አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ በሕግ የበላይነት መከበር፣ በህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሁም ሰላምና መረጋጋት ላይ ትልቅ ፈተና የሆነው ሙስና የሞራልና የሥነምግባር ዝቅጠት ውጤት መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።
16ኛውን ዓለም አቀፍ የሙስና ቀን አስመልክቶ በስካይላይት ሆቴል በተካሄደ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ አቶ ታገሰ እንደተናገሩት፤ ሙስናን ከመከላከልና መልካም ሥነምግባርን ከማስፋት አኳያ በርካታ ስራዎች የተከናወኑ ቢሆንም፤ ሙስና ዛሬም የኢትዮጵያ ልማትና ሰላም ችግር ሆኖ ቆይቷል። በመሆኑም የሙስና ተግባር የሞራልና የሥነምግባር ዝቅጠት ውጤት እንደመሆኑ ሁሉም ሊከላከለው ይገባል፡
እንደ አቶ ታገሰ ገለጻ፤ ሙስና ዓለምን ከዓመታዊ አጠቃላይ ምርቷ ላይ አምስት በመቶ ያህል ገቢ እያሳጣት ነው። አፍሪካም የአህጉሪቱን አጠቃላይ ምርት 25 በመቶ የሚሸፍን ገንዘብ በየዓመቱ በሙስና የምታጣ ሲሆን፤ ይሄም የሸቀጦች ዋጋን 20 በመቶ እንዲንር እያደረገ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ። በኢትዮጵያም ቢሆን ሙስና አገሪቱ ከወጪና ገቢ ንግድ ማግኘት ከሚገባት ዓመታዊ አጠቃላይ ገቢ ከ10 እስከ 30 በመቶ እያሳጣት ስለመሆኑ የዓለም ባንክ እና የትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ የ2018 መረጃዎች ያሳያሉ።
በመሆኑም ሙስና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ማነቆ ከመሆኑም በላይ ለሰላም እጦት፣ ለፖለቲካ አለመረጋጋት እና ለእርስ በእርስ ግጭት መንስኤ በመሆን የአገርን ህልውና የሚፈታተን ሆኗል። በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ በሕግ የበላይነት መከበር፣ በህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሁም ሰላምና መረጋጋት ላይ ትልቅ ጋሬጣ በመሆን ትልቅ ዋጋ እያስከፈሉ ካሉ ችግሮች መካከል ዋነኛው ሆኗል።
ይህ የሆነውም የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችና ተቋማት፣ የሲቪክና የሙያ ማህበራት፣ የግሉ ዘርፍና የሚዲያ ተቋማትን የመሳሰሉ ሙስናን ለመዋጋት ትልቅ ድርሻ ያላቸው አካላት ኃላፊነታቸውን በቁርጠኝነት ስላልተወጡ ነው። አሁን ላይ መንግሥት ከመቼውም በላቀ ሙስናን ለመዋጋት ቆርጦ የተነሳ እንደመሆኑ የሞራልና ሥነምግባር ዝቅጠት ውጤት የሆነውም ሙስና ከመከላከል አኳያ ሁሉም የድርሻውን ሊያበረክት ይገባል።
የፌዴራል ሥነምግባርና ጸረሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አየልኝ ሙሉዓለም በበኩላቸው እንዳሉት፤ መልካም ሥነምግባር ያለው ዜጋ ሙስናን ከመዋጋት አንጻር ትልቅ ድርሻ አለው። በአንጻሩ የሞራልና የሥነምግባር ጉድለት ለሙስና ተግባር መስፋፋት ምቹ ነው።
ሙስና ደግሞ በአገር ሁለንተናው የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የጎላ ተጽዕኖ ያሳድራል። ይሄን ችግር ከመከላከል አኳያም ኮሚሽኑ የሚችለውን እየሠራ ሲሆን፤ ከሙስና ተግባር ውስብስብነት አኳያ ችግሩን በሚፈለገው መልኩ መከላከል ባለመቻሉ የሞራልና የመልካም ሥነምግባር ግንባታን በማጎልበት ችግሩን ለማቃለል ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
‹‹ሙስና በግዕዝ ትርጓሜው መበስበስን፣ መሽተትን፣ መከርፋት፣ መትላትና መፍረስን የሚገልጽ ነው›› ያሉት ደግሞ በመድረኩ ንግግር ያደረጉት መጋቤ ሀዲስ አለማየሁ እሸቱ ናቸው። እሳቸው እንደገለፁት፤ የሙስና ተግባርም የበሰበሰ፣ የሸተተና የፈረሰ ህሊና ውጤት ነው።
በሙስና የተገዛ መኪና ከሬሳ ሳጥን ያልተለየ፤ ሙሰኛውም የቆመ እየመሰለው በቁሙ የሞተ መሆኑን የጠቆሙት መጋቤ ሃዲስ፤ ዛሬ ላይ ብዙ ሃብታሞች የቱን እንብላ በሚሉበት ወቅት በሚሊዬን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ምን እንብላ የሚሉበት ደረጃ ላይ ስለመደረሱ ይገልጻሉ።
ይህ ደግሞ ግንዛቤና ገንዘብ አብረው እየሄዱ ስላለመሆናቸው፤ ብዙዎች ኪሳቸው ባዶ ሆኖ ነፍሳቸው ሃብታም ብትሆንም ቁጥራቸው የማይናቁ ደግሞ ኪሳቸው ሞልቶ ነፍሳቸው ባዶ እየሆነች ስለመምጣቷ የሚያሳይ ነው ብለዋል። በመሆኑም ገንዘብና ግንዛቤ እንዲገናኙ፣ ሰርቆ ሳይሆን ሰርቶ መብላት እንዲቻል ሁሉም በንጹህ ህሊና ሊሰራ እንደሚገባ መክረዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2012
ወንድወሰን ሽመልስ