አዲስ አበባ፡- የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ፍሬወይኒ መብርሀቱ በዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙሀን CNN የ2019 ዓመት ጀግና በሚል እንድትመረጥ ድምፅ የሰጡ ኢትዮጵያውያንን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቷ ትናንት ምሽት ተሸላሚዋን በቤተመ ንግስት ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ከፍሬወይኒ ጥረት ጀርባ ሥራዋ እውቅና እንዲያገኝና ለሽልማት እንድትበቃ ድምፅ በመስጠቱ በኩል ኢትዮጵያውያን ትልቁን ድርሻ ወስደዋል፤ በዚህም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ሽልማቱ ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር ስለሆነ ከዚህ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብና ሴት ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ ለማድረግ ተሸላሚዋ ጠንክራ እንድትሰራ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ያሳሰቡ ሲሆን ፣ለዚህ የመንግሥት ድጋፍ እንደማይለያት አረጋግጠዋል፡፡
ወይዘሮ ፍሬወይኒ በበኩሏ በፕሬዚዳንቷ በተደረገላት አቀባበል መደሰቷን በመግለፅ ክብሩ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ሴቶች እንደሆነ ተናግራለች፡፡ በሽልማቱ ያገኘችውን መነሳሳትም ሰፊ ሥራዎችን በመስራት እንደምታስቀጥል እና በዘርፉ በርካታ የሥራ እድል የመፍጠር ውጥን እንዳላት ገልፃለች፡፡
ወይዘሮ ፍሬወይኒ በሴቶች የወር አበባ ወቅት ተገቢው የንፅሕና መጠበቂያ በማይገኝባት ኢትዮጵያ ዳግም አገልግሎት መስጠት የሚችል የወር አበባ መቀበያ አዘጋጅታ ለተማሪዎች እንዲዳረስ ማስቻሏ ለሽልማት እንዳበቃት ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2012
ድልነሳ ምንውየለት