የሶማሊያ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዋና ጸሐፊ ልዩ መልዕክተኛ ኒኮላስ ሃይሶም አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ አድርጓል፡፡ የአገሪቱ መንግሥት ውሳኔውን ያሳለፈው መልዕክተኛው የሶማሊያን ሉዓላዊነት የሚዳፈር ጣልቃ ገብነት ፈፅመዋል ብሎ ባቀረበው ወቀሳ ነው፡፡ የሶማሊያ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ መልዕክተኛው ሶማሊያ ውስጥ መሥራት እንደማይችሉ አስታውቋል፡፡
ኒኮላስ ሃይሶም የቀድሞው የአልሸባብ መሪ ለነበረው ሙክታር ሮቦው አጋርነታቸውን ያሳዩ ሰልፈኞች ግድያ አሳስቦኛል ብለው ነበር። ልዩ መልዕክተኛው ባለፈው ወር መጨረሻ ለሶማሊያ የአገር ደህንነት ሚኒስቴር በፃፉት ደብዳቤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፈው የሶማሊያ ጦር በሙክታር ሮቦው እስራት፣ በሰልፈኞች ግድያና እስራት መሳተፉ እንዳሳሰባቸው ገልጸው ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሮቦው ለምን እንደታሰረና በደጋፊዎቹ ላይ የተወሰደው እርምጃ እንዲመረመር ጠይቀው ነበር፡፡
የሶማሊያ የአገር ደህንነት ሚኒስቴርም ሮቦው በቁጥጥር ስር የዋለው በአካባቢው ግጭት እንዲቀሰቀስ ተዋጊዎችንና የጦር መሳሪያ ወደ ባይዶዋ አስገብቷል ተብሎ በመጠርጠሩ እንደሆነ ገልጿል፡፡ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ኢሴ አዋድ ‹‹ሃይሶም ራሳቸውን የሶማሊያ መሪ አድርገው በመቁጠር በሶማሊያ ሉዓላዊነት ላይ ጣልቃ ገብተዋል›› በማለት ለቢቢሲ የሶማሊኛው ክፍል ተናግረዋል፡፡
የሶማሊያን ደቡብ ምዕራብ ግዛት ለማስተዳደር ሊወዳደር የነበረው የቀድሞው የአልሸባብ መስራች እና አባል ሙክታር ሮቦው በሶማሊያዋ ባይዶዋ ከተማ በቁጥጥር ሥር ውሎ በምርጫ ሳይሳተፍ መቅረቱ ይታወሳል። ይህ በእንዲህ እንዳለ አልሸባብ ሞቃዲሾ ውስጥ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥሪያ ቤት ላይ ጥቃት ፈፅሞ ሦስት ሰዎች መጎዳታቸው ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2011
አንተነህ ቸሬ