አዲስ አበባ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት በአዲስ ከፍታ ላይ እንደሚገኝ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የቻይና ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪን ትናንት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አገራቱ ግንኙነታቸውን አጠናክረው ለመቀጠል በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሰክሬታሪያት የዲጂታል ሚዲያና የውጭ ቋንቋዎች ጉዳይ ኃላፊ ወ/ሪት ቢልለኔ ስዩም ውይይቱን አስመልክተው ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት በአዲስ ከፍታ ላይ እንደሚገኝና ግንኙነታቸውም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አረጋግጠውላቸዋል፡፡
የቻይና ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በበኩላቸው በዶክተር አብይ የሚመራውን የለውጥ ሂደት ለመርዳት ሀገራቸው ዝግጁ መሆኗን ገልፀው፤ ለዓመታት የቆየው የሁለቱ እህትማማች አገሮች ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ኃላፊዋ አስረድተዋል፡፡ በተያያዘ ዜና የቻይና ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር የቻይናና የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚያጠናክሩ የጋራ ጥቅሞቻቸው ላይ ተወያይተዋል፡፡ ቻይና ከኢትዮጵያ ብሎም ከአፍሪካ ጋር ጥብቅ የኢኮኖሚ ትሥሥር እንዳላት ያስታወሱት ዶክተር ወርቅነህ፣ እስካሁን በነበረው ጠንካራ ግንኙነት ውጤታማ ለውጦች መመዝገባቸውን አስረድተዋል፡፡
ቻይናዊያን የአፍሪካን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገትን በማገዝ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸውንና በአፍሪካ ሀገራት ውስጣዊ ጉዳዮች ጣልቃ የመግባት ፍላጎት ሳትይዝ በትብብር ላይ ብቻ ያተኮረ ግንኙነት መፍጠሯን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አድንቀዋል፡፡ ቀደም ሲል በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በንግድና በኢንቨስትመንት ውጤታማ የትብብር ሥራዎች እንደተሠሩ በማስታወስ አሁንም በኢትዮጵያ በመሰረተ ልማትና በተለያዩ ጉዳዮች ከቻይና ጋር በትብብር ለመሥራት መነጋገራቸውን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል፡፡
በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል የተፈጠረው ሰላማዊ ግንኙነት በተለይም ከኤርትራ ጋር የተፈጠረው እርቅ ለአካባቢው ሰላምና በሀገራቱ መካከል ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተነጋግረዋል፡፡ ለዚህ ጥሩ ጊዜ መፈጠርም የቻይና ሪፐብሊክ መንግሥት አስተዋጽኦ እንደነበረው ዶክተር ወርቅነህ አስታውሰዋል፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደፊት የተሻለ ነገር ለማምጣት ተባብረው እንደሚሠሩ በማረጋገጥ፣ ኢትዮጵያ በጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት እንድትቆይ ቻይና ስላደረገችው ድጋፍ አመስግነው፣ ተልዕኮዋን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቋን አስረድተዋል ፡፡
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በበኩላቸው በተያዘው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ማግሥት የመጀመሪያ ጉዟቸውን በአፍሪካ ማድረጋቸው እንዳስደሰታቸው በመግለጽ፣ ቻይና ከኢትዮጵያም ሆነ ከመላው አፍሪካ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን በአዲስ መልክ እያጠናከረች እንደምትሄድ ገልጸዋል፡፡
ቻይና ከአፍሪካ ጋር የምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም በትብብር ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ከዚህ በፊት በቻይናና በአፍሪካ ትብብር ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን፣ በቀጣይም በመሰረተ ልማት፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በመሳሰሉት በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን ገልጸዋል ፡፡ ቻይና እና ኢትዮጵያ ግንኙነት የጀመሩት እ.አ.አ. ከ1970 ጀምሮ እንደሆነ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2011
በኢያሱ መሰለ