አዲስ አበባ፡- በኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተመራ የልኡክ ቡድን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል ሽልማትን በተቀበሉ ማግስት የመጀመሪያውን የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ትናንት አዲስ አበባ ገብቷል፡፡
ልኡኩ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡
በእለቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ‘’የሰላም ጓዴ የሆኑትን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን እና የልዑካን ቡድናቸውን ሁለተኛ ቤታቸው ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ እንኳን በደህና መጡ እላለሁ።’’ በማለት አስፍረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
ከምክክሩ በተጨማሪም መሪዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ላይ በመገኘት ጉብኝት አድርገዋል፡፡
ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደኃላፊነት ከመጡ በኋላ እርሳቸው እና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በሰሩት ሥራ በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም ግንኙነቱ ወደነበረበት እንዲመለስ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ሁለቱ መሪዎች በአገራቱ መካከል የተደረሱ የሰላምና ወዳጅነት ስምምነቶችን በወቅቱ የተፈራረሙ ሲሆን ፤የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱንም ወደ ቀድሞ ገፅታው መመለስ ተችሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ2019 የሰላም የኖቤል ሽልማትን በተቀበሉበት ወቅት በኦስሎ ባደረጉት ንግግር በሁለቱ ሀገራት ሰላም መስፈንና ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶች ዳግም መመለስ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ሚና ትልቅ እንደነበር ገልፀው፤ ለሽልማት ለመብቃታቸውም ፕሬዚዳንቱንና የኤርትራን ህዝብ አመስግነው ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኖርዌይ አዲስ አበባ ሲመለሱ ባደረጉት ንግግርም በቅርብ ቀን ውስጥ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር ተገናኝተው ደስታውን በጋራ እንደሚያከብሩ ገልፀው እንደነበር ይታወሳል::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2012
ድልነሳ ምንውየለት