ኢትዮጵያ ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ራሷ አሰናድታ በአገሯ ያስቀረችው ከዛሬ 58 ዓመት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 13 ቀን 1954 ዓ.ም ነበር።
የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተመሰረተው በ1949 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ ነበር። መስራቾቹም ግብጽ ሱዳንና ኢትዮጵያ ነበሩ። በወቅቱ ኢትዮጵያን በመወከል በስብሰባው ላይ ታድመው የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ እና ሌተናል ኮሎኔል ገበየው ዱቤ ነበሩ። ፌዴሬሽኑ በተመሰረተበት አመት በሱዳን በተካሄደው የመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ አትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ተሳታፊዎች ነበሩ።
ከመስራቾቹ አንዷ የነበረችው ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ዎቹ ዓመታት ዋንጫውን ከፍ ማድረግ ከቻሉት አገሮች ተርታ ትጠቀሳለች። ሶስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅታ በወርቃማ ትውልዷ ለመጀመሪያ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ በመሆን ዋንጫውን ማስቀረት ችላለች። በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያረፈው እቴጌ ጣይቱ ሆቴል ነበር፡፡ሶስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማካሄድ የወሰደው ጊዜ አንድ ሳምንት ብቻ ነበር። ውድድሩ በተጀመረበት የመክፈቻ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥር 6 ቀን 1954 ዓ.ም በግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ቱኒዝያ ላይ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ለፍጻሜ አለፈ። ግቦቹን ያስቆጠሩትም ሉቺያኖ ቫሳሎ፣ ግርማ ዘለቀና መንግስቱ ወርቁ ነበሩ። በሌላኛው ምድብ ግብጽ ኡጋንዳን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ በፍጻሜው የኢትዮጵያ ተፋላሚ መሆኗን አረጋገጠች።
ጥር 11 ቀን 2011 ዓ.ም በታተመው አዲስ ማለዳ ቅጽ 1 ቁጥር 11 ላይ የሰፈረ መረጃ እንደሚያመለክተው ግብጽ ከአምስት ዓመታት በፊት በ1949 ዓ.ም የተደረገውን የመጀመሪያውን የአፍሪካ ዋንጫ ያነሳችው ኢትዮጵያን 4 ለ 0 በማሸነፍ ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት በዚህ ምክንያት ያደረባቸው ቁጭት ከሁለቱ አገራት ባላንጣነት ጋር ተዳምሮ የፍጻሜ ጨዋታውን ለማሸነፍ የጋለ ስሜት ውስጥ ገብተው ነበር።
የአዲስ አበባ ስታዲየም በ25 ሺ ተመልካቾች ጢም ብሎ ሞልቶ ግጥሚያው ተጀመረ። ለፍጻሜ ጨዋታው ኢትዮጵያ ያሰለፈቻቸው ተጫዋቾች ጊላ ሚካኤል ተስፋ ማርያም፣ ክፍሎም አርአያ፣ አስመላሽ በርሔ ፣ በርሔ ጎይቶም ፣ አዋድ መሐመድ፣ ተስፋዬ ገብረ መድኅን ፣ ግርማ ዘለቀ፣ መንግሥቱ ወርቁ፣ ሉቻኖ ቫሳሎ ፣ ኢታሎ ቫሳሎና ጌታቸው ወልዴ ሲሆኑ ተጠባባቂዎች ደግሞ ተክሌ ኪዳኔ ፣ ጌታቸው መኩሪያ፣ እስማኤል ጊሪሌ፣ ብርሃኔ አስፋው፣ ኃይሌ ተስፋ ጋብርና ነፀረ ወልደሥላሴ ነበሩ። ይድነቃቸው ተሰማ በዋና አሰልጣኝነት ፀሐየ ባሕረና አዳሙ ዓለሙ በረዳትነት ቡድኑን ሲመሩ ጥላሁን እሸቴ ደግሞ የብሔራዊ ቡድኑ ወጌሻ ነበሩ።
ጨዋታው በተጀመረ 35ኛው ደቂቃ ላይ ግብጽ በአብዱልፈታ በደዊ አማካኝነት ጎል አስቆጥራ ስታዲየሙ ጸጥ ረጭ እንዲል አደረገች። በ74ኛው ደቂቃ ግርማ ዘለቀን ቀይሮየገባው ተክሌ ኪዳኔ ግብ አስቆጥሮ ኢትዮጵያን አቻ አደረገ። ነገር ግን ከሽርፍራፊ ሰከንዶች በኋላ በደዊ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠሩ ደስታው ወደ ውጥረት ተቀየረ። ከደቂቃዎች ቆይታ በኋላ ሉቻኖ ቫሳሎ የአቻነቷን ግብ አገባ። ይህችን የአቻነት ጎል መንግስቱ ወርቁ እንዳስቆጠረ የሚገልጹ የታሪክ ሰነዶችም አሉ። ጨዋታው በዚህ መልኩ ቀጥሎ መደበኛ ጊዜው በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ።
የተጨማሪ ሰዓት ጨዋታው ተጀምሮ በ101ኛው ደቂቃ ላይ ግብጾች የፈጸሙትን የመከላከል ስህተት ተጠቅሞ ሉቻኖ ቫሳሎ ለራሱ ሁለተኛውን ለኢትዮጵያ 3ኛውን ግብ አገባ። በጨዋታው 117ኛ ደቂቃ ላይም አራተኛውንና የመጨረሻውን ጎል መንግስቱ ወርቁ ሲያስቆጥር በአዲስ አበባ ስታድየም ታድሞ የነበረው ተመልካች በደስታ ዘለለ። በዚህ መልኩ ኢትዮጵያ የ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ባለድል ሆነች። ብቸኛው ዋንጫ ከተገኘ 58 ዓመታት ቢቆጠሩም ለእግር ኳስ የተለየ ፍቅር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ዳግም የአፍሪካ ዋንጫውን የማንሳት ህልማቸውን እውን የሚያደርግ ብሔራዊ ቡድን አላገኙም።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 13/2012
የትናየት ፈሩ