• የሚስጥር ቁጥር የተገጠመላቸው ዲጂታል ሚዛኖች ሊያስገባ ነው
አዲስ አበባ:- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ 186 የንግድ ድርጅቶች ላይ የማሸግ እርምጃ ሲወስድ ለአራት ሺ 527ቱ ደግሞ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። የሚስጥር ቁጥር የተገጠመላቸው ዲጂታል ሚዛኖችንም ወደ ግብይት ስርዓት እንደሚያስገባ ገልጿል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ቢሮው በግብይት ወቅት በመስፈሪያ መሳሪያዎች አማካኝነት የሚፈጸመውን ቅሸባ ለመከላከል ባለፉት አራት ወራት ሰባት ሺ 500 የመስፈሪያ መሳሪያዎችን በመፈተሽ በ186 የንግድ ድርጅቶች ላይ የማሸግ እርምጃ ሲወስድ ለአራት ሺ 527ቱ ደግሞ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፤ በመዲናዋ ከሚስተዋለው የኑሮ ውድነትና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባሻገር ሸማቹ ማህበረሰብ እንደ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ስጋና ዳቦ የመሳሰሉትን ሲገዛ ለከፈለበት ዋጋ በትክክለኛው የመስፈሪያ መሳሪያ ተመዝኖ አይሰጠውም ፤ በዚህ ሁኔታ የሚፈጸመው ቅሸባ ከፍተኛ በመሆኑ ቢሮው ባለፉት አራት ወራት ችግሩን ለመከላከል በሰባት ሺ 500 የመስፈሪያ መሳሪያዎች ላይ ፍተሻ ማድረጉን ይናገራሉ።
አብዛኞቹ የንግድ ድርጅቶች የሚጠቀሟቸው የመስፈሪያ መሳሪያዎች አናሎግ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የሚታዩ ክፍተቶች እንዳሉ የሚናገሩት ሀላፊው፤ በእድሜ መግፋትና በአንዳንድ የቴክኒክ ክፍተት ከትክክለኛ ልኬታቸው በታች ወይም በላይ የሚለኩ የመስፈሪያ ማሽኖችን በማስተካከል ትክክለኛ አገልግሎት እንዲሰጡ ሆኗል። ከዚህ ውጪ ችግር የነበረባቸው 186 ማሽኖች እንዲወገዱ ተደርጓል።
ነጋዴዎቹ የመስፈሪያ መሳሪያዎቹን ሆን ብለው ከልኬታቸው በታች እንዲሰሩ በማድረግ በሸማቹ ላይ ጫና በፈጠራቸውም አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል። በዚህም 186 የንግድ ድርጅቶች ላይ የማሸግ በአራት ሺ 527ቱ ላይ ደግሞ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም አልፎ አልፎ በነዳጅ ማደያዎች ላይ የሚታየውን የነዳጅ ቅሸባ ለመከላከል በተደረገ የቁጥጥር ሥራ፤ ከሊትር ቅሸባ ባለፈ የአሰራር ክፍተቶች ታይተዋል ያሉት ኃላፊው፤ በዚህም ሶስት ነዳጅ ማደያዎች እንዲታሸጉ ተደርጓል። እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከልም ጉዳያቸው በህግ መታየት ያለበትን ወደ አቃቢ ህግ ተላልፎ እየታየ ነው።
በአጠቃላይ ችግሩን ለመቅረፍ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያለውን የመስፈሪያ መሳሪያዎች ማዘመን እንደሚገባ የሚናገሩት ኃላፊው፤ በተለይ በመዲናዋ በስፋት በዳቦ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ስጋ ቤቶች ላይ በቴክኖሎጂ የዘመኑ ዲጂታል ሚዛኖችን በጀት ዓመቱ መጨረሻ በግብይት ስርዓት ላይ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።
ሚዛኖቹ ከሰው እጅ ንክኪ በጸዳ መልኩ በመቆጣጠሪያ (በሪሞት) የሚታዘዙና የሚስጥር ቁጥር የተገጠመላቸው በመሆኑ ማንም ሰው የልኬት መጠናቸውን እንደፈለገ ከፍና ዝቅ ማድረግ እንደማይችል የሚያስረዱት ኃላፊው፤ ሚዛኖቹንም አስገዳጅ የሆነ የህግ ማዕቀፍ በማውጣት ነጋዴው ማህበረሰብ ሥራ ላይ እንዲያውላቸው ይደረጋል። የልኬት ማሺኖቹን በታቀደው ጊዜ ወደ ሥራ ለማስገባት በትኩረት እየተሰራ ነውⵆ ወደ ተግባር ሲገቡ አሁን ላይ የሚታየውን ችግር በመቅረፍ ተጨባጭ ለውጥ እንደሚያመጡም ነው ኃላፊው የተናገሩት።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2012
ሶሎሞን በየነ