ካንሰር በአለማችን እጅግ አስቸጋሪና ህይወት ቀጣፊ እየሆኑ ከመጡ በሽታዎች አንዱ ሲሆን፣ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረትም እጅግ ፈታኝ እየሆነ መጥቷል። በአሁኑ ወቅትም ኤች አይቪ ኤድስ፣ ሳምባ ነቀርሳና የወባ በሽታዎች በጋራ እያደረሱ ካሉት ሞት በላይ የሰዎችን ህይወት በከፍተኛ ደረጃ እየቀጠፈ ይገኛል። በሽታው በቂ ቁጥጥር ካልተደረገበትም በ20 አመት ጊዜ ውስጥ በየአመቱ 24 ሚሊዮን ለሚጠጉ የአለማችን ሰዎች ሞት መንሰኤ ይሆናል ተብሎ ተገምቷል።
የሳይንስ ሊህቃን ለካንሰር በሽታ ሁነኛ መፍትሄ ነው ብለው ያገኙት መድሃኒት ባይኖርም፣ በተለያዩ ጊዜያት በሰሯቸው ምርምሮች ለካንሰር ህመም መፍትሄ ይሆናሉ ያሏቸውን የጥናት ውጤቶች ይፋ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ሜዲካል ኒውስ ቱደይ በጨው ላይ አተኩሮ በአይጦች ላይ የተካሄደውን ለካንሰር በሽታ መፍትሄ ሊያመጣ ይችላል የተባለለትን አዲስ ጥናት ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል። የጥናቱ ተሳታፊ ተመራማሪዎች የካንሰር ህዋሳትን ለማጥፋት የሶዲየም ክሎራይድ ናኖ ፓርቲክሎችን በተሳካ ሁኔታ ተጠቅመዋል።
ለበርካታ አመታት ያህል ተመራማሪዎች ልዩ ልዩ የመድሃኒት አይነቶችን ለካንሰር ህመም መከላከያ ያበለፀጉ ቢሆንም፣ መድሃኒቶቹ ለካንሰር ህዋስ ብቻ ሳይሆን ለጤናማ ህዋሳትም መርዛማ ሆነው ቆይተዋል። እስካሁንም የካንሰር መድሃኒቶችን አድኖ የማግኘቱ ጉዳይ የእንፉቅቅ እየሄደ ያለው በቀረው የሰውነት ክፍሎች ላይ እምብዛም ጉዳት የማያስከትልና ውጤታማ ህክምና ለማግኘት የሚያስችል ሂደት ላይ ባለመደረሱ ነው።
በግሪክ ርእሰ መዲና አቴንስ የተሰባሰቡትና ጥናቱን ያካሄዱት የጆርጂያ ዩኒቨርስቲ የሳይንስ ሊህቃን ሶዲየም ክሎራይድ ወይም ጨውን ‹‹በናኖ ፓርቲክል መልክ›› ተመልክተዋል። ሶዲየም ክሎራይድ ለህይወት ወሳኝ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ባልሆነ የሰውነት ክፍል ላይ የሚውል ከሆነ ህዋሳትን ለሞት ሊያበቃ ይችላል።
ይህንንም ለመቆጣጠር የህዋሳትን የውስጥና የውጨኛው ክፍል የሚለዩና የከበቡ የአይዎን መተላለፊያዎች ወይም ቻናሎች ጨው እንዳይገባ ይከላከላሉ። በሰውነት ሴሎች ውስጥ በውጭ በሶዲየምና ክሎራይድ አይዎኖች እና በውስጥ በፖታሲየም መካከል ያለው እኩሌታ መጠበቅ ወጥነት ያለው የህዋሳት አካባቢ ለመፍጠር ያስችላል።
አጥኚዎቹ ንድፈ ሃሳባቸውን የሞከሩት የሶዲየም ክሎራይድ ናኖ ፓርቲክሎች ‹‹ትሮጃን ሆርስ ስትራቴጂ›› በሚል አይዎኖች ወደ ህዋሳት እንዲቀርቡ በማድረግና የአይዎኖችን የተስተካከለ የህዋሳት አካባቢዎችን እንዲረብሿቸው በማድረግ ነበር። የሶዲየም ናኖ ፓርቲክሎቹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሶዲየምና ክሎሪን አተሞችን የያዙ በሆንም ጨው እንዳይገባ የሚከለክሉት የአዮን ቻናሎች ወይም መተላለፊዎች እንደ ጨው እንዳይቆጥሯው ተደርጓል። በውጤቱም የሶዲየም ክሎራይድ ናኖ ፓርቲክሎቹ/ የሶዲየም ክሎራይድ ውህዶች/ ወደ ህዋሳት ለመግባት ነፃ አድል ያገኛሉ። ወደ ህዋሳት ውስጥ ከገቡ በኋላም በሴሎቹ ውስጥ ተይዘው የሚቀሩ የሶዲየምና ክሎሪን አይዎኖችን ይለቃሉ።
አዮዎኖቹ ህዋሳቱን በመረበሽ የውስጠኛውን የህዋሳት ክፍል ከውጨኛው የሚለየውን ሽፋን ያላቅቃሉ።
የሕዋስ ሽፋን ሲከፈት ደግሞ ሶዲየም እና ክሎሪን አተሞች ይለቀቃሉ። ይህም በተራው የበሽታ መከላከል ምላሽ ያስከትላል ።
የአይጥ ሞዴልን በመከተልም የሳይንስ ሊህቃኑ ይህንኑ ንድፈ ሃሳባቸውን ሞክረዋል። የሶዲየም ክሎራይድ ናኖ ፓርቲክሎቹን በዕጢዎች ላይ ከወጉ በኋላ ዕድገቱን መከታተል መመዝገብ ይጀምራሉ። በመቀጠልም የእነዚህን ዕጢዎች እድገት በቁጥጥር ቡድን ስር ካሉና ተመሳሳይ የሶዲየም ክሎራይድ መጠን ከወሰዱ አይጦች ጋር አነፃፅረዋል።
በዚህም የጥናት ቡድኑ ከቁጥጥር ቡድን አይጦች ጋር ሲነፃፀር ሶዲየም ክሎራይድ ናኖ ፓርቲክሎቹ የአይጦቹን እጢዎች 66 በመቶ መቀነሳቸውን አረጋግጧል። ክሎራይድ ናኖ ፓርቲክሎቹ በአይጦቹ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንዳላስከተሉም ለማረጋገጥ ችለዋል።
የጥናት ቡድኑ መሪ ረዳት ፕሮፌሰር ጂን ዢ እንደሚያብራሩት፤ ከህክምናው በኋላ እነዚህ ናኖ ፓርቲክሎች ከሰውነት ፈሳሽ ስርዓት ጋር የተዋሃዱ እና ስልታዊ ወይም የተከማቸ መርዛማነት የሚያስከትሉ ጨዎችን አያካትቱም። ክሎራይድ ናኖ ፓርቲክሎቹን በከፍተኛ መጠን በተወጉ አይጦች ላይም አንድም የመመረዝ ምልክት እንዳልታየ አስረድተዋል። ‹‹እንዲህ አይነቱ ካንሰርን የማከም ዘዴ ደህንነቱ የተጠበቀ ይመስላልም›› ብለዋል።
የካንሰር ሴሎች ከጤናማ ሴሎች በበለጠ ለክሎራይድ ናኖ ፓርቲክሎች የተጋለጡ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ፤ ምን አልባት የካንሰር ሴሎች ከፍተኛ መጠን ያለው ሶዲየም በውስጣቸው ስለሚይዙና ይህም ከፍተኛ ጫና ሊያሳድርባቸው ከሚችል ምክንያት የመነጨ መሆኑን አጥኚዎቹን አሳምኗቸዋል።
በአሁኑ ወቅት በርካታ ተመራማሪዎች የተለያዩ የናኖ ፓርቲክል አይነቶች ለህክምና ጠቃሚ ስለመሆናቸው ምርምር ያካሄዱ ቢሆንም እስካሁን ጥቂቶቹ ብቻ ለህክምና ሊበቁ ችለዋል። የጥናት ቡድን መሪው ጂን ዢ ‹‹ዋናውና አሳሳቢው ጉዳይ የፓርቲክሎቹ መርዛማነት፣ ቀስ ብሎ ከሰውነት ውስጥ መውጣትና ያልተጠበቀ የረጅም ጊዜ የጤና ተፅእኖ በታካሚው ላይ ማሳደር ናቸው›› ብለዋል። ይሁንና ሶዲየም ክሎራይድ ናኖ ፓርቲክሎች የተለያዩ መሆናቸውን፤ ጉዳት ከማያስከትሉ ቁሶች የተሰሩና መርዛማነታቸውም በናኖ ፓርቲክል ውስጥ የሚገባ መሆኑን የጥናቱ መሪ አብራርተዋል።
በሁለተኛው የጥናቱ ክፍል የሳይንስ ሊህቃኑ በሶዲየም ክሎራይድ ናኖ ፓርቲክሎች በጠፋው የካንሰር ሴል ውጤት ላይ ምርምር አድርገዋል። እነዚህኑ ህዋሳት በአይጦች ላይ የወጉ ሲሆን አይጦቹ በአዲስ የካንሰር ህመም ላለመያዝ ሰውነታቸው ተከላክሏል። ይህም በሌላ አባባል ህዋሱ እንደ ክትባት ሆኗል ማለት ነው። ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት የሶዲየም ክሎራይድ ናኖ ፓርቲክሎች የካንሰር ሴሎች እንዲሞቱና ድንገት ተከፍተው በሽታ የመከላከል ምላሽ ስለሚያሳዩ መሆኑን የሳይንስ ሊህቃኑ አምነዋል።
በተመሳሳይም የሳይንስ ሊህቃኑ በተገለሉ የእጢ ህዋሳት ላይ ተጨማሪ ጥናት አካሂደዋል። የሶዲየም ክሎራይድ ናኖ ፓርቲክሎችን በመጀመሪያዎቹ እጢዎች ላይ ከወጉ በኋላ የሁለተኛ እጢዎችን የእድገት መጠን ለክተዋል። በዚህም የጥናት ቡድኑ ከሁለተኞቹ በቁጥጥር ስር ካሉ እጢዎች ይልቅ የመጀመሪያዎቹ እጢዎች አድገት እየቀነሰ መምጣቱን አግኝተዋል።
ብዙውን ጊዜ ካንሰር በአይጦች ላይ ከሺ ጊዜ በላይ ሊፈወስ የሚችል ቢሆንም ሁሉም ጠቃሚ መድሃኒቶች በሰዎች ላይ ከመሞከራቸው በፊት በእንስሳት ላይ ማለፍ እንደሚገባቸው የሳይንስ ሊህቃኑ በመጨረሻ መግባባት ላይ ደርሰዋል። የሶዲየም ክሎራይድ ናኖ ፓርቲክሎቹ የፊኛ ፣ የፕሮስቴት ፣ የጉበት፣ የጭንቅላት እና የአንገት ካንሰር ሕክምና መተግበሪያዎችን ለማግኘት የሚስችሉ እንደሚሆኑም በተለይ የጥናት ቡድኑ መሪ ጂን ዢ ተስፋ አድርገዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 12/2012
አስናቀ ፀጋዬ