አዲስ አበባ:- በመንግሥት የግዥ ህግና መመሪያ መሰረት በማይጓዙ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመ ውሰድና አደብ ለማስገዛት እንዳልቻለ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ።
በኤጀንሲው ኦዲትና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ዘለቀ ታፈሰ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ ተቋማቱ የግዥ ህግና መመሪያ ጥሰው ሲገኙ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችለው ስልጣን ስላልተሰጠው እርምጃ መውሰድ አልቻለም፤ ስለሆነም ተቋማቱ በተደጋጋሚ ህግና መመሪያን እየጣሱ ነው።
እንደ አቶ ዘለቀ ማብራሪያ፤ ኤጀንሲው ተቋማት በመንግሥት የግዥ ህግና መመሪያ መሰረት ግዥ መፈጸማቸውን የመቆጣጠር እንዲሁም ንብረት ኦዲት ካደረገ በኋላ የኦዲት ግኝቱን ለተቋማቱ ሪፖርት የማድረግ ኃላፊነት ያለበት ሲሆን ፣ተቋማቱ ደግሞ ከኤጀንሲው በተሰጣቸው የኦዲት ግኝት መሰረት፤ የእርምት እርምጃ መውሰድና ተገቢው ማስተካከያ በማድረግ ማሳወቅ አለባቸው።
ከዚህ ውጪ ኤጀንሲው የመንግሥትን የግዥ ህግና መመሪያ ያልፈጸሙ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችለው ስልጣን ስለሌለው የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ አለመቻሉን ተናግረዋል።
‹‹ኤጀንሲው ጥርስ የሌለው አንበሳ ሆኗል›› የሚ ሉት ዳይሬክተሩ፤ በተገኙ የኦዲት ግኝቶች መሰረት ህግና መመሪያውን ተላልፎ የተገኘን አካል ተጠያቂ የሚያደርግበት የአሰራር ሥርዓት ካለመኖሩ ባሻገር ተቋማቱ በተሰጣቸው የኦዲት ግኝት ሪፖርት መሰረት ተገቢውን እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር በየዓመቱ መሰል የግዥ ህግና ደንብ የመጣስ ተግባር እንደሚታይባቸው ገልጸዋል።
ለአብነት በ2012 በጀት ዓመት 88 መስሪያ ቤቶችን ለመቆጣጠር ታቅዶ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 14 ተቋማትን ኦዲት ማድረግ መቻሉን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በዚህም የግዥ አፈጻጸም ሪፖርት ወቅቱን ጠብቆ አለመላክ፣ ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ማንኛውንም የግዥ ጨረታ ሰነድና ከአሸናፊው ጋር የተዋዋሉትን ውል በኤጀንሲው ድህረ ገጽ ለህዝብ ይፋ አለማድረግ፣ አቅራቢው እቃውን ሲያዘገይ የማካካሻ ገንዘብ አለመሰብሰብ ፣ በጨረታ ሰነዱ መሰረት ግዥ አለመፈጸምና ቅድሚያ ክፍያ እንደሚከፍሉ ሳይገልጹ ክፍያ መፈጸም፣ በጨረታ ሰነዱ ላይ ቀድሞ ባልተቀመጠ መስፈርት ተጫራቾቹን መገምገም እና የንግድ ምልክት (ብራንድ) መጥቀስ፣ ለአሸናፊና ተሸናፊ ተጫራቾች በእኩል ጊዜ የጨረታ ሂደቱን በደብዳቤ አለማሳወቅ፣ ግዥን ከፋፍሎ በመፈጸም መንግሥት ከጥቅል ግዥ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም ማሳጣት፣ ዋጋ ላልወጣላቸው ዕቃዎች ኮሚቴ በማቋቋም ዋጋቸውን አለማሳወቅ፣ የቋሚ ንብረቶች መመዝገቢያ ሰነድ አለመጠቀም፣ በመኪኖች ላይ የድርጅቱን አርማ አለመለጠፍና በሊትር ምን ያህል ኪሎ ሜትሮችን እንደተጓዙ ቁጥጥር አለማድረግ፣ የንብረት የእርጅና ወጪን አለማስላትና ሌሎችም በ 14ቱ ተቋማት ላይ የታዩ የኦዲት ግኝቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ አንጻር ተቋማት የግዥ ህግና መመሪያን እያወቁ ተግባራዊ ባለማድረግ ለፈጸሙት ስህተት እራሳቸው የእርምት እርምጃ እንዲወስዱ ስልጣን መሰጠቱ በተ ደጋጋሚ በማናለብኝነት ህግና መመሪያን እንዲጥሱ በር ከፍቷል። ኤጀንሲውም በኦዲት ግኝቱ መሰረት የእርምት እርምጃ እንዲወስዱ ሪፖርት ቢያደርግም ወደ ተግባር አለመቀየሩን አቶ ዘለቀ ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2012
ሶሎሞን በየነ