በመንግሥትም ይሁን በግል ተቋማት አንድ ሰራተኛ ከስራው ቦታ ወደ ሌላ አካባቢ አልያም ቢሮ ተንቀሳቅሶ እንዲሰራ ሲፈለግ የትራንስፖርት፣ የምግብና የማደሪያ ወጪውን ሊሸፍንለት የሚችል የውሎ አበል ይታሰብለታል። ይህ አሰራር በተለይ በግል ተቋማትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች አካባቢ የተሻለ ገጽታ ቢኖረውም ወደ መንግስት ሰራተኞች ስንመጣ ግን አንዳንድ ጊዜ ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ወይ የሚያሰኝ ሆኖ እናገኘዋለን።
ከሐምሌ 1ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ስራ ላይ የዋለው የመንግስት ሠራተኞች የቀን ውሎ አበል መመሪያ እንደሚያመለክተው የመንግሥት ሠራተኛው በየትኛውም ክልል ሄዶ ቢሰራ ከፍተኛ ደመወዝ አለው የሚባለው 225 ብር የሚታሰብለት ሲሆን፤ አነስተኛ ደመወዝ ተከፋይ ነው የሚባለው ደግሞ በቀን የሚያገኘው 111 ብር ነው።
ይህ ደግሞ አሁን በምናየው የገበያ ሁኔታ ምን ተበልቶ የት ታድሮ እንዲሁም በየትኛው የትራንስፖርት አማራጭ ተንቀሳቅሶ ነው ሰው ስራ የሚሰራው የሚለውን የሚያጠያይቅ ብሎም ‹‹ስራ እንዲሰራ ነው እንዳይሰራ የሚፈለገው›› የሚለውን ጥያቄ የሚያስነሳ በመሆኑ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ትኩረት ሰጥተው ሊያዩት ይገባል።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የትኛውም አካባቢ ላይ አልጋ ከ 200 ብር በታች፣ ከሽሮ አቅም ከ 70 እና 80 ብር ባነሰ ዋጋ ማግኘት ዘበት በሆነበት ወቅት አንድ ሰው ለመስክ ስራ በ 225ብር እና ከዛ በታች ይሂድ ማለት እንደ እውነቱ ከሆነ ስራው እንዳይሰራ መፈለግ፣ ሰውንም ለተጨማሪ ወጪ መዳረግ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ሊያስብበት ይገባል።
በተለይም አንዳንድ መስሪያ ቤቶች የስራ ኃላፊነታቸው ከባድ ሆኖ ለሠራተኞቻቸው የሚሰጡት ትኩረት ግን አናሳ ሆኖ ይስተዋላል። ይህ ዘመኑን ታሳቢ ያላደረገ የውሎ አበል ክፍያ ስራ እንዲበደል ሰዎችም በስራቸው ደስተኛ ከመሆን ይልቅ እንዲማረሩና ራሳቸውንና ቤታቸውን እየበደሉ ከኪሳቸው አውጥተው እየተሳፈሩ፣ እየተመገቡና ሌሎች ወጪያቸውንም እየሸፈኑ እንዲሰሩ አስገድዷል።
በመሆኑም ይህንን መሰል መመሪያ ጊዜን ወቅታዊና ነባራዊ እድገትንና ገበያን ታሳቢ እያደረገ በየጊዜው መሻሻል ይኖርበታል። ማሻሻል ባልተቻለና የዛሬ ስምንት ዓመት በነበረ መመሪያ ዛሬም ይሰራ የሚባል ከሆነ ከጥቅሙ ጉዳቱ ማመዘኑ የማይቀር ነው።
በአጠቃላይ በተለይም የመስክ ስራ የሚበዛባቸው ሠራተኞች በወር ወይም እንደ አስፈላጊነቱ በተንቀሳቀሱ ቁጥር የሚከፈላቸው የትራንስፖርት፣ የምግብና የመኝታ አበል የዘመኑን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ከግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ፤ ‹ከወረቱ ስንቁ ላቀ› እየሆነ ብዙዎችንም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየዳረገ በመሆኑ እንደገና በማየት መሻሻል ያለበትን በማሻሻል መቅረት ያለበትንም ኋላ ቀር አሰራር በዘመናዊና ወቅቱ በሚጠይቀው መልኩ በመቃኘት መስራት ያስፈልጋል።
በአሁኑ ወቅት አይደለም ወደ ክልል መውጣት፤ አዲስ አበባ ውስጥ ባሉ መስሪያ ቤቶች ተንቀሳቅሶ ስራውን ማከናወን ያለበት የመንግስት ሠራተኛ በቀን በአማካይ ለትራንስፖርት ብቻ ቢያንስ 20 ብር ያስፈልጋል። ምናልባት ስራው ካልተጠናቀቀ እዛው አካባቢ ምሳም መብላት ሊኖርበት ይችላል፤ ሆኖም አሁን እንደሚታየው በአንዳንድ መስሪያ ቤቶች ለአንድ ሰራተኛ ከተማ ውስጥ የሚንቀሳቀስ ከሆነ በወር ለትራንስፖርት የሚከፈለው 75 ብር ነው።
ይህ ብር ደግሞ ለምን ልትበቃ እንደምትችል በእውነት ከሆነ ከፋዩም አካል እርግጠኛ ሊሆን አይችልም። ስለሆነም የመንግሥትን ገንዘብ ከብክነትና ከአላስፈላጊ ወጪ መከላከል በጀትንም ቆጥቦ በተገቢው ሁኔታ መጠቀም የሚያስመሰግን ቢሆንም፤ ሰዎችን ለስራ ልኮ ማንገላታትና ለተጨማሪ ወጪ መዳረግ ደግሞ ህግም ህሊናም የማይፈቅደው ስራ ነው። ስለሆነም ከሐምሌ 1 ቀን 2004 ጀምሮ ስራ ላይ ያለው የመንግሥት ሠራተኛ የውሎ አበል መመሪያ ሊሻሻል ይገባል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2012