እሁድ የካቲት 23 ቀን 1958 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ 25ኛ ዓመት ቁጥር 308 እትም በአዲስ አበባ ጥርስ ያላት ሕፃን ስለመወለዷ የሚገልጽ ዘገባ አስነብቦ ነበር።
ወይዘሮ ዘነበች ጥርስ ያላት ሕፃን ወለዱ
በአዲስ አበባ ግርማዊት እቴጌ ትምህርት ቤት አጠገብ ዘነበች ኃለማሪያም የተባለች ሴት መንታ ልጆች ወልዳለች። አንዱ ወንድ ሲሆን ሁለተኛይቱ ሴት ናት። ሴቲቱ ልጅ የታችኛው ድዷ በሙሉ ጥርስ አብቅሏል። እናቲቱ ዘነበች በግርድና የምትሠራ ነበረች። በማርገዟ ምክንያት ከተቀጠረችበት ተባራለች። አሁን ከሁለት ልጆቿ ጋር ያለችው በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ ነው። ዘነበች ስለልጆቿ አባት ለመናገር አፍራለች። መንትያው ወንዱ ልጅ ደህና ደንቦጭ ያለ ነው። ባለጥርሷ ልጅ ግን ኮሳሳ ነች። እናቲቱ ልጅቱ ጡጦም ሆነ ምንም ለመጥባት አልቻለችም ብላለች። ልጅቱን ትናንት እንዳየናት የህክምና ዕርዳታ ከተደረገላት የመዳን ተስፋ አላት።
****************
ቅዳሜ ጥር ስምንት ቀን 1963 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ 30ኛ ዓመት ቁጥር 315 ዕትም ይበልጥ የሚፋቀሩ ባልና ሚስት ወንድ ልጅ ይወልዳሉ ሲል ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር።
ባልና ሚስት ሲፋቀሩ ወንድ ልጅ ይወልዳሉ
ከማይዋደዱ የትዳር ጓደኞች ይልቅ በደንብ የሚዋደዱት የትዳር ጓደኞች ወንድ ልጅ የመውለድ ዕድል የሚያጋጥማቸው መሆኑን እንግሊዛዊው ዶክተር ዊልያም ጄምስ ገልጠዋል። ዶክተሩ ለምርምራቸው መሠረት ያደረጉት ወታደሮች ከጦርነት መልስ ፈቃድ ተሰጥቷቸው እቤታቸው ከሚስቶቻቸው ጋር እረፍት በሚያሳልፉበት ጊዜ ብዙ ወንዶች ልጆች መውለዳቸውን በጥናት ስለደረሱበት ነው።
በጫጉላ ወራት የሚረገዘውም ልጅ አብዛኛውን ጊዜ ወንድ እንደሚሆን ዶክተሩ ተረድተዋል። በተጨማሪም ከጦርነት በፊትና በኋላ የተወለዱትን ልጆች በማወዳደር ውጤቱን አግኝተዋል። ሴቶች የወር አበባቸው ወዲያው እንደቆመ ያረገዙ እንደሆነ ወንድ ልጅ ይወልዳሉ። የወር አበባቸው ቆሞ ጥቂት ቀን እንደቆዩ ካረገዙ ደግሞ ሴት ትሆናለች የሚለውን የድሮ እምነት ዶክተሩ ይደግፋሉ።
****************
ረቡዕ መስከረም 27 ቀን 1963 ዓ.ም የወጣው የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ 13ኛ ዓመት ቁጥር 25 ዕትም ተከታዩን ማሳሰቢያ አስነብቦ ነበር።
ማሳሰቢያ
ሰው ገና ሲፈጠርና ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ትልቁ እዳ ሞት ተከትሎት መምጣቱ አይዘነጋም። በመቆምም ላይ ደግሞ መፍረስ እንዳለበት ከድሮ ይታወቃል። እንዲሁም ማግኘትም ፤ ማጣትም ፤ ኃያላንም ፤ ድኩማንም ፤ አሸናፊና ተሸናፊም ፤ አጥቂም ተጠቂም ፤ ጠቢባንም ፤ የበላይም መሆን በእግዚአብሔር እጅ እንዳለና ይህም ሁሉ በእርሱ ቸርነት እንደሚፈጸም በብዙ ይታሰባል።
- ሰው ለምን ሥራ ተፈጠረ ?
- በሕይወት ሳላ ዓለምን እንጂ አብሮ በቀሉን ሞት ለምን አያስብም ?
- ደግሞስ ቋሚ ገንዘቡ ላልሆነው (በኋላ ለሚከዳው) ዓለም ለምንድን ነው በከንቱ መነቋቆሩ ?
****************
ማክሰኞ ጥር ጥቅምት 18 ቀን 1963 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ 30ኛ አመት ቁጥር 322 ዕትም በመብረቅ ተመትታ ህይወቷ ስለለፈ እንስት ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር።
መብረቅ ሴቲቱን ገድሎ ልብሷን አቃጠለ
ዓመት ሎሚቴ ወርዶፋ የተባለች ሴት በመብረቅ ተመትታ መሞቷን የሸዋ ፖሊስ ማስታዊቂያ ክፍል ገለጠ። በሴቲቱ ላይ አደጋው የደረሰው ታህሳስ 22 ቀን 1963 ዓ.ም በሰላሌ አውራጃ በውጫሌ ወረዳ ነው። ሟችቷ አደጋው ደርሶባት እንደ ወደቀችም የለበሰችው ልብስ በላይዋ ላይ ተቃጥሏል። ከላይ በተጠቀሰውም ቀን ከባድ ዝናብ ይዘንብ እንደነበረ የማስታወቂያ ክፍሉ ከስፍራው በደረሰው ሪፖርት መሠረት አስረድቷል።
አዲስ ዘመን ጥር 6/2012
የትናየት ፈሩ