ኢትዮጵያ በአጠቃላይ የለውጥ ሂደት ላይ ትገኛለች። ከእነዚህ የለውጥ መገለጫዎች ውስጥ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ተጠቃሽ ነው። ለዚህም አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። ይህን ሪፎርም ውጤታማ ለማድረግ አገሪቱ እያከናወነቻቸው ባሉ ተግባራት ዙሪያ ከኢንሼቲቭ አፍሪካ ዋና ስራ አስፈጻሚና ኢኮኖሚስት አቶ ክቡር ገና ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከአለም ባንክና ከአይ.ኤም.ኤፍ 9 ቢሊዮን ዶላር ብድርና እርዳታ አግኝታለች። አጠቃላይ ሁኔታውን እንዴት ያዩታል?
አቶ ክቡር፡- የተገኘው ብድር ነው። ብድር መከፈል አለበት። ለመክፈል አቅም ያስፈልጋል። ገንዘቡ ሊወጣ የታሰበው ለተጀመሩና በጅምር ላሉ ፕሮጀክቶች በወቅቱ ገንዘብ ተበድረውባቸው ለተሰሩ ፕሮጀክቶች ሊሆን ይችላል። እነዚህን ፕሮጀክቶች ጨርሶ ይሄን ብድር ለመክፈል አቅም ይኖራል ወይንስ አይኖርም የሚለው ዋናው ጉዳይ ነው። ሁልግዜም ችግሩ ብድር መምጣቱ ላይ አይደለም። የመክፈል አቅም አለን ወይስ የለም የሚለው ነው። የመክፈል አቅም ከሌለ የበለጠ ችግር ውስጥ እንገባለን።
ዋናው ጥያቄ የብድር ገንዘቡ መምጣት አለመምጣት ሳይሆን ገንዘቡ እንዴት ሊመጣ ቻለ የሚለው ነው። አይ ኤም ኤፍ ብድሩን ሲሰጥ ለኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ ምን አይነት ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጦአል የሚለው መታየት ያለበት። ይሄ ባልተገለጸበት ሁኔታ እነዚህ ብድሮች መምጣት አለመምጣታቸው ብዙም ትርጉም የለውም።
አዲስ ዘመን፡- በቀደሙት አመታት የመንግስት ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታነት ሲዞሩ ብዙ ሰራተኞች ከስራ ይቀነሳሉ። አሁንም ተመሳሳይ ችግር ይከሰታል የሚል ስጋት አለ። ስራ አጥነትን አያበራክትም ?
አቶ ክቡር፡- ይሄ እንደሚሆን የታወቀ ነው። የመንግስት አላማ ትርፍ ማምጣት አይደለም። ድርጅቶቹን ሲያስተዳድር ወጪያቸውን እንዲ ሸፍኑ ከተቻለም የተወሰነ ገቢ እንዲያገቡ ነው። የሕዝብን ፍላጎት ለማሟላት እንጂ ትርፍ ላይ ያተኮረ አይደለም። የንግድ ድርጅት አላማ ትርፍን መሰረት ያደረገ ነው። ትርፍ የሚመጣው አንደኛው በተቻለ መጠን ወጪን መቀነስ በሚቻልበት ሁኔታና ወጪው ሊያድግ የማይችልበትን መንገድ ማለትም የሰው ኃይልን መቀነስ ብቻ ሳይሆን የሰው ኃይል በቴክኖሎጂ እንዲለወጥና እንዲሸፈን ለማድረግ ነው። ሁለተኛው ሠራተኛ መቀነስ ብቻ ሳይሆን የዋጋ ጭማሪም ይኖራል። ምክንያቱም ድርጅቱ ለማትረፍ ነው የመጣው። የግል ድርጅት ስለሆነ መንግስት የዋጋ ቁጥጥሩን ለሕዝብ ሊጠቅም በሚችልበት መልኩ ለማስተካከል አቅም አይኖረውም።
ሶስተኛው ደግሞ ትላልቅ ስትራቴጂክ የሆኑ የሀገር ሀብቶች በተለይ ቴሌኮሙኒኬሽንን ብንወስድ አንድ ቀን የገዛው ድርጅት የግል ስለሆነ በራሱ ምክንያት ይሄ ካልተደረገልኝ በሚል ስራውን ሊያቆም ይችላል። የዚህን ጊዜ መንግስት ምንድነው የሚያደርገው የሚለው አስቀድሞ መታየት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ግዙፍ ሀገራዊ ተቋማትን አየር መንገድ፣ቴሌ፣ ባንክ የመሳሰሉትን ለኢንቨስተሮች መሸጡ ለኢትዮጵያ የሚያ ስገኘው ጥቅም ምንድነው?
አቶ ክቡር፡- የሚሸጡበት ምክንያት ምንድነው ለሚለው በመንግስት እይታ በትክክል አልተቀመጠም። ብድር ለመቀነስ ነው ይላል። ብድር ለመቀነስ ነው ከተባለ አሁን የሚመጡት ብድሮች በሙሉ ያለብንን ብድር እየጨመሩት እንጂ እየቀነሱት አይሄዱም። በአንድ በኩል ‹‹ብድር ለመቀነስ ነው የምንሸጠው›› ተብሎ በሌላ በኩል ብድሩ እንዲቀጥል ከተደረገ ትርጉም የሌለው ስራ ነው። በተለይ ደግሞ እነዚህ ገንዘቡን የሚያመጡት የእኛ ድርጅቶች ትርፋማነታቸው የታወቀ ወደድንም ጠላንም የሀገር ኩራት የሆኑ ናቸው። በተለይ አየር መንገድ የሀገራችን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም መኩሪያ ነው።
ብዙ ለሀገሪቷ የሚጠቅም አስተዋጽኦ አለው። ቴሌኮሙኒኬሽን፤ መብራት ኃይል (ኤልፓን) የመሳሰሉት ትላልቅ ድርጅቶች መጀመሪያም በመንግስት እጅ የሆኑበት ምክንያት አለ። የግል ሴክተሩ ለሕዝብ ጥቅም አገልግሎት መስጠት አይችልም በሚል ነው። አሁን አገልግሎቱ የሚፈለገው ትርፍ የሚያመጣ ድርጅት ትርፍ ሊያመጣ እንዲችል ተደርጎ እነዚህ ድርጅቶች እየተዘጋጁ ነው ያሉት ።
ለአገልግሎት ለሕዝብ ጠቀሜታ ሳይሆን ለገዢው ትርፍ ማግኛ ብቻ የገዢውን ኪስ ማዳበሪያ ነው የሚሆኑት ማለት ነው። ቴሌኮሙኒኬሽን ቅልጥፍና ይጎለዋል በጣም ኋላ የቀረ ድርጅት ነው የሚል እሳቤ አለ። መንግስት ለዚህ ችግር መፍቻ መሆን የሚችል የአስተዳደራዊ ፤ የሠው ኃይል ፤ የክፍያ ለውጥ፤ ማድረግ ሲችል አላደረገም። ምክንያቱ ተቀባይነት የለውም። ሌላው ሀሳብ ኢንቨስተር ይስባል የሚለው ነው። መሳቢያው እሱ ነው ወይ? ፕራይቬታይዝ ሲደረግ ነው ኢንቨስተር የሚስበው? ወይስ ለኢንቨስተር የሚሆን አገልግሎት መስጠት የሚችል ሲኖር ነው። በዚህ መልክ ነው የሚታየው የሚመስለኝ። የፕራይቬታይዜሽኑ አላማ ግልጽ አይደለም። በእኔ አስተያየት የውጭዎቹ የጠየቁት ጥያቄ ስለሆነ የእነሱን ፍላጎት ለሟሟላት የሚደረግ ነው ብዬ እገምታለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የተሻለ መፍትሄ ነው የሚሉት ምንድነው ?
አቶ ክቡር፡- ችግሩ እንደገለጽኩት ነው። የገንዘብ ችግር ከሆነ የገንዘብ ችግር መፍቻ የሚሆኑ አማራጮች አሉ። ከስንቶቹ አማራጮች ተመርጦ ነው ፕራይቬታይዝ ይደረጉ የተባለው? ኃላፊዎቹ ይህን ችግር መፍቻ ሀሳብ አምጡ ሲባሉ አንድ ሁለት ሶስት ተብሎ ሀሳብ ይመረጣል። ሁለተኛና ሶስተኛ የመጡት ሀሳቦች ምን ሆነው ነው አንደኛው ፕራይቬታይዝ ይደረጉ የተባለው የተመረጠው?
የመንግስት ድርጅቶች ፕራይቬታይዝ የሆኑበትን የሌሎችን ሀገራት ተሞክሮ መመልከት ነው። የእንግሊዝ ትልቁ የሌበር ፓርቲ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በቅርቡ በምርጫ ቢሸነፍም አንደኛው አላማው በፕራይቬታይዜሽን የተሸጡ ድርጅቶችን መመለስ ነው። የእንግሊዝን አንድ ሴክተር እንውሰድ። የባቡር መስመሩ ተሸጠ። መጨረሻ ላይ ለማን እንደተሸጠ አይታወቅም። ሻጩ ሌላ ነው። ሌላ ሻጭ ይሸጣል። እዛ ቦታ መንግስት አያገባውም። ቢያገባውም ብዙ ከእሱ የሚያመልጡ ነገሮች አሉ።
አዲስ ዘመን፡- በረቂቅነት የቀረበው ኤክሳይዝ ታክስን በተመለከተ የሚሰጡት አስተያየት ካለ?
አቶ ክቡር፡- ኤክሳይዝ ታክስ ድሮም ነበረ። ድሮም ሀገሪቷ ከምትሰበስባቸው የታክስ አይነቶች ውስጥ ዝቅተኛው ነው። እሱን ከፍ ለማድረግ ነው የተሞከረው። የኤክሳይዝ ታክሱ ጭማሪ ከፍተኛ በመሆኑ ብዙዎችን አስደንግጧል። ነገር ግን አዋጁ አዲስ ሆኖ አይደለም። በዚህ ገንዘብ የህዝብን ኑሮ ለማሻሻል ነው ጭማሪው የሚወጣው ወይንስ አሁን ያለውን አካሄድ ለመደገፍ ነው የወጣው የሚለው መታየት አለበት። በዚህ ታክስ ምክንያት የህዝቡ ኑሮ፤ ትምህርት ቤቶች ይሻሻላሉ፤ በጤናው ዘርፍ የምንሰጠው አገልግሎት ከፍ ያለ ይሆናል፤ ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ ይቀርባል የሚለውን የሚሸፍን ከሆነ ሰው እየደኸየም ቢሆን በሌላ በኩል አገኘዋለሁ ይላል። አሁን ከዚህ የሚገኘው ገንዘብ ለምን እንደሚውል እንኳን አናውቅም።
አዲስ ዘመን፡- በገንዘብ እጥረት ተጀምረው የቆሙ በርካታ ፕሮጀክቶች አሉ። ቀጣይ እጣ ፈንታቸው ምን ይሆናል ብለው ይገምታሉ ?
አቶ ክቡር፡- እነዚህን ፕሮጀክቶች ለመስራት የወጣ ገንዘብ አለ። ገንዘቡ መመለስ ስላለበት ነው ወደ ፕራይቬታይዜሽን መሄድ የተፈለገው። ፕራይቬት ሴክተሩ ሞኝ አይደለም። እንኳን በጨረታ ገበያ ላይ አውጥተህ ትርፍ ያመጣል ለማለት በነጻ ብትሰጠውም አይወስድም። ስለዚህ ቀዳሚ የሆኑትን ነገሮች እንደገና መመልከት ያስፈልጋል።
እንደሚታወቀው ብዙ ገንዘብ በሙስና ጠፍቶአል። በሙስና ውስጥ ገብተው ይሄ ችግር እንዲፈጠር ያደረጉት ሰዎች በከተማው ውስጥ አሉ። መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። የሕዝብ ገንዘብ እስከሆነ ድረስ ወደ ሕዝብ መምጣት መቻል አለበት። የሕዝብ ገንዘብ መሆኑ ከታመነበት መውሰድ መውረስ ወደ ሕዝብ መመለስ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- አለም አቀፍ ተቋማት ብድር ሲሰጡ የሚያስቀምጡት ቅድመ ሁኔታ አለ።(ሎን ኮንዲሽንድ) የሚሉት። በአሁኑ ብድር ይሄ ሁኔታ (ኮንዲሽን) አለ ብለው ያስባሉ ?
አቶ ክቡር፡- በሁሉም አለም ያደርጉታል። ለእኛ የተለየ ሊያደርገው የሚችል ምን ነገር አለ? ፕራይቬታይዜሽኑ አንዱ ኮንዲሽን ነው። በሩን ክፈቱ አንዱ ኮንዲሽን ነው። የውጭ ድርጅቶች ገብተው ይስሩ እነዚህ ሁሉ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው። ብዙ ኮንዲሽኖች አሉ። ያሉህን ካላደረክ የቅጣት ኮንዲሽኖችም አሉ። ይሄን በዚህ ቀን ካላደረክ ይሄን ደግሞ እንደዚህ ካላደረከው አለ። ለምሳሌ የቴሌኮሙኒኬሽኑን ብትወስድ ሁለት የግል ተሳታፊ ድርጅቶች እንዲገቡ 49 ፐርሰንት ይሁን ምን እንዲሸጥ ኮንዲሽኑ ውስጥ አለ። እነዚህን ሁሉ እኛ የምንቆጣጠራቸው አይደሉም።
አዲስ ዘመን፡- አለም አቀፍ ተቋማት በብድርና እርዳታ የሚገኘውን ገንዘብ የሚሰጡት በአንዴ ነው ወይንስ እያከፋፈሉ ?
አቶ ክቡር፡- እንደ ስምምነቱ ነው ። አበዳሪው በአንድ ግዜ ለምን ይሠጥሀል? አይሰጥም። ያስቀመጠልህን ቅድመ ሁኔታ ሟሟላትህን እያየ ነው የሚሰጥህ። ያልኩህን ይሄን ይሄን አድርገሀል ወይ ይልሀል አዎ ትላለህ እሺ አሁን ይሄን ያህል እለቅልሀለሁ ይላል። ይሄን አላደረክም አዎን አላደረኩም ይሄን ካለደረክማ አለቅልህም ይልሀል። እንደዛ እየተባለ ነው እስከዛሬ በሙሉ ሀገራትን ያደሀዩት።
አዲስ ዘመን፡- የተገኘው ብድርና እርዳታ የኢኮኖሚ መረጋጋት ይፈጥራል ብለው ያምናሉ ?
አቶ ክቡር፡- ለተወሰነ ግዜ ሊፈጥር ይችላል። ለተወሰነ ግዜ የውጭ ምንዛሪ ችግር ሊነሳ ይችላል። የኤክሳይዝ ታክስ ኮንዲሽናሊቲው አንዱ ነው። የሀገር ውስጥ ገንዘብ በበቂ ሁኔታ አይሰበሰብም ሲል ይህን በማድረግ እንዲሰበሰብ ያደርጋል። እነዚህን ለመሰብሰብ ደግሞ መንግስትን ላያስቸግር ይችላል። ብድር ሀገርን ሊያሳደግ እንደማይችል ራሳቸው ያውቁታል። ብድር የወቅቱን የግዜውን ችግር ይፈታ እንደሁ እንጂ ዘላቂነት ያለው ነገር አይሰጥም። ዘላቂነት ሊሰጥህ ካልቻለ አንድ ቦታ ላይ መውደቅህ አይቀርም። የዶላሩ ብድር እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም የሚሄደው።
አዲስ ዘመን፡- ኢኮኖሚው ካሉበት ችግሮች መውጣት የሚችለው እንዴት ነው ?
አቶ ክቡር፡- ለሁሉም ነገር መፍትሄው የሀገር አንድነትና ሰላም መኖር ነው። በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች አነሰም በዛ የሰላም ችግሮች አሉ። በየክልሉ ጸጥታ ለማስከበር አቅም እያነሰ ነው ያለው። ቢዝነስ ሰላም ይፈልጋል። ገንዘቡን ከባንክ አውጥቶ ሰርቶ ነግዶ መልሶ ባንክ መመለስ አለበት። ያንን ለማድረግ የሚያመች ሁኔታ ከሌለ ገንዘቡን ለማውጣት የሰው ፍላጎቱ ይቀንሳል። ስለዚህ አሁን ባለንበት ሁኔታ በመጀመሪያ ደረጃ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች መስመር መያዝ አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ ክቡር፡- እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 16 /2012
ወንድወሰን መኮንን