ባሌ ሮቤ፦ የሰብል ማጨጂያና መውቂያ ማሽን/ኮምባይነር/ እጥረት ምርትን በወቅቱ ለመሰብሰብ ስጋት እንደፈጠረባቸው በኦሮሚያ ክልል የባሌ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ::
የባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ አርሶ አደሮች ሰሞኑን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በአካባቢያቸው በኮምባይነር ሰብልን ማጨድና መውቃት የተለመደ ነው:: ይሁን እንጂ በዘንድሮ የምርት ዘመን የኮምባይነር አቅርቦት እጥረት በማጋጠሙ ምርታቸውን በወቅቱ ሰብስበው ለማስገባት ሥጋት ፈጥሮባቸዋል::
የኮምባይነር ተጠቃሚ ከሆኑት አንዱ አርሶ አደር አብዱል ሀኪም አማን እንደገለጹት፤ የሲናና ግብርና ማዕከልና የአጋርፋ ወረዳ ግብርና ቢሮ በሚያደርጉላቸው እገዛ በየጊዜ የግብርናቸው አሰራር ዘምኗል:: ምርታቸውም ጨምሯል:: የዘንድሮው ምርታቸው ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥሩ እንደሆነ ይገልጻሉ:: ነገር ግን ባጋጠመው የኮምባይነር አቅርቦት እጥረት ሰብላቸውን በወቅቱ መሰብሰብ እንዳልቻሉ አመልክተዋል:: ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የማጨጂያና መውቂያ ማሽኖችን እንዲያቀርቡላቸው ጠይቀዋል::
የአጋርፋ ወረዳ ግብርና ኤክስቴንሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ አማን አብዱል ቃዲር እንዳስረዱት፤ በሰብል መሰብሰብ ወቅት ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ኮባይነሮችን በማስመጣት ምርት የመሰብሰቡ ሂደት ይከናወን ነበር:: በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተው የሰላም ችግር ኮባይነሮችን ወደ አካባቢው ማምጣት አላስቻለም:: ችግሩን ለመፍታትም ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል::
የአካባቢው አርሶ አደሮች የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል በሚያደርገው ድጋፍ ምርታማነታቸው መጨመሩንና በምርት ዘመኑም አብዛኛው መሬት በተለያዩ የስንዴ ሰብሎች መሸፈኑን የጠቆሙት አቶ አማን፣ የኮምባይነር እጥረት ሰብሉን በወቅቱ ሰብስቦ ምርት ለማስገባት እንቅፋት እንደሆነ ገልጸዋል:: ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ አካላት ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል::
በባሌ ዞን የአጋርፋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሶፊያን ተማም የአካባቢው አርሶ አደሮች በትራክተር የማረስ እና በኮምባይነር የማሳጨድ ልምዳቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በምርት ዘመኑ የሰብል ማጨጂያና መውቂያ ኮምባይነር ማግኘት የተቻለው ጥቂት ብቻ መሆኑን አመልክተዋል:: ችግሩን ለመፍታት ከተለያዩ አካላት ጋር በሚደረጉ ምክክሮች በተያዘው ወር አቅርቦቱን ለማስተካከል ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል::
የአጋርፋ ወረዳ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚመረትበት አካባቢ ሲሆን በመኸር ወቅቱም አንድ ሺ 28 ሄክታር መሬት በሰብል እንደተሸፈነ እና ከዚህም አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ሶፊያን ገልጸዋል::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2012
ኢያሱ መሰለ