አዲስ አበባ፡- በደቡብ ክልል የሲዳማ ዞን አስተዳደር በህዝብ ላይ የመልካም አስተደዳር ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ፣ የአመለካከትና የብቃት ክፍተት ያለባቸውን 60 በመቶ የሚሆኑ አመራሮችን በአዲስ ኃይል መተካቱን አስታወቀ፡፡
የሲዳማ ዞን አስተዳደር ምክር ቤት ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቃሬ ጫውቻ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤አስተዳደሩ በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ተከትሎ ዕቅድ የማዘጋጀትና በህዝቡ ውስጥ የነበሩ ችግሮችን የመለየት ስራ በመስራቱ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት የመስጠት ችግር ያለባቸውን አመራሮች ገምግሞ ከኃላፊነታቸው የማንሳት ስራ ሰርቷል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው «እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ሰፊ የማጥራት ስራ በመስራት በምትካቸውም አዲስ ኃይል ገብቷል፡፡ ይህንን ስናደርግ በተለይ ከአቅምና ረጅም ጊዜ ከማገልገል ጋር ተያይዞ አሁን ወቅቱ ከሚፈልገው ትኩረትና ከሚጠበቀው ፍጥነት አኳያ በርካታ አመራሮች ተልዕኮውን በብቃት መወጣት አልችልም በሚል በገዛ ፈቃዳቸው ከስልጣናቸው ለቀዋል፤ ይህ ተግባር ያልተመደ በመሆኑ የህዝብ ፍላጎትን በመረዳት የመፍትሄ አካል ሆኖ በራስ ፈቃድ መውጣት እንደመልካም ልምድ ሊወሰድ ይገባል » ብለዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው አብዛኞቹ አመራሮች በተለይም ከትርፍ አበል፥ ከማዳበሪያ እዳ፣ ከከተማ መሬትና ከብልሹ አሰራር ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ አመራሮች ጉዳይ እየተጣራ ሲሆን፤ አብዛኞቹ በብልሹ አሰራር ውስጥ በመገኘታቸው ቅሬታዎችን መሰረት በማድርግ ከስልጣን እንዲነሱ መደረጉን ጠቅሰው፤ እነዚህን ከፖለቲካዊና ከአስተዳደራዊ ተጠያቂነት ባሻገር በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው ተተኪው አዲሱ ኃይል የለውጥ ፍላጎት ያለውና ለውጥን ማስቀጠል የሚችል መሆኑ ታምኖበት የተመደበ መሆኑን ገልፀው፤ ሂደቱ አንዱን አስወጥቶ ሌላውን ማስገባት ሳይሆን ሕዝብን የማገልገል ተልዕኮአቸውን በትክክል ይወጣሉ ተብሎ የታመነባቸው ሊመደቡ መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2011
በማህሌት አብዱል