አዲስ አበባ፡- ለዳያስፖራው ማህበረሰብ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ታሳቢ ባደረገው ከወለድ ነፃ የቤት ግዥ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአንድ ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ 127ሺ ዶላር መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳያስፖራ ቅርንጫፍ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ለማ ዋቀዮ አገልግሎቱን አስመልክተው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ባንኩ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2019 ጥቅምት አራት ቀን በጀመረው ዲያስፖራ ከወለድ ነፃ የቤት ግዥ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአንድ ወር ተኩል ውስጥ የባንከ ሂሳብ ከከፈቱ 125 ዲያስፖራዎች 127ሺ ዶላር መሰብሰብ ችሏል፡፡
እንደ አቶ ለማ ማብራሪያ ቤት ፈላጊው 20 በመቶ በዶላር ቅድመ ክፍያ እንዲፈጽም በማድረግ፣ 80 በመቶውን ደግሞ ባንኩ በብር በማሟላት የቤት ግዥው የሚከናወን ሲሆን፣ ባንኩ ያሟላውን 80 በመቶ ዳያስፖራው ባንኩ ባመቻቸው የክፍያ ማጠናቀቂያ ጊዜ ክፍሎ እንዲያጠናቅቅ ያደርጋል፡፡
ባንኩ አገልግሎቱን የሰጠው በግንባር ከቀረቡት ዳያስፖራዎች ጋር መሆኑን የጠቆሙት አቶ ለማ ፤ወደፊት ባሉበት ሀገር ሆነው በበይነ መረብ ግንኙነት በመፍጠር የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋት ከውጭ ጉዳይ የዲያስፖራ ኤጀንሲ፣ ኤምባሲዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አገልግሎቱን ማጠናከር ከተቻለ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማሳደግ ወይም ሀብት ማሰባሰብ እንደሚቻል በአጭር ጊዜ ውስጥ በተሰጠው አገልግሎት ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን ማረጋገጥ መቻሉን አመልክተዋል፡፡ ባንኩም ፍላጎቱን የሚመጥን አደረጃጀት እንዲኖር ለጊዜው አገልግሎቱን በማቆም እየሰራ መሆኑንና ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት በኋላ በተደራጀና በተጠናከረ አሰራር እንደሚጀምር ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ ለማ ገለፃ ባንኩ በአጭር ጊዜ አገልግሎቱ ካያቸው ክፍተቶች ውስጥ የቤት ግዥ የሚፈጸምላቸው ዳያስፖራዎች የሥራ ቅጥር ውል፣ የደመወዝ መጠንና የተለያዩ ሰነዶች ትክክለኛነት ማረጋገጥ አንዱ ሲሆን፣ ችግሩን ለመቅረፍ ከውጭ ጉዳይ የዳያስፖራ ኤጀንሲ ጋር ምክክር ተደርጎ መፍትሄ ተበጅቷል፡፡ የቤት አቅርቦትና የዋጋ ግነት ችግርንም ባንኩ ቤት ገንብተው ለሚያቀርቡ ቅድሚያ በመክፈል ለመከላከል አቅዷል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2012
ለምለም መንግሥቱ