939 ነጻ የስልክ ጥሪ ሲታወስ ወደ አዕምሮአችን የሚመጣው የእሳት አደጋ መኪና የጩኸት ድምጽ ነው፡፡
መልዕክት መቀበያ ስልክ አብዛኛውን ጊዜ ያለምንም አደጋ ክስተት ስድብና ቀልድ እንደሚስተናገድበት የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን በተደጋጋሚ በምሬት ይገልጻል፡፡ እንዲህ ያለው ቀልድና ቧልት አገልግሎት የሚሰጠውን ከማማረሩም በላይ ተጎጂዎች እርዳታ እንዳያገኙ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡ ሰዎች በተጨነቁ እና በተሸበሩ ጊዜ እንዲህ ያለው ተግባር ከወንጀል ተለይቶ አይታይም፡፡
በተለይ በበዓላት ወቅት በሚከሰቱ ድንገተኛ አደጋዎች የህክምና እርዳታ ሳያገኙ የሚቀሩ ሰዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ችግሩ ዛሬ ባይቀረፍም ባለሥልጣኑ መስመሩን ክፍት አድርጎ ለትክክለኛ መረጃ ማዋሉን አላቋረጠም፡፡ ባለሥልጣኑ በመጪው የገና በዓል ለሚያጋጥሙ ችግሮችም ተያያዥ ቅድመ ዝግጅቶችን አድርጌያለሁ እያለ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሠለሞን መኮንን እንደሚሉት፤ በገና በዓል ሊከሰቱ የሚችሉ የእሳት አደጋዎችን ህብረተሰቡ አስቀድሞ እንዲከላከል ቅድመ ዝግጅቶች ተደርገዋል፡፡ በአደጋ ወቅት ሊወሰዱ የሚገቡ የመፍትሄ እርምጃዎች መልዕክት የያዙ በራሪ ጽሁፎች በማሰራጨት፣ በመገናኛ ብዙኃንና በየጎዳናው ላይ በሚደረጉ የተለያዩ እቅንስቃሴዎች መልዕክት የማስተላለፍ ስራ እየተሰራ ነው፡፡
በየክፍለ ከተማው ባሉት ጽህፈት ቤቶችም ባለሙያዎች ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ ከሚችሉ አደጋዎችና ለአደጋ መንስኤ ከሆኑ ነገሮች እንዲጠነቀቅ እንዲሁም አካባቢያዊ ቅኝት በማድረግ የማስጠንቀቂያ ሥራዎችም ይከናወናሉ፡፡ ሆቴሎች፣ መዝናኛ ሥፍራዎችና ለአደጋ ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉ አካባቢዎችንም በማሰስ የምክር አገልግሎት የመስጠትና የቅድመ አደጋ መከላከል ሥራዎችም በቅድመ ዝግጅቱ ተካተዋል፡፡
የቅድመ አደጋ መከላለከል ሥራው ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ እንደሚከናወንና ከህብረተሰቡ የሚደርሰውንም ጥቆማ መሰረት አድርጎ ለመንቀሳቀስ የሰው ኃይል በማቀናጀት ልዩ ዝግጅት አድርጓል፡፡ ህብረተሰቡ አደጋ ሲያጋጥመው በነጻ የስልክ ጥሪ በ939 ደውሎ ማሳወቅ ይችላል፡፡ ለማስዋቢያ ጥቅም ላይ የሚውሉ ተቀጣጣይ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀም በበዓላት ወቅት ለአደጋ አጋላጭ መሆናቸውን ህብረተሰቡ ተገንዝቦ እንዲጠነቀቅና የምሽት ሥራ የሚሰሩ ተቋማትም በበዓል ሰሞን የሚኖረው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ፍጆታ አደጋ እንደሚያስከትል በመረዳት ሁሉም የየቡኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
ህብረተሰቡ ከድንገተኛ እሳት አደጋ ብቻ ሳይሆን፣ በገበያ ቦታዎች ከሚያጋጥሙ መሰል ወንጀሎች ጭምር እንዲጠነቀቅ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መልዕክት አስተላልፏል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ፤ በክርስትና እምነት ተከታዮች በኩል በድምቀት ከሚከበሩት አበይት በዓላት ውስጥ አንዱ የገና በዓል መሆኑን በመጥቀስ፤ በዓሉን ህብረተሰቡ በሚንቀሳቀስባቸው ሁሉም ቦታዎች በተለይም በመዝናኛ ስፍራዎች፣ በዕምነቱ ተቋማትና በገበያ ቦታዎች አደጋ እንዳይደርስበትና የወንጀል ጥቃት እንዳይፈጸምበት ይሰራል ብለዋል፡፡
በዓሉ በሰላም እንዲከናወን ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ማብራሪያ የቁጥጥር ሥራውን መስራት ከሚገባቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የጸጥታ አስከባሪ ኃይል በቂ እውቀት ኖሮት ስራውን እንዲሰራ እየተደረገ ነው፡፡ በቂ የሰው ኃይል በመመደብ በሁሉም አካባቢዎች በግልጽና በሥውር ጥበቃዎች ይደረጋሉ፡፡ የሚኖረውን ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰትም በመቆጣጠር አደጋን ለመቀነስ የተጠናከረ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
በስውርና ግልጽ ጥበቃ ላይ የሚሰማራው የጸጥታ አስከባሪ ኃይል ዜጎች ወንጀል እንዳይፈጸምባቸውና ወንጀል ተፈጽሞ ከተገኘም ከህዝብ ጋር በመሆን አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል፡፡ የሰው ኃይሉ በአእምሮም ሆነ በአካል ዝግጁ መሆኑን ነው ኮማንደር ፋሲካ የገለጹት፡ ፡ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጎን እንዲሆን እንዲሁም በዓሉን የሚታደሙ የውጭ ሀገር ዜጎችን በተለመደው የእንግዳ አቀባበል በማስተናገድ በዓሉን በሠላም እንዲያከብሩ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
በበዓል ወቅት ከወንጀል ጋር በተያያዘ አብዛኛውን ጊዜ ህገ ወጥ በሆነ መልክ ለማክበር የሚፈልጉ አካላት የገበያ ግርግርን በመጠቀም በአድ ነገሮችን ቀላቅለው እንደሚሸጡና በዚህ የማጭበርበር ተግባር ውስጥ የሚሳተፉትን አካላት ፖሊስ እርምጃ እንደሚወስድበት ኮማንደሩ አስታውቀዋል፡፡ በግብይት ወቅት የኪስ ስርቆትና ሌሎች የሌብነት ወንጀሎች ሲፈጽሙ የሚገኙትም ተገቢውን ቅጣት ያገኛሉ ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2011
በአዲሱ ገረመው