በዚህ ዕትም በርካታ ተግባራትን አከናውነው ሳለ ስለሥራዎቻቸውና አበርክቷቸው ግን ብዙም ያልተነገረላቸውን የብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስን ታሪክ በጥቂቱ እንመለከታለን።
መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ መጋቢት 17 ቀን 1891 ዓ.ም ተወለደ። አባቱ አለቃ ወልደ ቂርቆስ አልታመን በደብረ ሊባኖስና በእንጦጦ ማርያም የቤተልሔምን መዝገበ ድጓ ሲያስተምሩ የነበሩና በዜማ መምህርነት የታወቁ ሰው ነበሩ። የአባታቸው አጎት አለቃ ገብረ ክርስቶስ የብሉይና የሐዲስ ሊቅ እንዲሁምና የቅኔ መምህር የነበሩና በንጉሥ ኃይለ መለኮት፣ በአጼ ዮሐንስ ፬ኛ እና በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ቤተ መንግሥት እጅግ የተከበሩ ሰው ነበሩ። የአባቱና የአጎቱ ሊቅነት መርስዔ ኀዘንም የእነርሱን ፈለግ ተከትሎ እንዲጓዝ አስተዋፅኦው ቀላል አልነበረም።
ሕፃኑ መርስዔ ኀዘን አራት ዓመት ሲሞላው ፊደል መቁጠር ጀመረ። በ1896 ዓ.ም ወደ እንጦጦ መጥቶ ንባብ ተማረና ዳዊት ደገመ። ቀጥሎም የዜማ ትምህርት በመጀመር ጾመ ድጓና ድጓን አጠናቀቀ። ከ1901 እስከ 1904 ዓ.ም በጅሩና በአዲስ አበባ ከታላላቅ የዘመኑ ሊቃውንት እግር ስር ተቀምጦ የቅኔ ትምህርት ተማረ።
በ1906 ዓ.ም በቀኛዝማች ናቄ ዘንድ የጸሐፊነት ሥራ ተቀጥሮ ለአንድ ዓመት ከአራት ወራት ያህል ካገለገለ በኋላ በአባቱ ወዳጅ በአቶ ሕለተ ወርቅ እሸቴ ምክር የጸሐፊነቱን ሥራ ትቶ በነሐሴ ወር 1907 ዓ. ም ወደ ትምህርት ገበታው ተመለሰ። ከዚህ በኋላ የመጻሕፍተ ሐዲሳትንና የዮሐንስ አፈ ወርቅ ትርጓሜዎችን ከታላላቅ መምህራን ተማረ።
በ1912 ዓ.ም በስመ ጥሩው ሊቅ በአለቃ ገብረ መድኅን አማካኝነት የመንግሥት ሥራ ጀመረ። ሥራውም የትርጓሜ ሥራ መሥራትና የትርጓሜውን ንባብ ከነትርጉሙ ለኅትመት ማዘጋጀት ነበር። በወቅቱም ‹‹አረጋዊ መንፈሳዊ›› ከተባለውና አልጋወራሽ ተፈሪ መኮንን (በኋላ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ) በ1920 ዓ.ም ድሬዳዋ ላይ ካሳተሙት ሥራ በተጨማሪ ሌሎችን የትርጓሜ ሥራዎችንም አዘጋጅቶ አቅርቧል።
በቀጣዩ ዓመት ደግሞ እንግሊዝኛ ቋንቋ ለመማር ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ገባ። ይሁን እንጂ ከሦስት ወር በኋላም የትርጓሜ ሥራውን ብቻ እንዲሠራ ስለታዘዘ የቋንቋ ትምህርቱን አቋረጠ። የቋንቋ ትምህርቱ ስለመቋረጡ ‹‹ትዝታዬ ስለራሴ የማስታውሰው›› በሚል ርዕስ በ2005 ዓ. ም ላይ ታትሞ በወጣው የብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ የግለ ታሪክ መጽሐፈ ላይ እንደሚከተለው ተገልጿል።
‹‹ … የቋንቋ ትምህርት መጀመሬንም እንዳይሰሙብኝ ለማድረግ ተጣጣርሁ። ዳሩ ግን ተደብቆ የሚቀር ነገር ስለሌለ ወሬውን ሰምተው ጠሩኝና እያዘኑ ክፉኛ ገሠጹኝ። ‹ዳግመኛ ወደዚያ ስፍራ እንዳትመለስ› ብለውም አስጠነቀቁኝ። እንግዲህ የተፈሪ መኰንን ተማሪ ቤት እስከተከፈተ ድረስ የቋንቋ ትምህርቴን አቋርጬ ተቀመጥሁ። ጌታ አለቃ ገብረ መድኅን ይህን ማድረጋቸው በእርሳቸው አስተያየት እኔን ለመጥቀም እንጂ ለክፋት እንዳላደረጉት ሕሊናዬ ስላወቀ አላዘንሁባቸውም … ››
ታኅሣሥ 23 ቀን 1917 ዓ.ም በአልጋወራሽ ተፈሪ መኮንን አማካኝነት ‹‹ብርሃንና ሰላም›› የተባለ ጋዜጣ ሲመሰረት መርስዔ ኀዘን ወደ ጋዜጠኛነት ተዛውሮ በዋና ጸሐፊነት መሥራት ጀመረ። ከአራት ወር በኋላም ሚያዝያ 19 ቀን 1917 ዓ.ም የተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ተመርቆ ሲከፈት የግዕዝና የአማርኛ አስተማሪ ሆኖ ወደ ትምህርት ቤቱ ተዛወረ። በዚህ ጊዜ ያሰናዳት ‹‹ትምሕርተ ሕፃናት›› የተባለች መጽሐፍ ግንቦት 1 ቀን 1917 ዓ. ም ታትማ ወጣች፤የግብረ ገብ ትምህርት ማስተማሪያም ሆነች። በዚህ ጊዜ መርስዔ ኀዘን ቀደም ሲል አቋርጦት የነበረውን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ለመማር በትጋት ጥረት ማድረግ ጀመረ።
ከአንድ ዓመት በኋላ ጽፎ ያቀረበው ‹‹በአዲስ ሥርዓት የተሰናዳ የአማርኛ ሰዋስው›› የተሰኘው ሥራ በደብተር እየተገለበጠ የተማሪዎች መማሪያ ሆኖ በአገልግሎት ላይ ዋለ። ይህ ሰዋሰው በኋላ ከፋሺስት ኢጣሊያ ጦር መባረር በኋላ በ1935 ዓ.ም ታትሞ የወጣው ነው። ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል ለኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች መደበኛ የሰዋሰው ማስተማሪያ ሆኖ አገልግሏል።
ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ከሕክምና ሙያቸው በተጨማሪ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ‹‹የዓለም ጂኦግራፊ›› መጽሐፍ በአማርኛ ቋንቋ ጽፈው ነበር። ሐኪም ወርቅነህ መጽሐፉን እንደገና ባረሙበትና ለሕትመት ባዘጋጁበት ወቅት መርስዔ ኀዘን ከፍተኛ ድጋፍ አድርጎላቸዋል። ሐኪም ወርቅነህም በ1920 ዓ.ም በታተመው በዚሁ መጽሐፋቸው መቅድም ላይ ‹‹ይህንም ለማረም ምሁር የሆነ ወዳጄ አቶ መርስዔ ኀዘን በትዕግሥትና በልበ ፈቃድ ከእኔ ጋር በማረም ረዳኝ፤ ቀጥሎ መጽሐፉ ሲታተም ግድፈቱን እያረመ አሳተመልኝ፤ ይህን የመሰለ ዕርዳታ ባላገኝ ኖሮ ይህ የጅኦግራፊ ትርጉም ወደ ፍጻሜ ባልደረሰም ነበር›› በማለት ምስጋና አቅርበውለታል።
በ1922 ዓ.ም ወደ ጂግጂጋ በመዛወር በዚያ ለተከፈተው ራስ መኮንን ትምህርት ቤት ዋና ሹም በመሆን ለአምስት ዓመታት አገልግሏል። ከትምህርት ቤቱ ዋና ሹምነት በተጨማሪም በወሰን አከላለል ሥራ ላይ ኃላፊነት ተሰጥቶት ሠርቷል። መርስዔ ኀዘን በታኅሣሥ ወር 1924 ዓ.ም በተጀመረው የኢትዮጵያና የእንግሊዝ ሱማሌላንድ የወሰን አከላለል ሥራ እስከተጠናቀቀበት እስከ የካቲት ወር 1927 ዓ.ም ድረስ በዋና ጸሐፊነት አገልግሏል።
ወራሪው የፋሺስት ኢጣልያ ጦር ኦጋዴን ውስጥ ወልወል በተባለው ስፍራ ላይ ኅዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም በኢትዮጵያውያን ላይ አደጋ ባደረሱበት ጊዜ መርስዔ ኀዘን በስፍራው ተገኝቶ አደጋውን በመከላከል ሥራው ላይ ተሳትፏል። በፋሺስት ኢጣሊያ የወረራ ዓመታት በጅሩ፣ በዓድአና በሌሎች አካባቢዎች እየተዘዋወረ በነፃነት ተጋድሎው ላይ ተሳትፎ አድርጓል።
መርስዔ ኀዘን ወልደቂርቆስ ወራሪው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ በተለያዩ መንግሥታዊ ኃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል። ከእነዚህም መካከል፡-
1. የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ (1933-36 ዓ.ም)
2. የጋዜጣና ማስታወቂያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር (1936 ዓ.ም)
3. የታሪክና የቤተ መንግሥት ዜና ማስናጃ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር (1936-46 ዓ.ም)
4. የፍርድ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር (1941-50 ዓ.ም)
5. የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ዓቃቤ ጉባዔ (1950-54 ዓ.ም)
6. የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባልና የሕግ ኮሚቴ ሊቀ መንበር (1950-63 ዓ.ም)
7. የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት (በ1954፣ በ1956 እና 1960-61 ዓ.ም)
8. የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት (1960 ዓ.ም)
9. የታሪካዊ ቅርሶች አስተዳደር አማካሪ (1963-66 ዓ.ም) ተጠቃሾች ናቸው።
በ1936 ዓ.ም ደግሞ የ‹‹ብላታ››ነት ማዕረግን አግኝተዋል።
ከላይ ከተጠቀሱት ኃላፊነቶቻቸው በተጨማሪ (በመደበኛ ሥራቸው ላይ ደርበው) የአንጋፋው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሹም ሆነው ለ14 ዓመታት፤ የሕዝብ ጤና ሚኒስቴር ተጠባባቂ ሹም ሆነው ደግሞ ለአንድ ዓመት ሠርተዋል። እንዲሁም በብዙ ድርጅቶች የሥራ አስፈፀሚ ቦርዶችም በአባልነትና በሊቀ መንበርነት አገልግለዋል። ከእነዚህም መካከል ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸው።
- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ቦርድ ሊቀ መንበር (1946-54 ዓ.ም)
- የትምህርትና የሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ቦርድ አባል (1940-54 ዓ.ም)
- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ቦርድ አባልና ምክትል ሊቀ መንበር (1942-66 ዓ.ም)
- የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወ. ወ. ክ. ማ) ቦርድ አባልና ምክትል ፕሬዚዳንት (1941-1966 ዓ.ም)
ከብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደቂርቆስ ሥራዎች ሁሉ ጎላ ብለው የሚጠቀሱላቸው የድርሰት ሥራዎቻቸው ናቸው። በተርጓሚነት፣ በአዘጋጅነት እና በደራሲነት ባገለገሉበት ጊዜ ከ35 በላይ የሚሆኑ መጽሐፍትን ለሕትመት እንዲበቁ አድርገዋል። ከድርሰት ሥራዎቻቸው (የትርጉሞቹን ጨምሮ) መካከል፡-
• ትምህርተ ሕፃናት
• የአማርኛ ሰዋሰው
• የአማርኛ ሰዋሰው መክፈቻ
• የአማርኛ ሰዋሰው አንደኛ ክፍል
• የአማርኛ ሰዋሰው ሁለተኛ ክፍል
• የትእምርተ መንግሥት ታሪክ
• ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጎንደርን የመጎብኘታቸው ታሪክ
• ዐውደ መዋዕል
• የኢትዮጵያ መዝገበ ዕለታት
• የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፣ የዘመን ታሪክ ትዝታዬ፣ ካየሁትና ከማስታውሰው (1896-1922)
• ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ (1922-1927)
• የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት
• የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዕረፍት መታሰቢያ
• ጥበብን መፈለግ ፣ ቅን ጥበብ በቅን አማርኛ 1ኛ መጽሐፍ
• ጥበብን መፈለግ ፣ ቅን ጥበብ በቅን አማርኛ 2ኛ መጽሐፍ
• ጥበብን መፈለግ ፣ ቅን ጥበብ በቅን አማርኛ 3ኛ መጽሐፍ
• ፍሬ ከናፍር
• ሔሮዶቱስ ፡- 1ኛ መጽሐፍ – የጥንት ታሪክ ሔሮዶቱስ እንደጻፈው
• ሔሮዶቱስ ፡- 2ኛ መጽሐፍ – የጥንት ታሪክ ሔሮዶቱስ እንደጻፈው
• ሔሮዶቱስ ፡- 3ኛ መጽሐፍ – የጥንት ታሪክ ሔሮዶቱስ እንደጻፈው … የሚሉት ይገኙበታል።
በብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደቂርቆስ ከተዘጋጁ ሐይማኖታዊ መጻሕፍት መካከል ደግሞ ‹‹አረጋዊ መንፈሳዊ››፣ ‹‹የቤተ ክርስቲያን ጸሎት››፣ ‹‹የቤተ ክርስቲያን ዜና››፣ ‹‹መጽሐፈ ቅዳሴ በግዕዝና በአማርኛ››፣ ‹‹ሢመተ ሊቀ ጳጳሳት ኢትዮጵያዊ››፣ ‹‹የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ›› እና ‹‹ቅዳሴ በእንግሊዝኛ (ትርጉም)›› ይጠቀሳሉ። ከእነዚህ ሥራዎቻቸው በተጨማሪም ከስድስት በላይ ያልታተሙ ሥራዎች እንዳሏቸው ታሪካቸው ያስረዳል።
በሐይማኖታዊ ጉዳዮችና ጽሑፎች ላይ የጎላ ተሳትፎ የነበራቸው ብላታ መርስዔ ኀዘን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ፓትርያርክ እንድትሾም በኢትዮጵያና በእስክንድርያ አብያተ ክርስቲያናት መካከል በሚደረገው ድርድር ተካፋይ እንዲሆኑ ተመርጠው እስከድርድሩ ፍጻሜና የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ የአቡነ ባስልዮስ ሢመት እስከሚፈጸም ድረስ ተሳታፊ ሆነው አገልግለዋል። ከዚህ በተጨማሪም፣ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ አራሚ ኮሚቴ እንዲሁም በ1942 ዓ.ም የወጣው መጽሐፈ ቅዳሴ አዘጋጅ ሆነው ሠርተዋል።
መጋቢት 17 ቀን 1946 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትዕዛዝ የፍትሐ ነገሥት ኮሚሲዮን (የኮዲፊኬሽን ኮሚሸን) ሲቋቋም የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ሆነው የተሾሙት የፍርድ ምክትል ሚኒስትሩ ብላታ መርስዔ ኀዘን ነበሩ። የኮሚሽኑ አባላት ሦስት የታወቁ የአውሮፓ የሕግ ፕሮፌሰሮችና የካበተ የባህልና የሕግ ዕውቀት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ነበሩ። የኮሚሽኑ ዓላማ በፍትሐ ነገሥትና በኢትዮጵያ የነበሩትን ልማዶችና ባህሎችን መሠረት በማድረግ የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔር፣ የንግድና የባሕር ሕጎችን ማዘጋጀት ነበር። የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በ1949 ዓ.ም፣ የፍትሐ ብሔር ሕግ በ1952 ዓ.ም እንዲሁም የንግድና የባሕር ሕጎች ደግሞ በ1953 ዓ.ም በፓርላማ ተቀባይነትን አግኝተውና በንጉሠ ነገሥቱ ፀጽቀው ሕግ ሆነው ወጥተዋል። በእነዚህ ሕጎች ዝግጅት ሂደት ውስጥ የብላታ መርስዔ ኀዘን አበርክቶ ትልቅ ነበር። ከእነዚህ ሕግጋት መካከል ብዙዎቹ አሁንም ድረስ እያገለገሉ ይገኛሉ።
በ1960 ዓ.ም. የፍትሐ ነገሥት ንባብና ትርጓሜ የሚሠራ ኮሚቴ በተቋቋመበት ወቅት የኮሚቴው ሰብሳቢ የነበሩት ብላታ መርስዔ ኀዘን ሲሆኑ፤ የፍትሐ ነገሥት ንባብና ትርጓሜ ሥራው በ1962 ዓ.ም ተጠናቆ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ታትሞ ወጥቷል። ከ1964 እስከ 1966 ዓ.ም ደግሞ የአማርኛ ቋንቋን ማዳበርና የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ እንዲስፋፋ ማበረታታትን ዓላማው አድርጎ የተቋቋመው የአማርኛ መርሐ ልሳን (አካዳሚ) አባል ሆነው ሠርተዋል።
በርካታ የአማርኛ ቋንቋ ባለሙያዎች ‹‹ብላታ መርስዔ ኀዘን አንዱ የአማርኛ ቋንቋ አባት ተብለው ቢወደሱ ማጋነን አይሆንም›› ብለው ይመሰክሩላቸዋል። ይህ የተባለበት ምክንያትም የአማርኛ ሰዋሰውን አስመልክቶ ባደረጓቸው ጥልቅ ምርምሮች እና በተቀናጀ መልክ የተዘጋጁ የአማርኛ ሰዋሰው መማሪያ መጸሐፍትን በመጻፋቸው ነው። የአማርኛን ቋንቋ ከዘመናዊ እና ከኪነታዊ አነጋገር በማስማማት ያሳደጉ ታላቅ ባለሙያ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል።
ብላታ መርስዔ ኀዘን በተለይ በአማርኛ ስነ-ጽሑፍ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋፅኦ በ1964 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ሽልማትን አሸንፈዋል።
አንጋፋው የታሪክና የቋንቋ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ስለብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ እንዲህ በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል …
‹‹ … ክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ለኢትዮጵያ የሰጡትን ልባዊ አገልግሎትና እሳቸውንም በአካል የሚያውቅ ሰው በየምእት ዓመት አንድ ጊዜ የሚታዩ የዕውቀትና የጥበብ ሰዎች ካሉ ክቡርነታቸው አንዱ መሆናቸውን አይጠራጠርም።››
ጡረታ እስከወጡበት እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ በአጠቃላይ ለ50 ዓመታት ያህል አገራቸውን በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉት አንጋፋው ባለሙያና የአገር ባለውለታ ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ጥቅምት 19 ቀን 1971 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ሥርዓተ ቀብራቸው ጥቅምት 21 ቀን 1971 ዓ.ም ተፈጽሟል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22/2012
አንተነህ ቸሬ