ዛሬ የከተራ በዓል ነው፡፡ በዓሉ በመላ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ይከበራል፡፡ ከተራ ስረቃሉ ግዕዝ ሲሆን ትርጉሙም ከተረ፣ ሰበሰበ፣አገደ የሚል ትርጉም እንዳለው የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገብ ቃላት ይገልጻል፡፡ የበዓሉ ስያሜም ውሃን በአንድ ቦታ በመከተር ወይም በመሰብሰብ የሚከናወን በዓል በመሆኑ የተሰጠው እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዓሉ በተለያዩ ስፍራዎች የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በአንድ ቦታ ተሰባስበው የሃይማኖት አባቶች ጸሎት ሲያደርሱ የሚያድሩበት ትልቅ የመሰባሰብ በዓል ነው፡፡
ይህ በዓል በኢትዮጵያ ከ12ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሲከበር እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዓሉ የጥምቀት በዓል በሚከበርበት ዋዜማ የሚከበር ሲሆን ቀደም ሲል የቤተክህነት አገልጋዮች የጥምቀት በዓል ከመከበሩ አንድ ቀን ቀደም ብለው ጀምበር ከመጥለቋ በፊት ተሰባስበው ውሃ በመገደብና ታቦታቱን በመያዝ ለጥምቀት በዓል ዝግጅት የሚያደርጉበት በዓል ነው፡፡ በዚህ እለትም የሃይማኖት አባቶች ባዘጋጁት ዳስ ውስጥ ሌሊቱን ሙሉ በመፀለይና ፈጣሪን በመለመን ያሳልፋሉ፡፡
እነሆ የዘንድሮው የከተራ በዓልም በዛሬው እለት በመላ አገሪቱ በድምቀት ይከበራል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ፣ ጎንደር እና ባሌ በልዩ ሁኔታ የሚከበር ሲሆን ምዕመናንም በስፍራው በመገኘት ታቦታቱን በመሸኘትና በስፍራውም በማደር ሃይማኖታዊ ክብረበዓሉን በድምቀት ያከናውናሉ፡፡
የዘንድሮ የጥምቀት በዓል ለየት ባለ ድምቀት ይከበራል፡፡ ምክንያቱም በዓሉ በዓለም አቀፉ የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ተቋም(ዩኔስኮ) በተመዘገበ ማግስት የሚከበር በመሆኑ ልዩ ትኩረት ስለሚሰጠው ነው፡፡
በዓሉ በዩኔስኮ በመመዝገቡ በርካታ ቱሪስቶች በዚህ በዓል ላይ እንዲሳተፉ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ ይህ ደግሞ ለአገራችን የቱሪዝም ዘርፍ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም አገራችንን ማስተዋወቅና የቆየውን የኢትዮጵያዊነት ባህል ማሳየት ይጠበቅብናል፡፡ በተለይ በብዙ አገራት የማይገኙት ጠንካራ የመተባበር፣ የመቻቻል እና የአንድነት ምልክቶች በዓሉን ምክንያት በማድረግ የምናሳይበት ወቅት ሊሆን ይገባል፡፡
በተለይ ቱሪስቶች በሚገለገሉባቸው የትራንስፖርት፣ የማስጎብኘት፣ የሆቴልና ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ዜጎች ሁሉ ተገቢውን አገልግሎት በመስጠትና ቱሪስቶች በተገኘው አጋጣሚ ሆሉ አገራችንን መልካም ገጽታ በሚገነባ መልኩ ትብብር በማድረግ ቱሪስቶችን መደገፍ ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ የተለያዩ ሐይማኖቶች የሚገኙባት ህብረብሄራዊ አገር ናት፡፡ ይህ ህብረብሄራዊነት ደግሞ በፍቅር የታጀበ ነው፡፡ ለዚህም ሰሞኑን በከተራ በዓል ዋዜማ ላይ የሚታዩ የአንድነት፣ የመከባበርና የመረዳዳት ተምሳሌቶች ማሳያዎች ናቸው፡፡ ለዚህም የተለያ አብነቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡
እንደሚታወቀው ለጥምቀት በዓል ታቦታቱ የሚያልፉባቸውንና የሚያድሩባቸውን ስፍራዎችን የማስዋብ ስራ ሰሞኑን በስፋት ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች አካባቢያቸውን ሲያፀዱና ምንጣፍ ሲያነጥፉ ከርመዋል፡፡ በዚህም በተለይ አዲስ አበባ ከመቼውም ጊዜ በላይ ውበትን የተላበሰችበትና የደመቀችበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
በዚህ የማስዋብ ስራ ውስጥ ደግሞ የሚሳተፉት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ብቻ አይደሉም፡፡ በርካታ ሙስሊም ወጣቶች እና የሌላ እምነት ተከታዮችም የዚህ አካል ነበሩ፡፡ እነዚህ ወጣቶች ይህንን ስራ ሲሰሩ በማንም አስገዳጅነት ወይም ጥሪ ሳይሆን በራሳቸው ተነሳሽት ነው፡፡ ወጣቶችን ያስገደዳቸው ለረጅም ዘመን የዘለቀው የአብሮነትና የመተሳሰብ እንዲሁም የአንድነት መንፈስ ነው፡፡
ይህ የወጣቶቹ ስራ በዚህ ላይ ብቻ የሚንፀባረቅ አይደለም፡፡ ኢትዮጵውያን አንዱ የሌላውን በዓል ከማክበር ጀምሮ አብሮ የመብላትና የመጠጣት፣ በዓልን በደስታ አብሮ የማሳለፍ የቆየ እሴት ያለን ህዝቦች ነን፡፡ በዚህ የተነሳ የከተራ በዓልም የዚሁ አካል ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ የከተራ በዓልና በዋዜማው የታየው የአንድነት፣ የመተሳሰብና የፍቅር ድባብ ዘላቂ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ሰላማችን ይረጋገጣል፤ አንድነታችንም ይበልጥ ይደምቃል!
አዲስ ዘመን ጥር 10/2012