ጣርማበር/ ደብረብርሃን:- አንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር የሚፈጀው የጣርማበር ወገሬ ኮንክሪት አስፓልት መንገድ ስራ የመንዝ አካባቢ ህዝብ የረጅም ጊዜ የልማት ጥያቄን መመለስ የሚያስችል ፕሮጀክት መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ገለፁ።
የመንገድ ፕሮጀክቱን ሥራ የማስጀመር ሥነሥርዓት በመንዝ ሞላሌ በትናንትናው እለት በተካሄደበት ወቅት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የአካባቢውን ህዝብ የረጅም ጊዜ የመንገድ ልማት ጥያቄ ለመመለስ ከዚህ በፊት የነበረው የጠጠር መንገድ ወደ አስፓልት ኮንክሪት ሲቀየር አርሶ አደሩ ምርቶቹን በቀላሉ ወደገበያ እንዲያወጣ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሯ የመንገድ ግንባታው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ፣ የአካባቢው አስተዳደሮችና የግንባታው ሰራተኞች ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ገልፀው፤ የፕሮጀክቱ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ማህበረሰቡ ከወሰን ማስከበር ጀምሮ እስከ ግንባታው ሥራ ፍፃሜ ቅንነት በተሞላበት መልኩ መሳተፍ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ወጪው አንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ፣ የመንገዱ ግንባታ ሙሉ ወጭም በኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚሸፈን፣ ግንባታውን የሚያከናውነው የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ መሆኑንና የቁጥጥር ሥራውን ደግሞ ከላሲክ ኮንሰልቲንግ የተባለ ሀገር በቀል ድርጅት እንደያሚከናውን ገልጸዋል፡፡
እንደ ኢንጅነሩ ገለጻ የመንገዱ ሥራ ሲጠናቀቅ ታሪካቸው በሚገባ ያልታወቁት እንደ እመጓ ዑራኤል፣ ጓሳ፣ ዘብር ገብርኤልና አርባሀራ የመሳሰሉት ሃይማኖታዊ ቦታዎችን ለመጎብኘት አመች ይሆናል፡፡ የአካባቢው የእንስሳት ሀብትና የግብርና ውጤቶች ለማዕከላዊና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ አጋዥ ይሆናል፡፡
ከአንድ ወር በፊት የአካባቢው ሽማግሌዎች ስለመንገድ ግንባታው ከመንግስት ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ያስታወሱት ኢንጅነሩ፤ የአካባቢው ነዋሪዎች በወቅቱ የመንገድ ግንባታው ስለመጀመሩ ስጋት አድሮባቸው እንደነበረ ገልፀው፤ አሁን ግን ግንባታው እውን በመሆኑ ማህበረሰቡ ፊቱን ወደ ግል ሥራውና ወደ ልማቱ ማዞር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መከላከያ ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍሰሀ ወልደሰንበት በበኩላቸው ግንባታውን የሚያካሂደው የመከላከያ ኮንስትራከሽን ኢንተርፕራይዝ አስቸጋሪ መልክዓ ምድር ያላቸውን የመንገድ ግንባታዎች የመከወን ልምድ ያለው በመሆኑ ግንባታውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጨረስ ዝግጅት ማድረጉንና በመንገድ ሥራው ለአካባቢው ማህበረሰብ ቅድሚያ የስራ እድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል፡፡
የጣርማበር-መለያ፣ ሰፌድ ሜዳ-መለያ፣ ሞላሌና ወገሬ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ 118 ኪሎሜትር እንደሚሸፍንና በሶስት ዓመት ውስጥ እንዲጠናቀቅ እቅድ መያዙ ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2011
በጌትነት ተስፋማርያም