ሱዳን ባለፉት ሁለት ሳምንታት በህዝባዊ ተቃውሞ እየተናጠች ነው፡፡ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኡመር ሀሰን አልበሽር በተያዘው የፈረንጆች አዲስ ዓመት ሀገራቸው ምጣኔ ሃብታዊ እድገት እንደምታስመዘግብና የዜጎች የቁጣ ምንጭ የሆነው የመሰረታዊ ሸቀጥ ዋጋ እንደሚረጋጋ ቃል ገብተዋል፡፡
አልጀዚራ ከካርቱም እንደዘገበው ፕሬዚዳንቱ ሱዳን ከቅኝ ግዛት ነጻ የወጣችበትን 63ኛ ዓመት በዓልን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር፤ የ2019 በጀት መጽደቁንና በጀቱም አሁን ሀገሪቱ ከገባችበት ቀውስ እንድትወጣ እገዛ በሚያደርግ መልኩ ጥቅም ላይ እንደሚውል ገልጸዋል፡፡ በጀቱ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ለዘለቀው የህዝቡ ቁጣ ምንጭ የሆነው የመሰረታዊ ሸቀጦች እጥረትና የዋጋ መናር ችግርን በመፍታት ሀገሪቷ አሁን ከገባችበት ቀውስ እንድትወጣ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
መንግስታቸው የዜጎችን የመሰረታዊ ሸቀጥ እጥረትና የዋጋ መናር ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል፡፡ ከሚወሰዱ እርምጃዎች መካከልም የመሰረታዊ ሸቀጦች አቀርቦትን መደጎም፤ የደመወዝ ጭማሪና ዜጎች ግብር እንዳይከፍሉ ማድረግ ዋነኞቹ መሆኑን አንስተዋል፡፡ እቅዳቸውን እውን ለማድረግም ከቻይና፣ ከሩሲያና ከባህረ ሰላጤ ሀገራት ጋር የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ወዳጅነት ለማጠናከር የሚያስችል ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ አክለው እንደገለጹት፤ ሱዳናዊያን የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነታቸውን ወደጎን በማድረግ አሁን ሀገሪቱ ውስጥ እየታየ ያለውን ቀውስ ለመፍታት በጋራ ሊቆሙ ይገባል፡፡ ለዚህም ወደ ውይይት መምጣት አለባቸው፡፡
ምንም እንኳ ፕሬዚዳንቱ ሱዳናዊያን አሁን የያዙትን የአመጽ መንገድ ትተው ወደ ውይይት መምጣት አለባቸው ቢሉም፤ በሀገሪቱ እየታየ ያለውን ተቃውሞ የሚመራው አካል የማይታወቅ መሆኑ ፕሬዚዳንት አልበሽር ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚደርጉትን ጥረት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ተንታኞች እየተናገሩ ነው፡፡
የሀገሪቱ የጸጥታ ሀይል በዋና ከተማዋ ካርቱም እና በሌሎች ከተሞች ውስጥ ፕሬዚዳንቱን ለመቃወም በወጡ ዜጎች ላይ የሀይል እርምጃ በመውሰድ የግድያና የአካል መጉደል ጉዳት ማድረሱን ቀጥሎበታል፡፡ የጸጥታ ሀይሎች የሀይል እርምጃ ያልበገራቸው ለተቃውሞ የወጡ ዜጎች በበኩላቸው ፕሬዚዳንቱ ላለፉት 29 ዓመታት ዜጎች ለተቃውሞ ሲወጡ ቃል ሲገቡ መቆየታቸውንና አንድም ጊዜ በገቡት ቃል መሰረት የዜጎችን የኑሮ ውድነት ችግር የሚቀርፍ እርምጃ ወስደው እንደማያውቁ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ በመሆኑም ኡመር ሀሰን አልበሽር ከስልጣናቸው እንዲወርዱና ሁሉንም የፖለቲካ ሀይሎች የሚያሳትፍ ምርጫ እስኪካሄድ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም እየጠየቁ ነው፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት በመሰረታዊ ሸቀጦች እጥረትና የዋጋ መናር ምክንያት የተቀሰቀሰው የሱዳናዊያን ቁጣ ፖለቲካዊ መልክ እየያዘ መምጣቱ ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2011
መላኩ ኤሮሴ