡፡ ገናውን የያዙት ልጆችም የባህል ልብስ የለበሱ ናቸው፡፡ የሰውየው ሱቅ የሙዚቃ መሳሪያ ወይም ጠጅ የሚሸጥበት አይደለም፤ በቃ እንደማንኛውም ሌሎች ሱቆች ነው፡፡
እንደ ሞኝ ቆሜ ማስተዋል ጀመርኩ፡፡ የገረመኝ ደግሞ የሚሸጡ ዕቃዎችን ከመደርደሩ በፊት እነዚያን የባህል ጌጦች ማስቀደሙ ነው፡፡ እነርሱን ካየሁ በኋላ ታክሲ መያዝ ስለነበረብኝ ሰውየውን በልቤ እያደነቅኩ ወደ ሥራዬ ሄድኩ፡፡
ይህን ያሳየን እንግዲህ የገና በዓል ሰሞን ስለሆነ ነው፡፡ ጥሩ ነገርም ሲገኝ ማመስገን ይገባል ብዬ እንጂ በብዛት የምናየው ግን ይህን ዓይነት አይደለም፡፡ ከጥቃቅን ሱቆች ጀምሮ እስከ ትልልቅ የገበያ ማዕከላት ድረስ የምናየው በውጭው አምሳል የተሰራ የገና ዛፍ ነው፡፡ በስጦታ ዕቃዎች ላይ የምናየው ‹‹ስንታ ክላውስ››ን ነው፡፡ የሃይማኖታዊ ምስሎች ላይ ሳይቀር ‹‹Happy Christmas›› የሚል የእንግሊዘኛ ጽሑፍ ነው ያለው፡፡ በየሰዎች ላይ የምናያቸው የጌጣጌጥ ዕቃዎችም በ ‹‹ሳንታ ክላውስ›› ቅርጽ የተሰሩ ናቸው፡፡
እንግዲህ ይሄ ሁሉ ሲሆን አሳዛኙ ነገር ሸማቹም ምን እንደሆነ አለማወቁ ነው፡፡ ፒያሳ ገዳም ሰፈር አካባቢ የስጦታና የጌጣጌጥ ዕቃዎችን የሚሸጠው አቤል መላኩ አገርኛ የገና ስጦታ ማለት የትኛው እንደሆነ አያውቅም፡፡ ደንበኛ የሚፈልገውን ብቻ ያመጣል፡፡ ደንበኛም የአገራችንን ብሎ ጠይቆት አያውቅም፡፡ ሸማቹም እንደዚሁ ነው፤ የገና ስጦታ ወይም ጌጣጌጥ ሲባል ይሄው እንጂ ሌላ ያለ አይመስለውም፤ ለምን?
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የባህል ጥናት ትምህርት ክፍል መምህርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት መምህር ተመስገን በየነ ይህን ያስደረገው መገናኛ ብዙሃኑ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ እንኳን እንዲህ ዓይነት ትልልቅ በዓላት እያንዳንዱ የልጆች ጨዋታ ሁሉ አገርኛ ይዘት እንደነበረው የሚገልጹት መምህሩ መገናኛ ብዙኃን ግን ይህን አላሳዩም፡፡ እነዚህ ባህላዊ የሆኑ ነገሮች ያሉት ገጠር አካባቢ ነው፤ መገናኛ ብዙኃን ያንን አልሰራውም፤ አላስተዋወቀውም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ይሄ የባህል ወረራው ከ‹‹ቢዝነስ›› ጋር እንደሚገናኝ ነው የሚገልጹት፡፡ በብዛት የሚታየውም በትልልቅ የንግድ ቦታዎች ላይ ነው፡፡ ይሄም ጎልቶ የሚታየው በከተሞች አካባቢ ነው፤ በገጠር አካባቢ አሁንም ባህላዊ ይዘቱ አልጠፋም፡፡ ይሄ ገጠር አካባቢ ያለው ግን እዚያው ህብረተሰቡ ይጠቀምበታል እንጂ በመገናኛ ብዙኃን አልታየም፡፡ ከገጠር አካባቢ ወደ ከተማ የሚመጣውም መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚደጋገመውን ብቻ ስለሚያይ የራሱን እየጣለ የሚያየውን ይከተላል፡፡ በንግዱ ዘርፍ ውስጥ የውጭው ዕቃ በብዛት ስለሚገባ ነው የውጭ ዕቃዎች የሚገቡት፡፡
መገናኛ ብዙሃኑ ጎንደር ላይ ያለ፣ አክሱም ላይ ያለ ወይም ቦረና ላይ ያለ የገና በዓል አከባበርን ከሚያቀርብ ይልቅ ፈረንሳይ ወይም ጃፓን ወይም ዱባይ ውስጥ ያለውን ግን እየደጋገመ ስለሚያሳይ ተፅዕኖ መፍጠሩ የግድ ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃን ያለው ደግሞ ከተማ ቦታ ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃን ይህን ያህል ኃይል አለው፡፡ ለብዙ ዘመናት የኖረውን ባህል ነው አሥር እና አሥራ አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የባህል ወረራውን ያፋጠነው፡፡ የሚሰሩትም ገንዘብ ያለበት ቦታ ላይ ስለሆነ ነው ስለአገራዊ ገጽታው የማይጨነቁት፡፡ ገበያው በሞቀበት አካባቢ ከማስታወቂያ ሥራዎች ጀምሮ ይረባረቡበታል እንጂ ወደ አገርኛው አይሄዱም፡፡
በአገሪቱ ውስጥ ያለው አኗኗርም ሁለት ዓይነት መሆኑ የራሱ ሚና እንዳለው ነው አቶ ተመስገን የሚናገሩት፡፡ በገጠር አካባቢ ያለው ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱን ነው የሚያከብረው፡፡ ከተማ ውስጥ ያለው ግን የሌላውን ዓለም የአኗኗር ሥርዓት የሚከተል ነው፡፡ የአገር ውስጡም እንደ ኋላቀርነት ስለሚታይ ነው፡፡ የውጭው ግን የዘመናዊነትና የመሰልጠን መለያ ነው፡፡ ‹‹ይሄ ደግሞ የአውሮፓው ያን የሸቀጥ ማራገፊያ መሆን ነው›› ይላሉ፡፡ ሰው ሰራሽ አበባ መግዛት፣ የገና ዛፍ እያሉ መግዛት፣ የገና አባት እያሉ መግዛት የአውሮፓውያን የንግድ ማጧጧፊያ ነው፡፡ ይሄ ለኢትዮጵያውያን የባህል ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚም ውድቀት ነው፡፡ ከሰላሳና ዓርባ ዓመታት በኋላ አገሪቱ የአውሮፓ ስሪት ትሆናለች፡፡
አቶ ተመስገን፤ መገናኛ ብዙኃን ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል አንድ ማሳያ ይጠቅሳሉ። የሐበሻ ልብስ እንደገና እየተስፋፋ፣ ከፍተኛ የገቢ ምንጭም እየሆነ ነው፡፡ ይህ የሆነው በመገናኛ ብዙሃን ኃይል ነው፡፡ ከማስታወቂያ ሥራዎችም ይሁን በሌሎች መደበኛ ፕሮግራሞች የመታየት ዕድሉ ሲፈጠር የሐበሻ ልብስ ተወዳጅነቱ ጨመረ፤ ስለዚህ መገናኛ ብዙኃኑ ቢሰራበት ለውጥ ማምጣት እንደሚችል ማረጋገጫ ይሆናል፡፡
ገና ምን አገራዊ ቃና ነበረው?
የባህል ስፖርት መነሻው ራሱ ገና እንደሆነ ነው አቶ ተመስገን የሚነግሩን፡፡ የገና ጨዋታው ደግሞ በውስጡ ብዙ ሥርዓተ ክዋኔ አለው፤ ግን ያ ተዳፍኖ ነው የቀረ፡፡ የመጫወቻ ገናው፣ ሩሯ ከሳምንት በፊት ጀምሮ የሚጫወቱት ጨዋታ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን የራሱ የሆነ የአጨዋወት ሥነ ሥርዓት አለው፡፡ የአባቶችና የእናቶች ምርቃት አለበት፡፡
የገና ጨዋታው ብቻ ሳይሆን የገና ሰሞን የሚደረጉ ብዙ ባህላዊ ሥነ ሥርዓቶችም አሉ፡፡ እንደየ አካባቢው ባህል የጋብቻም ሆነ የሌሎች ማህበራዊ ግንኙነቶች የሚደረጉት የገና ሰሞን ነው፡፡ እነዚህ ባህላዊ ክዋኔዎች በማህበራዊ ሕይወት ውስጥ መልካም ግንኙነትን የሚፈጥሩና የሚያስተሳስሩ ናቸው፡፡ የራሳቸው የሆነ ሥርዓት እያላቸው ግን እነርሱ አይታወቁም፤ ጭራሹንም እየተረሱ እንዲመጡ ነው የተደረገው፡፡
ምን ይደረግ?
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የባህል ጥናት (ፎክሎር) ትምህርት ክፍል በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ ነው፡፡ ዳሩ ግን የባህል ወረራ እየባሰው እንጂ እየተሻለው አልመጣም፡፡ መምህር ተመስገን እንደሚሉት ትምህርት ክፍሉ ገና 15 ዓመት እንኳን ያልተሰራበት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የትምህርት ክፍሉ የአገሪቱን የባህል ወረራ ሊከላከል አይችልም፡፡ መከላከል የሚችለው ማህበረሰቡ ነው፡፡ የትምህርት ክፍሉ ጥናት ማድረግ አለበት፤ ማህበረሰቡ ደግሞ ባህሉን መጠበቅ አለበት፡፡ ማህበረሰቡ ለባህል ተቆርቋሪ ይሆን ዘንድ ደግሞ መገናኛ ብዙሃንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መሥራት አለባቸው፡፡
እንግዲህ ለባህላችን መወረር የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊነትን አለመወጣት፣ የማህበረሰቡ በባህሉ አለመኩራት ምክንያት ሆነዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ላይ በትልቁ መሰራት አለበት፡፡ አለበለዚ ባህላችን መወረር ብቻ ሳይሆን ጭራሹንም ተወርውሮ ሊጠፋና ሙሉ በሙሉ በሌላ ሊተካ ይችላልና!
አዲስ ዘመን 28/2011
ዋለልኝ አየለ