. የኪራይ ቤቶች የዋጋ ማሻሻያ ላይ ጥሎት ከነበረው መጠን ቅናሽ አደረገ፤
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በየጊዜው የሚደረጉ የኪራይ ተመን ማሻሻያዎችን ተከትሎ የሚነሱ ውዝግቦችን ለማቃለል እንዲቻል የኪራይ ውል ክለሳ ጊዜ ገደብ ሊያስቀምጥ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል ተናገሩ፡፡
ኮርፖሬሽኑ በቅርቡ ባለደረገው የንግድ ቤቶች ኪራይ ተመንን ተከትሎ ከተከራይ የቀረቡለትን ቅሬታዎችም በጥልቀት በመገምገም ተገቢ ምላሽ መስጠቱንና የዋጋ ቅናሽ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡
እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ ኮርፖሬሽኑ ያሉት ቤቶች በጣም ውስን ናቸው፡፡ ስልሆነም በአነስተኛና ጥቃቅን እንደሚደረገው ለአምስት ወይም ለሶስት ዓመት ተጠቅመው ለሌሎች ተራ እንዲለቅቁ መደረግ ነበረበት፡፡ ነገር ግን ይሄ እስካሁን ተግባራዊ ባለመደረጉ አንድ ሰው የተከራየውን ቤት እስከ አርባ አመት እንዲጠቀምባቸው ሆኗል፡፡ በየጊዜው ኮርፖሬሽኑ ለሚያከናውናቸው ተግባራትም እንቅፋት ሆኗል፤ በቅርቡ ባደረገው የዋጋ ማሻሻያ የታየውም ይሄንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ይልቁንም ተከራዮችን ወደ መዘናጋትና ቤቱ የእኛ ነው ወደማለት አድርሷቸዋል፡፡
የኪራይ ጊዜ ገደብ ባለመተግበሩ ተቋሙ በራሱ ሰንፎ ተከራዮችን አስንፏቸዋል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ በቀጣይ ይሄን ችግር ለመፍታት እንደሚሰራና በየሶስት ዓመቱ የውል ክለሳ እንዲደረግ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ኮርፖሬሽኑ ያደረገውን የዋጋ ማሻሻያ ተከትሎ ለተነሱ ቅሬታዎች ምላሽ ሲሰጥ ያስቀመጠው የሶስት ዓመት የእፎይታን ጊዜ ከግምት ያስገባ ሲሆን፤ ይህ የእፎይታ ጊዜ ሲጠናቀቅና ከፍለው ሲደርሱ ግን በየሦስት ዓመቱ የኪራይ ውል እንዲከለስ ይደረጋል፡፡
በቅርቡ የተደረገውን የዋጋ ማሻሻያ ተከትሎ ለቀረበው ቅሬታም ተገቢውን ምላሽ የሰጠ መሆኑንና፤ በዚህም የሶስት ዓመት የእፎይታ ጊዜ ከመስጠት ጀምሮ እንደየኪራይ ቤቶቹ ባህሪ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉት ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የገለጹት፡፡ በዚህም የንግድ ቤቶች አሁን በሚከፍሉት ላይ በመጀመሪያው ዓመት 35 በመቶ ጨምረው እንዲከፍሉ፤ በሁለተኛው ዓመት ደግሞ 70 በመቶ እንዲደርሱና በሥስተኛው ዓመት 100 በመቶ እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡
አቶ ረሻድ እንደገለጹትም፤ የትግበራ ጊዜውም ለአንድ ወር ተራዝሞ የካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም እንጂጀምር ሆኗል፡፡ የንግድ ያልሆኑ ቤቶች በካሬ ከ339 ብር ወደ 140፣ እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ ለተከራዩ በካሬ ከ92 ዶላር ወደ 59 ዶላር እንዲቀንስ ተወስኗል፡፡
በወንደሰን ሽመልስ