ነገርና ቃል፤ አባባልም እንዲሁ እንዳመጣጡ ነው የሚተረጎመው። የቃል ፍች በአውደ-ቃል ይወሰናል ይላሉ ፤ የቋንቋ ሊቃውንት። ለዛሬ የመረጥኩላችሁ ርእስ ግን ትርጓሜ በእኔው የአረዳድ መጠን የተፍታታ ነውና ፤ አብረን እናዝግም።
በዘመናችን በርካታ የቋንቋው አዋቂዎች፣ የሚስማሙበት አንድን ሰው ነገረ ፈጅ ነው ሲሉ በአንድ ጉዳይ ዙሪያ የጀመረውን ነገር ከሥረ መሰረቱ፣ በያዘው አግባብ ሳይቋጭ ወይም እልባት ሳይሰጥ የማያቆም ሰውን የሚያመለክት ነው። በዚህም መሰረት ለዚሁ ሥራ አግባብ የተሰየሙ ሰዎች በነገረ ፈጅነት በተሰጣቸው ሥራ ወይም ጉዳይ መሰረት ሥራቸውን የሚያከናውኑና ጉዳዩን በአግባቡ ለመፍታት ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች መጠሪያ ቃል ነው።
ለዚህም ነው ተቋማት፣ ግለሰቦች ድርጅቶች ወይም ኩባንያዎች ነገረ ፈጅ ለመቅጠር የወጣ ማስታወቂያ እያሉ ጉዳያቸውን በህግ አግባብ የሚጨርስላቸው ሰው የሚቀጥሩት። ሰዎቹም ስማቸውን ተቀብለውት የዚህ መስሪያ ቤት ጠበቃ ነኝ ከማለት ይልቅ ነገረ-ፈጅ ነኝ ማለት የሚቀናቸው።
በአይነ ህሊናችሁ ግን ስታስቡት ፤ ነገረ ፈጅ የሆነ ሰው ነገር ባይኖር ምን ይሆን ነበረ? ምንም ማለት አትችሉም ፤ ምክንያቱም ነገር እንጀራው ነዋ! የጀመረውን ነገር በህግ አግባብ ተከራክሮ የደንበኛውን ጥቅም ለማስከበር ጥረት ያደርጋል። ህጉ በፈጠረለት መንፈስና አንቀጽም መሰረት ተረድቶ ያሸንፋል ወይም ይረታል (“ረ”ን ጠበቅ አድርገው ያንብቧት)።
የሰው ልጆችም ህግ ይደግፈናል፤ ህጉ ይረዳናል ብለው በሚያስቡበት ጉዳይ ላይ በነገረ-ፈጆቻቸው ድጋፍ ይሟገታሉ፤ ይከራከራሉም።
አሁን በቀደም እለት አንድ ነገረ-ፈጅ ከሆነ ጓደኛዬ ጋር ስናወጋ እንዲህ አለኝ። አንዳንዴ የሚገጥሙን ጉዳዮች ከጉዳዮቹ ባለቤቶች አንጻር ስታየው ትገረማለህ። እናም እርግጠኛነት ሳይሰማህ ትገባበትና ትደነቃቀፋለህ አለኝ። እስቲ አንዱን ምሳሌ አድርገህ አጫውተኛ አልኩት።
አንዱ ሰው ደወለና ፣ እገሌ ነህ አለኝ። አዎ አልኩትና ማን ልበል አልኩት ። ማንነቴ ለጊዜው ይቆይህና “ኬዙን” ልንገርህና ያዋጣ አያዋጣ እንደሆነ ትነግረኛለህ አለኝ። ነገር በዓይን ይገባል ይባላልና ፤ ተገናኝተን ብንነጋገር አይሻልምን? ስለው በቃ ወኪሌን ልክብህና እርሱ ያጫውትሃል፤ ከዚያም መልሱን ትነግረዋለህ ፤ አለኝና ሰዓት ተቀጣጠርንና ስልኩን ዘጋው።
በተባባልነው ሰዓት ተገናኘን ፤ እያወራኝ ሳለ ድምጹን ለየሁት ወኪሉ ሳይሆን ራሱ ነው። እሽ… ታሪኩን ቀጥልልኝ አልኩትና፤ ህጋዊ ክርክሩንም ስንጀምር በወኪል ነው፤ የምናወራው ወይስ ሰውየው ራሱ በአካል ይመጣል ፤ ስል ጠየኩት። ያኔውኑም ሰውየውን ማግኘት ችግር የለውም ፤ አለኝና ወደ ህግ ማምራት እንችላለን ማለት ነው? ብሎ ፈገግ አለ። ጉዳዩን መጀመር እንችላለን ማጥናት ግን አለብኝ፤ መጨረሻው ላይ የሚዳኘንም ህግ ነው፤ አልኩት።
እንዴት ነው እሱ…? ላናሸንፍ ነው እንዴ የምንሟገተው አለኝ፤ ቆጣ ብሎ። አሸናፊነታችንን፣ ህጉና የነገሩ አግባብነት እንዲሁም የተካሳሾቻችን ጉልበት ይወስነዋል ፤ ስለው ፤ “ማለት?” ሲል፣ እነርሱ የሚመጡበት የህግ አግባብ አዋጭነት ከእኛ የህግ አካሄድ ካነሰ ይሸነፋሉ፤ ከበረታ ግን ፍትህ ወደሚያደላበት ይበይናል ፤ አልኩት።
በራስህ አትተማመንም ፤ ማለት ነው?
የለም በህጉ እተማመናለሁ ፤ ማለቴ ነው።
ስለዚህ ጉዳይህን ንገረኝ ፤ አልኩት።
ይኸው፣ አለ ባለጉዳዩ እርሱ መሆኑን ሳያስተባብል… ሚስቴ ለፍቼበታለሁ በሚል ሰበብ ስንለያይ ሀብቷን በሙሉ ሳታካፍለኝ ልታሰናብተኝ አስባለች ፤ አለኝ።
ለምንድነው የምትለያዩት ስለው ፤ የወንድን ነገር ታውቀው የለ፤ አንዲት ልጅ አሳዝናኝ ስረዳት ነበረና እርሷ ደረሰችበትና ሌላ ሚስት አግብተሃል አስብላ ምስክር ቆጠረችብኝና ከሰሰችኝ።
ይች የምትረዳት ልጅ ከኢኮኖሚያዊ እርዳታ ውጭ ሌላ ግንኙነት የለህም ማለት ነው? እርሷስ ስለዚህ ቃል ምን አለች? የለኝም ስልህ …አንድ ሁለት ቀን አብሬያት ቀብጫለሁ፤ ግን ሚስቴ አይደለችም ሰማኒያ ወላ 40 የለንም እንዲሁ ነገር ሲያጋግሉ ነው፤ አለኝ ።
ስንት ጊዜ ሆናችሁ ስትረዳት?
ሁለት ዓመት ገደማ ቢሆን ነው።
ከሚስትህ ከተጋባችሁስ?
አምስት ዓመታችን ነው።
ማለት እርዳታህን መስጠት የጀመርከው በትዳራችሁ ፕሮጀክት አጋማሽ ላይ ነዋ።
አዎ ልትለው ትችላለህ ። (ሁሉንም ጥያቄ እኔ እያለ መመለሱን ልብ በሉልኝ)
በዚህ ጊዜ ውስጥ በመካከላችሁ ሰው አልተፈጠረም ? ማለት ልጅ አልወለዳችሁም ?
እርዳታውን የቀጠልኩትም በዚህ የተነሳ ነው።
ስለዚህ ሰማንያም ባይኖራችሁ ከሁለት ወደ ሶስት እንዲያውም ከዋናዋ ጋር አራት ሆናችኋላ?!
ማለቴ ወንድ ልጅ እንደሚሳሳት ይገባሃል ….ተሳስቼ እንጂ አስቤበት አይደለም፤ ወደዚህ ዓለም ልጁ የመጣው።
እና…ልጁ በስህተት የመጣ ይምሰልህ እንጂ የእግዚአብሔር እቅድ ነው፤ ለማንኛውም ወንድሜ ወደ ቁምነገሩ እንምጣና ሞራላዊ ጥያቄ በሚያስከትል ነገር ላይ እጄን አልከትም። ልጁም ይደግ፤ አንተም የተሰጠህን ውስን ሀብት ተጠቀምበት እንጂ ወደስህተትህ አትመለስ። ስህተትም በስህተት ፣ ጥፋትም በጥፋት አይታረምም፤ አልኩት።
እኔ የሞራል ስብከት አይደለም የምፈልገው፤ ህግ ፊት አቅርቤ ላንቀባርራት እፈልጋለሁ፤ አለኝ።
ማለት?
እሷንና ልጆቿን ፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት ሳላንከራትትማ እንቅልፍ የለኝም ፤ ደግሞ አንተ ባትፈልግ እኔ አድርጌ አሳይሃለሁ፤ ሲል ከመቀመጫው ተነስቶ ተንቆራጠጠ።
መቀጠል ትችላለህ ነገር ግን ምንጊዜም ጠማማ ዓላማ በምንም ዓይነት ቀና መንገድ ወደግቡ አይደርስም ፤ ይህንን አትርሳ። ፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት ልታዞራት ትችላለህ ግን በቀኑ መጨረሻ 50 አስበህ 20 ፣መቶ አስበህ ሰላሳ ወይም ምንም ይዘህ የምትቀረው አንተ ነህ። ጉዳዩን ወደ ሰበር ችሎት ልትሰቅለው ትችላለህ፤ ነገር ግን በላይኛውም ፍርድ ቤት አሸናፊ እንደማትሆን ልነግርህ እወዳለሁ። ምክንያቱም እውነትም ክብደትም የሌለው በክፋት ተጸንሶ፣ ያለፍሬ የሚወለድ ከንቱ ሃሳብ ነው፤ የያዝከው ስል ነገርኩት።
በመጨረሻም ሊወጣ ሲል ጠቀም ያለ ኮሚሽን ባስብልህስ አለኝ። ሳቅ እፍን አደረገኝና ምን ያህል ነው፤ ጠቀም ያለ ኮሚሽን ፣ ወይም ከፍ ያለ ክፍያ ያልከው ስል ጠየቅኩት።
በንብረት ልከፍልህ እችላለሁ።
ምን ?
በሞተር ከምትንቀሳቀስ፣ መኪና ብገዛልህስ? ወይም ኮንዶሚኒየም ብሸምትልህ…..
ለዚህ ሰውዬ፣ ጥብቅና መቆም ፣ በእሾህ ላይ እንደመረማመድና በመጨረሻ እጅንም እግርንም በደም አበላ መንከር ነው አልኩና፤ በልቤ፣ ስለክፍያው አመሰግናለሁ፤ ሁለቱም የጠራሃቸው ነገሮች ያስፈልጉኛል፤ ግን አንተ ባልከው መንገድ ግን አይደለም ፤ ደህና ክረምልኝ አልኩት፡ ከመውጣትህ በፊት ግን፣ አሁን ላማከርኩህ ክፍያ ለጸሐፊዬ ብር መክፈል እንዳትረሳ ብዬ ስለው፣ ሁለት ሶስት መቶ ብር ከኪሱ መዥረጥ አድርጎ ሜዳው ላይ በትኖት ሄደ።
እና ነገር በአግባቡ ስንፈጅ ነገርን ያለመላው ለመግመድ የሚፈልጉ ፣ ነገረ በሎችም ይገጥሙናል ማለቴ ነው፤ ሲል አጫወተኝ።
ይኼንን ወዳጄን ታዲያ ወዲያውኑ ያልኩት አንተ ነገረ ፈች እንጂ ነገረ ፈጅ አይደለህም። ምክንያቱም ከሚወስደው ይልቅ ያለው ፤ ከሚታሰበው ይልቅ ያሰበውና የሚያዋጣው፤ ከሚያጓጓው ይልቅ ተገቢው ነገር እንዲሆን የሚፈልግ የእምነቱ ተገዢ የሆንክ ሰው መሆንህን ነው፤ የተረዳሁት።
በህይወታችን ውስጥ ነገራቸውን ሊያራግፉባችሁና የኑሯቸውን ቆሻሻ ተሸክማችሁ እንድታጓጉዙላቸው የሚወድዱ ሰዎች ሞልተዋል። እነዚህን መሰል ሰዎች ሲጠሉ እንድትጠሉላቸው፤ ሲጣሉ እንድትዋጉላቸው የሚፈልጉ እና አብራችኋቸው ካልቆማችሁ ከእናንተም ጋር ቢሆን ወደ ጸብ ለመግባት የማያመነቱ ግብዞች ናቸው። በራሳቸው ስለማይተማመኑ አጋዥ ፍለጋ ከስፍራ ስፍራ ይሯሯጣሉ። በተቻላቸው መጠንም የቆሰቆሱትን የራሳቸውን ፀብ ሰው እንዲጋፈጥላቸው ያበረታታሉ። ነገሩ ከርሮና ገፍቶ ከመጣ ደግሞ በገዛ ፀባቸው፣ ገላጋይ ከመሆን አይመለሱም ።
እነዚህ ጭር ሲል የማይወዱ ግብዞች በቤተ እምነት መካከል ፣ በስፖርት ቡድኖች፣ በፖለቲካ ሃይሎች፣ በጓደኞችና በዘመዳሞች መካከል ራሳቸውን ከማስገባት አይመለሱም።
ጸባቸውን እንደ ወተት በጉያቸው ይዘው መጥተው ይግቱህና ባንተ ላይ ቁጭት ፈጥረው ያንቀሳቅሱሃል። በተለይ ጸብ በእምነትና በዘር ሲነሳማ ለእነርሱ ገበያቸው ነው። አንተ ከማን ታንሳለህ ፤ አንተም እንደ እሱ ሱሪ ታጥቀሃል፤ አንተም እንደ እርሱ ደም አለህ። ስለዚህማ እንደ መናቅ የሚያንገበግብ ነገር የለም ይሉሃል። ከዚህ በኋላም ፣ አንተ እናት ቤተ-ክርስቲያኔ ተደፈረች ፣ ነዋየ- ቅዱሳቱ ተመዘበሩ፤ በደጀ ሰላሙ ተደነሰበት፣ በቤትህ ላይ ጣታቸውን ቀሰሩብህ እያሉ ሲነግሩህ …መቼ ሄጄ ስፍራው ላይ ወድቄ ልጽደቅ እንጂ የምትለው አታመነታም። ይህንን ከመንፈሳዊነት ጋር የተቆራኘ ቅስቀሳ የሚያዛምቱትም ፊደል ቆጠር በሆኑ ሐሳዊያን አማካይነት ሲሆን፣ ለጥላቻቸው ማራገቢያነት ጥቃቅን ችግሮችን በመጠቀምና የማይበርድ ጸብ በመፍጠር ለራሳቸው የላቀ ግብ መጠቀሚያ ያደርጉሃል።
ይልቅ አንተ ማለት ያለብህ ፤ ለዚህ ምላሽ የምሰጠው በፍቅር ነው ወይስ በጸብ ፣ በግብግብ ነው በጽሞና ፣ በመወያየት ነው ወይስ በመፋጠጥ ብለህ የክፉዎችን ግብዣ በደግ ለመመለስ መዘጋጀት ነው። አንድ ጊዜ የተሞተላት የጸናችና እየተሰራች ያለች ቤት ሌላ ሰሪም ቃፊርና አጋዥ፤ አዛዥና ናዛዥ አያስፈልጋትም። ቤቱ የባለቤቱ ነው። እንዴት እንደሚጠብቀው እርሱ ያውቃል እንጂ አንተ አይደለህም ፤ የፖሊስን ሥራ ለፖሊስ ነው መተው ያለብህ ። አምላክ ፖሊስም ቃፊርም ፣ ክላሽም፣ ፆርም፣ ቤንዚንም፣ ሞልቶቭም አያስፈልገውም።
ነጮቹ አንድ ዘመን “የመስቀል ጦርነት” ብለው በኢየሩሳሌም ደም አፋሳሽ እልቂት ፈጥረው ነበረ፤ ውጊያው የዘመኑ የሰው ልጆች ከንቱ ሙከራ ስለነበረ አምላክ ለስንፍናቸው ተዋቸው እንጂ ሰልፍ ገብቶ አልተዋጋላቸውም። አሁንም በዚህ ዘመን ነገረ-በሎች በአንድ ሐገር፣ በአንድ ሰፈር፣ በአንድ ዞንና ቀጠና ውስጥ እንዲህ ዓይነት ውጊያ፣ ለመፍጠር ሲሞክሩ ያለጭንቀት ሳቅ ብለህ ይህን ውጊያ የምዋጋለት እርሱ እንደ ሰው ሰነፍ ነውን ? ደም አፍሳሽስ ነው ወይስ አንዴ ደሙን አፍስሶ ዋጋ ከፍሎ ጨርሶልኛል ማለት ነው ፤ያለባችሁ።
በየትኛውም እምነት ውስጥ ያላችሁ ያገሬ ሰዎች፣ አምላክ የሰላም እንጂ የጦርነት ነጋሪት ጎሳሚ አለመሆኑን ለማጤን ሩቅ መሄድ አያስፈልጋችሁም ። ምክንያቱም ስሙም ሩህሩህ፣ አፍቃሪና ታላቅ እንጂ ጨካኝ ጠበኛና ትንሽ አምላክ አይደለም። ሰዎች በየትኛውም መለኪያ ትናንሽ ግቦቻቸውን ለማሳካት ከዘር ሌላ ሰውን የሚቀሰቅሱበት ዓውደ ውጊያ የሚያወጡበት መንገድ የእምነት (የሃይማኖት) ጉዳይ ነው። ነገረ-በሎች እምነታችሁን የጸብ በትር ሲያደርጉባችሁ ዝም ብላችሁ እትጎተቱላቸው፤ አትሳቡላቸው፤ ቀለበት ውስጥ አትግቡላቸው።
አስመሳዮች እነ እገሌ፣ የእንቶኔን እምነት በ2033 ዓ/ም ለማጥፋት እቅድ ይዘው በ2015ዓ/ም በድብቅ እንትን ሐገር ላይ በተያዘ አጀንዳ እየተንቀሳቀሱ ነው፤ ማለት የሰውን ልብ ሸረፍ ያደርጋል ግን ፤ ምንጭህ ከየት ነው ነገርህ ወዴት ነው ማለት ነው ያለባችሁ። አንዳንዶች ከዘመን ቀድመው የጸብ አጀንዳ ይቀርጻሉ፤ ሌሎች ደግሞ ያረጀና ያፈጀ ዘመን ትርክት ይዘው ክስና ወቀሳ ውስጥ ይገባሉ። ዘመን አስቀዳሚዎቹም ሆነ የአሮጌ ዘመን እስረኞቹ ግብ ሲተረተር ሌላ አይደለም። የአምነት ቁጭት በመፍጠር የሰውን ልብ ወደሚፈልጉበት የሸር አዙሪት መክተትና በጊዜ ሂደት የራሳቸውን አጀንዳ ማስፈጸም ነው።
ስለዚህ ለነገረ -በሎች እጃችሁን በየትናንሹ አጀንዳ ውስጥ በመክተት መተኪያ የሌላትን ህይወታችሁን ፣ አንድ ጊዜ ብቻ ለመኖር የተፈቀደላችሁን ነፍሳችሁን አትገብሩላቸው። እነዚህ ዘመን የሞተባቸው ጁጁዎች፣ የራሳቸውን ጊዜ ቅርጥፍ አድርገው በልተው የእናንተንም ዘመን ለመብላት የማያቅማሙ የክፋት ምንጮች ናቸው።
ታላላቅ መጻህፍት እንደሚነግሩን የክፉ መታሰቢያው በየጫካው ጥሻ ውስጥ በሐረግ ሲተበተብ፣ የደጋጎች (ሄራን) መታሰቢያ ደግሞ በትውልድ ልብ ውስጥ ተተክሎ እየለመለመ ልብን በኩራት እፍን ያደርጋል። ነገረ-ሰሪዎች መቼም የሰውን ልብ ስለማያገኙ የድንጋጤ ከዘራቸውን እያወዛወዙ ከጨለማቸው ጋር ይንከራተታሉ፤ እንጂ አይረቱም ። ከነገረ በልነት ይልቅ ነገረ-ፈጅነት በስንት ጣዕሙ!!
የመልካም ጣዕም ሳምንት ይሁንላችሁ!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 9/2012
ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ