የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ አገራቸው ታይዋንን ወደ ቻይና ለመቀላቀል የኃይል አማራጭ ልትጠቀም እንደምትችልና ታይዋን የቻይና አካል መሆኗ ፈፅሞ የማይካድ እውነታ ነው ብለው መናገራቸው የቀጣናውን ሰላም አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል፡፡ፕሬዚዳንቱ ሰሞኑን ከቤጂንግ ለታይዋን ዜጎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹ሁለት ቻይና፣ አንድ ቻይና-አንድ ታይዋን የሚሉና የታይዋንን ነፃነት እንደግፋለን እያሉ የሚያሴሩ አገራትን ጣልቃ ገብነት አምርረን እንቃወማለን፡፡
የተገንጣይ ቡድኖችን እንቅስቃሴዎች የመደምሰስ ስኬታማ ልምድና ታሪክ ያለን በመሆኑ ታይዋን የቻይና ሕጋዊ ግዛት አካል መሆኗን መካድ አይቻልም›› ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቻይና ታይዋንን ወደግዛቷ ለመቀላቀል ሁሉንም ዓይነት አማራጮችን ልትጠቀም እንደምትችልና የቻይናን እርምጃ ለማስተጓጎል በሚሞክሩ አካላት ላይ እርምጃ እንደምትወስድም አስጠንቅቀዋል፡፡
የፕሬዚዳንቱ ንግግር የተሰማው የታይዋን ፕሬዚዳንት ሳይ ኢንግ-ወን የታይዋን ሕዝብ ራስ-ገዝ ሆኖ መቀጠል እንደሚፈልግና ከቻይና ጋር ያላቸው አለመግባባት በሰላማዊ ድርድር ብቻ እንዲፈታ ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ፕሬዚዳንቷ በ2019 የአዲስ ዓመት መልዕክታቸው ‹‹ቻይና የ23 ሚሊዮን ታይዋ ናውያንን በነፃነትና በዴሞክራሲ የመኖር መብትና ፍላጎት ማክበር ይገባታል፡፡ ልዩነቶቻችን መፍታት የሚገባው በሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው›› ብለዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ቻይና በታይዋን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የምታደርገው ጣልቃ ገብነት የታይዋን የወቅቱ ፈታኝ አጀንዳ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
በናንያንግ ቴክኖሎጂካል ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ጥናት ተመራማሪ የሆኑት ግርሃም ኦንግ-ዌብ፣ የፕሬዚዳንት ሺ የሰሞኑ ማስጠንቀቂያ ላለፉት 40 ዓመታት የቻይና መሪዎች ሲናገሩት ከነበረው የተለየ እንዳልሆነና የቻይና መንግሥት ውህደቱን ማሳካት የሚፈልግበት የራሱ የሆነ የጊዜ ሰሌዳ ሊኖረው እንደሚችል ለአልጀዚራ አስረድተዋል፡፡
የቻይና መንግሥት ፕሬዚዳንት ሳይ ኢንግ-ወን ሥልጣን ከያዙበት ከ2016 ጀምሮ አገራት ከታይዋን ጋር ያላቸውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲያቋርጡና አየር መንገዶችም ታይዋን የቻይና አካል እንደሆነች አድርገው በረራቸውን እንዲያከናውኑ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የቻይና መንግሥት ሳይ ኢንግ-ወን የታይዋንን ሙሉ ነፃነት ይጠይቃሉ ብሎ ቢሰጋም ፕሬዚዳንቷ ግን ሁኔታው እስካሁን በነበረበት እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳላቸው ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ ቤጂንግም በተደጋጋሚ ጊዜያት የጦር አውሮ ፕላኖችንና መርከቦችን ወደ ታይዋን በመላክ ስታስፈራራ ቆይታለች፡፡
ይሁን እንጂ ቻይና በታይዋን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳልገባች በተደጋጋሚ ስትገልፅ ቆይታለች፡፡ ቻይና ታይዋንን እንደ ሕጋዊ የግዛት አካሏ ትቆጥራታለች፡፡ ደሴቲቱን ወደቻይና ለመቀላቀልም ወታደራዊ አማራጭን ያካተተ የመፍትሄ እርምጃ እንደምትጠቀምም ስትገልፅ ቆይታለች፡፡ ከታይዋን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሌሎች አገራት ግንኙነታቸውን እንዲያቋርጡ በየጊዜው ታስጠነቅቃለች፡፡ እንዲያውም ታይዋን ትንኮሳ እንደምትፈፅምባት ስሞታ ታሰማለች፡፡ በቻይና የታይዋን ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሊው ጄይ ‹‹ታይዋን ባለፈው ዓመት ሆን ብላ የፈፀመችውን ትንኮሳ በትዕግስት አልፈነዋል፡፡ የታይዋንን ጉዳይ በተመለከተ መጪው ጊዜ ቀላል ይሆናል ተብሎ ባይታሰብም የሚያጋጥሙንን መሰናክሎች ለማለፍ የሚያስችል አቅም አለን›› በማለት ተናግረዋል፡፡
የዴሞክራሲ ሥርዓት የሰፈነባት እንደሆነች የሚነገርላት ታይዋን ግን በቻይና አስተዳደር ስር የመሆን ፍላጎት የላትም፡፡ እ.አ.አ በ2020 በታይዋን የሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ገና ከወዲሁ የታይዋንንም ሆነ የቻይናን ፖለቲከኞች ቀልብ ስቧል፡፡ ባለፈው ኅዳር ወር በተካሄደ አካባቢያዊ ምርጫ የታይዋንን ነፃ አገርነትና ሉዓላዊነት የሚደግፈው የፕሬዚዳንት ሳይ ኢንግ-ወን ‹‹ዴሞክራቲክ ፕሮግረሲቭ ፓርቲ (Democratic Progressive Party)›› የቻይና ወዳጅ እንደሆነ በሚነገርለት ‹‹ኩዎሚን ታንግ (Kuomintang)›› ፓርቲ ብዙ ድምፅ አጥቷል፡፡
ግርሃም ኦንግ-ዌብ፣ ቀጣዩ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የቻይናንና የታይዋንን ግንኙነት በመወሰን ረገድ የራሱ የሆነ ሚና እንደሚኖረው ይገልፃሉ፡፡ ‹‹በምርጫው የቻይና መንግሥት ታይዋን ውስጥ ሥልጣን እንዲይዝ የሚፈልገውን አካል ለሥልጣን ለማብቃት ጥረት ሊያደርግ ይችላል ተብሎ ይገመታል›› ብለዋል፡፡
የታይዋን ፕሬዚዳንት ሳይ ኢንግ-ወን የፕሬዚዳንት ሺ ዢን-ፒንግን ጥሪ እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹በታይዋንና በቻይና መካከል የሚካሄዱ ድርድሮች በሁለት መንግሥታት መካከል እንደሚካሄዱ ድርድሮች እንጂ በአንድ መንግሥት ስር ባሉ ሁለት የአስተዳደር ሥርዓቶች መካከል የሚደረጉ ግንኙነቶች መሆን የለባቸውም፤ቻይና የታይዋን ዜጎችን መብትና ፍላጎት ልታከብር ይገባል›› ብለዋል፡፡
እ.አ.አ ከ1945 እስከ 1949 ድረስ በተካሄደው የቻይና የእርስ በርስ ጦርነት የኮሚዩኒስት ጦር ቻይናን ከተቆጣጠረ በኋላ ከቻይና ሸሽተው በሄዱ ብሔርተኞች የተመሰረተው የታይዋን ራስ ገዝ አስተዳደር፣ ከቻይና ጋር የንግድና የባሕል ግንኙነት ቢኖረውም እስካሁን ድረስ ከቻይና ጋር ያለውን አለመግባባት ያስቆመ የሰላም ስምምነት አልተፈራረመም፡፡
እ.አ.አ በ2016 ሳይ ኢንግ-ወን የታይዋን የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ሆነው ሥልጣን ከያዙ ወዲህ በቻይናና በታይዋን መካከል ያለው ግንኙነት ከድጡ ወደ ማጡ ሆኗል፡፡ በበዓለ ሲታቸው ዕለት ያደረጉት ንግግር ቻይና ከደሴቲቱ ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታቋርጥ ምክንያት ሆነ፡፡ በታኅሣሥ 2016 ደግሞ አወዛጋቢው ሰው ዶናልድ ትራምፕ ለፕሬዚዳንት ሳይ ኢንግ-ወን ስልክ ደውለው ተነጋገሩ፡፡ ይህም አሜሪካ ለዓመታት በታይዋን ላይ ስትከተለው የቆየችውን ዲፕሎማሲያዊ ፖሊሲ የለወጠ ነበር፡፡
ይባስ ብሎም የትራምፕ አስተዳደር አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነት ከታይዋን ጋር ተፈራረመ፡፡ ይህ የአሜሪካ ድርጊትም ቤጂንግን ክፉኛ አስቆጥቷል፡፡ ባለፈው መጋቢት ወር ደግሞ አሜሪካ ከታይዋን ጋር ያላትን ግንኙነት የሚያጠናክር ሕግ አፅድቃለች፡፡ ታይዋን ሕጋዊ የግዛቴ አካል ናት የምትለው የአሜሪካ ባላንጣ ቻይና ደግሞ የትራምፕ አስተዳደር እርምጃዎች የአሜሪካንና የቻይናን ግንኙነት የሚጎዱ አደገኛ ውሳኔዎች ናቸው በማለት ተቃውሞዋን አሰምታ ነበር፡፡
እ.አ.አ በጥር 1979 ታይዋን ከቻይና ጋር እንድትዋሃድና በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ወታደራዊ ፍጥጫ እንዲያበቃ ቻይና ጥሪ አቅርባ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሺ ከ40 ዓመታት በኋላ ለታይዋን ዜጎች ያስተላለፉት መልዕክት አንዳንዶች የተለመደ ነው ቢሉም ሌሎች ደግሞ ቻይና አሁን በዓለም ፖለቲካ ላይ ካላት ተፅዕኖ አንፃር ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችልና በዚህም የምስራቅ እስያ ቀጣና ሰላም አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ስጋታቸውን እየገለፁ ይገኛሉ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2011
አንተነህ ቸሬ