እኔ ቁልቁል እየጎተተን ላለው ድህነትም ሆነ ያስተሳሰብ መንጠፍ ዋነኛው ችግር መተባበር ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ። መፍትሄው ደግሞ ያለምንም ማመንታት በጋራ በመሆን ችግራችንን መፍታት ነው። ማለትም መተባበር። ዛሬ ላይ ወደ ጥልቁ ጉድጓድ ሊጥሉን እያንገዳገዱን ያሉት ድህነት፣ የፖለቲካ ቀውስ፣ ጎጠኝነት የሚሸነፉት በመደማመጥ እና በብልሀት ነው።
ለዚህ ደግሞ ቅድሚያ የመተባበር ፍላጎት ሊኖረን ይገባል። እንደ ዳንቴል ክር የተወሳሰበው ችግራችንን በሆይ ሆይታ ልንፈታው ካሰብን ይበልጥ እናጠላልፈዋለን እንጂ አንፈታውም። እስቲ ለዛሬ ይህንኑ ሃሳቤን የሚያጠናክርልኝ አንድ ጥሩ ታሪክ ላጋራችሁ። በዚህ መንገድ ከሄድን የመፍትሄው ቁልፍ በእጃችን እንደሆነ ይሰማኛል።
ከብዙ ዓመታት በፊት በአንድ መስሪያ ቤት ውስጥ የሚያገለግሉ 30 ሰራተኞች ነበሩ። እነዚህ ሰራተኞች ወጣት ከመሆናቸውም በላይ፤ ታታሪ እና የስራ ተነሳሽነታቸው እጅግ የሚያስደስት ነበር። ከዚህም ሌላ ወጣት ሰራተኞቹ አዳዲስ ሀሳቦችን ቶሎ ለመቀበል እና ለመማርም ዝግጁ ነበሩ።
ታዲያ በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ያሉት ሀላፊዎች እነዚህን ሰራተኞች እንዴት ለችግሮች መፍትሄ ማግኘት እንደሚችሉ ሊያስተምሯቸው ይፈልጋሉ። በመሆኑም ሀሳቡን ይነግሯቸዋል። ሰራተኞችም በሀሳቡ ይስማሙ እና የስልጠናው ቀን ይወሰናል።
ስልጠናው በሚሰጥበት እለት ሰራተኞቹ በአንድ አዳራሽ እንዲሰባሰቡ ይደረጋል። እዚህ አዳራሽ ውስጥም አንድ ጨዋታ እንደሚጫወቱ ይነገራቸዋል። እነዚህ ሰራተኞችም ትምህርት ነክ ስብሰባ እንጂ ጨዋታ ለመጫወት እንደተጠሩ ስላልገመቱ፤ በነገሩ በጣም ይገረማሉ። ሁሉም ወደዚህ ስፍራ ሲመጡ የየራሳቸውን ግምት ይዘው ነበር።
አዳራሹ በጣም በሚያምሩ ቀለማት የተዋበ እና የተለያየ የልጆች መጫወቻ የያዘ ነበር። በዚህ ስፍራ አየር የተሞላበት ፊኛ ወይም «ባሎን» በሁሉም ቦታዎች ይገኛል። አዳራሹ ስብሰባ ከማስተናገድ ይልቅ ለጨዋታ በጣም የሚመች ሆኖ ነበር የሚታየው። ሁሉም በነገሩ ስለተገረሙ እርስ በእርስ መንሾካሾክ እና መነጋገር ይጀምራሉ።
በዚህ አዳራሽ ውስጥ በተለየ መልኩ በትልቅ ካርቶን አየር ተሞልቶበት የተቀመጠ ፊኛ ነበር። ፊኛዎቹ የተለያዩ ቀለማትንም የያዙ ነበሩ። ሁሉም ወደ አዳራሹ ገብተው ከተረጋጉ በኋላ የቡድን አስተባባሪው አንዳንድ ፊኛ ከካርቶኑ ውስጥ እንዲወስዱ ይነግራቸዋል። ከዛም ሁሉም እንዲያፈነዱት ይጠይቃቸዋል።
እነዚህ 30 ሰራተኞች በታዘዙት መሰረት የያዙትን አየር የተሞላ ፊኛ ያፈነዱታል። ሁኔታው በጣም የሚያስገርም እና አዝናኝም ነበር። በዚህ ጊዜ ሰራተኞቹ እየተሳሳቁ እና ደስተኛ እየሆኑ ነበር። በድጋሚ የቡድን አስተባባሪ ተመሳሳይ ፊኛ እንዲያነሱ እና በያዙት እስኪሪብቶ እላዩ ላይ ስማቸውን እንዲፅፉ ይጠይቃቸዋል። ፊኛው እንዳይፈነዳም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ይነግራቸዋል።
የጨዋታው ተሳታፊዎች በያዙት ፊኛ ላይ ስማቸውን በጥንቃቄ ለመፃፍ ይሞክራሉ። ሆኖም ግን ፊኛው በአየር በጣም ስለተወጠረ አብዛኛው ይፈነዳል። ስማቸውንም ሳይፅፉ ይቀራሉ። የቡድን አስተባባሪው አሁንም ፊኛው ለፈነዳባቸው ሰራተኞች በድጋሚ እድል ይሰጣቸዋል። ለሁለተኛ ጊዜ እድል ቢሰጣቸውም ግን ከ30 ሰራተኞቹ ውስጥ አምስቱ እድለኛ ሳይሆኑ አሁንም ይፈነዳባቸዋል። በዚህም 25 ሰራተኞች ለሁለተኛው ዙር ጨዋታ ያልፋሉ። በድጋሚ እድል ተሰጥቷቸው ስማቸውን መፃፍ ያልቻሉት ደግሞ በጨዋታው ህግ መሰረት ከውድድሩ ይሰረዛሉ።
በሁለተኛው ዙር የቡድን መሪው ስማቸው የተፃፈበት ፊኛን በመሰብሰብ፤ በአንድ ከፍል ውስጥ ያስቀምጠዋል። ለሁለተኛው ዙር ያለፉትን ሰራተኞች እንዲህ የሚል ትእዛዝ ይሰጣቸዋል « ፊኛውን ባስቀመጥንበት ክፍል ትገቡና ሰማችሁ የተፃፈበትን ፊኛ ታነሳላችሁ። በዚህ ጊዜ ፊኛዎቹ መፈነዳት የለባቸውም» በማለት ያስጠነቅቃቸዋል።
25 ቱም ሰራተኞች ፊኛው በሚገኝበት ክፍል ውስጥ ይገባሉ። የራሳቸው ስም የተፃፈበት ፊኛ ለማግኘትም በጥንቃቄ መፈለግ ይጀምራሉ። በግርግር ወቅት ፊኛው እንዳይፈነዳም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጀምራሉ። ክፍሉ ጠባብ እና በፊኛ የተሞላ በመሆኑም የራሳቸው ስም የተፃፈበትን ለማግኘት አስቸጋሪ ነበር።
በክፍሉ ውስጥ የራሳቸውን ስም ለማግኘት ብዙ ጥረት አደረጉ። በሚያደርጉት ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ ረጅም ደቂቃ ወሰደባቸው። ሆኖም ስማቸው የተፃፈበትን ፊኛ ለማግኘት አልቻሉም ነበር። በዚህ ጊዜ የቡድን አስተባባሪው ስማቸው ያረፈበትን ፊኛ ለማግኘት የሚያደርጉት ጨዋታ ጊዜ እንዳለቀ ይነግራቸዋል።
ጨዋታውን እንዲያቆሙ ያስጠነቀቀው የቡድን መሪ፤ ሶስተኛ ዙር ጨዋታ እንደሚቀርም ይገልፅላቸዋል። ሰራተኞቹ ቀጣዩ የጨዋታ ህግ ምን እንደሚሆን ለማወቅ ጉጉት አደረባቸው። ቡድን መሪው እንዲህ አላቸው « አሁን ክፍል ውስጥ ትገቡና ያገኛችሁትን ፊኛ በማንሳት ስሙ ለሚመለከተው ሰው ትሰጡታላችሁ» አላቸው።
ሰራተኞች በክፍል ውስጥ ይገባሉ። ከፊት ለፊታቸው ያገኙትንም ፊኛ በማንሳት የተፃፈውን ስም ተመልክተው ለጓደኛቸው ይሰጣሉ። በዚህ ጊዜ ፊኛዎቹን በፍጥነት ለሚፈለገው ሰው ደረሱ። በሁለት ደቂቃ ውስጥ የራሳቸው ስም ያለበትን ፊኛ ማግኘት ቻሉ። በነገሩም በጣም በመደነቅ እርስ በእርስ እየተነጋገሩ መሳሳቅ ጀመሩ።
የቡድን አስተባባሪያቸው ጨዋታው ማለቁን አሳውቆ «ይሄ ማለት ለችግሮቻችን ትክክለኛውን መፍትሄ የምናገኝበት ነው። ነገሮችን ሳናገናዝብ በራሳችን ጥረት መፍትሄ እንፈልጋለን። አንድ መገንዘብ ያለብን ነገር፤ እርስ በእርስ በመረዳዳት እና ነገሮችን በመጋራት፤ ለችግሮች መፍትሄ ማምጣት እንችላለን» በማለት ለስራ ባልደረቦቹ በምሳሌ አስረዳቸው።
ሰራተኞቹ በሁኔታው ስለተገረሙ እና ትክክለኛውን መፍትሄ ስላገኙ ተደሰቱ። ለቡድን መሪያቸውም ከመቀመጫቸው በመነሳት ሞቅ ያለ ጭብጨባ አደረጉ ። በመስሪያ ቤታቸው መደጋገፍ እና በጋራ መስራት ጀመሩ። ድርጅቱም ትርፋማ እነሱም ደስተኛ ሆኑ።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19/2012
ዳግም ከበደ