ዘወትር እሁድ ከማለዳው ጀምሮ እስከ ቀኑ ስምንት ሰዓት ድረስ በአዲስ አበባ፣ አዲስ ከተማ ክፍለከተማ ጎጃም በረንዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተገኘ ሰው የወጣቶችን በጎ ተግባር መመልከት ይችላል::ወጣቶቹ ጎዳና የሚኖሩና የአዕምሮ ህመምተኞችን ገላ አጥበው፣ ጥፍር ቆርጠው፣ ፀጉራቸውን ሰርተው ልብስ ያለብሷቸዋል፤ ይመግቧቸዋልም::የዘመመች ጎጆንም በማቃናትም ይታወቃሉ::
በበዓላትና በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ተመሳሳይ አልባሳትን በማሰራት አብሮነታቸውን እያጎለበቱ የመጡት እነዚህ ወጣቶች ግንቦት 12 ቀን 2010ዓ.ም የአንድነታቸውንና የፍቅራቸውን ጥግ በሌላ የበጎ ሥራ ውስጥ ለማሳለፍ በተስማሙት መሰረት ነው ስራቸውን የጀመሩት::
በዚህም በቅድሚያ መኖሪያቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ሁለት ግለሰቦችን ገላ በማጠብና ልብስ በመቀየር የበጎ አድራጎት ስራቸውን ጀመሩ::ዛሬ ላይ ሥራቸውን አስፋፍተው በየሳምንቱ ቢያንስ 200 ለሚሆኑ አቅመ ደካሞችና የጎዳና ተዳዳሪዎች አገልግሎት በመስጠት የሰብዓዊነትን ጥግ እያሳዩ ይገኛሉ::
እመቤት አለባቸው የራሷ የግል ቤት የሌላትና የምትኖረውም በደባል ሲሆን፤ በዚህ ቤት ውስጥ እንደ ልብ ውሃ ማግኘትና ንጽህናዋን ለመጠበቅ አያስችላትም::በመሆኑም ልጇን በጀርባዋ አዝላ ከፈረንሳይ ለጋሲዮን ጎጃም በረንዳ በመገኘት ፍቅር ነደያን የበጎ አድራጎት ድርጅት የሚሰጠውን አገልግሎት ተጠቃሚ ናት::
ድርጅቱ ሥራ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ልብስ ለማግኘትና ንጽህናዋን ለመጠበቅ በ15 ቀን እንድ ጊዜ ትመጣለች::በምታገኘው አገልግሎትም እርካታ ይሰማታል::አገልግሎት ሰጪ ወጣቶቹ ሳይሰለቹ ይህንን ሁሉ ሰው ማስተናገድ መቻላቸውን በማድነቅ ፍረቅራቸውና ትጋታቸው ለሌሎች የከተማዋ ወጣቶች ምሳሌ መሆኑን ጠቅሳለች::
መርካቶ ጎጃም በረንዳ አካባቢ ነዋሪ የሆነችው ወይዘሮ በለጡ ሀይሌ የልጆቿ አባት ጥሏት ሲጠፋ ሰውጋ ተጠግታ ብትኖርም ዘላቂ ኑሮ ሊሆንላት አልቻለም:: የሰው ልብስ እያጠበች ኑሮዋን ለመግፋት ብትሰራም የምታገኘው ብር የእለት ጉርሷን መሸፈን አልቻለም::በመጨረሻም ከነ ልጆቿ ወደ ጎዳና ህይወት ወጣች::
በአሁኑ ወቅት ግን የፍቅር ለነዳያን በጎ አድራጎት ወጣቶች ባደረጉላት ድጋፍ ልጆቿንና ራሷን ከማስተዳደር አልፋ የቤት ሰራተኛ ቀጥራ ደስተኛ ኑሮን እየመራች ትገኛለች:: የተደረገላት ሁሉ በህይወቷ ውስጥ ተስፋን ሰንቃ ወደፊት እንድትራመድ ረድቷታል::በዚህም የእነርሱን ፈለግ ተከትላ በዚህ የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ለመሰማራት ቁርጠኛ መሆኗን ትናገራለች::
ወይዘሮ አስናቀች አለሙ ከዚህ ቀደም ይኖሩበት የነበረው ቤት ለመኖሪያነት አመቺ ያልነበረና ውስጡ አላስፈላጊ በሆኑ ቁሶች የታጨቀ እንደነበር ገልጸው፤ አሁን ላይ የአካባቢው ወጣቶች ተረባርበው ለእርሳቸው ምቹ በሆነ መልኩ ቤቱን በማደሳቸው ደስታቸው ወደር የለውም::ቤቱን ለማሳደስም ሆነ ለማጽዳት ምንም ቅሪት ያልነበራቸው ወይዘሮ አስናቀች፤ ለዘመናት የዘመመችው ጎጆአቸውም ተቃንታ በማየታቸውም ለወጣቶቹ ምስጋናቸውን አቅርበዋል::
የዚሁ በጎ ተግባር ተቋዳሽ የሆኑት መቶ አለቃ አሰፋ ተክሉ እድሜያቸው 65 ዓመት ሲሆን፤ የሚረዳቸው ልጅም ሆነ ዘመድ የላቸውም::ካገኙ አልጋ ተከራይተው ካላገኙ ደግሞ በጎዳና ላይ ያድራሉ::
ምንም እንኳን ኑሯቸው አሁንም የተደላደለ ባይሆንም በየሳምንቱንጽህናቸው ይጠበቅላቸዋል:: ልብስም ያገኛሉ:: ጸጉራቸውን ይስተካከላሉ:: የፍቅር ለነዳያን በጎ አድራጎት ወጣቶች እንደ ልጅ እየተንከባከቧቸው ነው::በዚህ ደስተኛ መሆናቸውን የሚናገሩት መቶ አለቃ አሰፋ ወጣቶቹን መንግስት መደገፍ እንዳለበትና ተቋሙ የሚያድግበት ሁኔታ መመቻቸት እንዳለበትም ይናገራሉ::
የፍቅር ለነዲያን በጎ አድራጎት ተቋም መስራች ወጣት ኪሮስ በላይ፤ ድርጅቱ የተመሰረተው፤የግለሰቦችን ንጽህና ለመጠበቅ ታስቦ ሲሆን ፤ በአሁን ወቅት የአረጋውያንና የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፣የታመሙ ሰዎችን የቤት ለቤት እንክብካቤ ማድረግና መሰል ተግባራትን ጨምሮ አቅም የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን እየረዳ መሆኑን ይናገራል::
እንደ ወጣት ኪሮስ ማብራሪያ ወጣቶቹ ከህብረተሰቡ በሚያገኙት ድጋፍ፤ ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ቤት የማደስ ሥራ እንዲሁም ዘወትር እሁድ የንጽህና አገልግሎት ይሰጣሉ::እስካሁንም በላስቲክ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ህጻናትን በትምህርት ማገዝ ችለዋል:: ቤት ውስጥ ሆነው መለመን ፈርተው ያሉትን አቅመ ደካሞችና ታማሚዎችን ቤት ከማደስ ጀምሮ የሚያስፈልጋቸውን ነገር አቅም በፈቀደ ልክ አሟልተዋል::
በመኪና አደጋ ተጎድተው እግርና እጃቸው መንቀሳቀስ የማይችሉ እንዲሁም ማየትም መስማትም የተሰናቸው ሰዎች እንደሚያጋጥሟቸውና ይህ ደግሞ በድርጅቱ አቅም ብቻ የሚቻል ስላልሆነ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ወጣት ኪሮስ ጥሪ አቅርቧል::
የበጎ አድራጎቱ ተሳታፊ ወጣት ስማቸው ይታየው እንደሚለው፤ ብዙዎች በነጻ ለማገልገል ፍቃደኛ ይሆኑና ሥራው ከበድ ሲላቸው ጥለዋቸው ይሄዳሉ::የቁርጠኝነት ችግር ይታያል::ሙሉ ተሳትፎ የማድረግ ፍላጎት ይዳከማል::በአካባቢው ለመረዳት ከሚመጡት ነዳያን ቁጥር አንጻር ሥራው በርካታ የሰው ሀይል ስለሚፈልግ በርካታ በጎ ፈቃደኞች ያስፈልጋሉ::በመሆኑም ማንኛውም በጎ ፈቃደኛ ወጣት ድጋፉን በተለያየ መልኩ በመስጠት ድርጅቱን እንዲያግዝ ጠይቋል::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2012
አዲሱ ገረመው