– በነባሩ አዋጅ 80 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመዝገበዋል
አዲስ አበባ፡- የተሻሻለው የምርጫ ቦርድ አዋጅ የሚጠይቀውን መስፈርት አሟልቶ ለመመዝገብ የቀረበ ፓርቲ አለመኖሩን ምርጫ ቦርድ ገለጸ :: በቀድሞው አዋጅ እስካሁን 80 የፖለቲካ ፓርቲዎች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ ::
የቦርዱ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ አዲስ የሚያመለክቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊስተናገዱ የሚችሉት በተሻሻለው የምርጫ ቦርድ አዋጅ ቁጥር 1162 መሰረት ነው:: ይህ አዋጅ የሚጠይቀውን አሟልቶ ለመመዝገብ የቀረበ ፓርቲ ግን የለም::
በተሻሻለው የምርጫ ቦርድ አዋጅ 1162 ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመመዝገብ ለሃገር አቀፍ ፓርቲ 10 ሺ የድጋፍ ፊርማ ፣ ለክልላዊ ፓርቲነት ደግሞ 4 ሺ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ እንደሚጠበቅባቸው አብራርተዋል ::
እንደ ወይዘሪት ሶሊያና ገለጻ ፤የፖለቲካ ፓርቲዎቹም በአዋጅ 1162 ላይ በተቀመጠው መሰረት ወደ ቦርዱ የፖለቲካ ክፍል በመምጣት የስራ ክፍሉ አስፈላጊ የሆኑ ጥያቄዎችን ካቀረበላቸው በኋላ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ በዝርዝር ይነግራቸዋል:: ቴክኒካዊ ድጋፍ ከሰጣቸው በኋላም እያንዳንዱን ሂደት አልፈው እንዲመዘገቡ ይደረጋል::
እንደ ወይዘሪት ሶሊያና ገለጻ፤ በነባሩ አዋጅ ቀደም ሲል 69 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመዝግበዋል፤ ከዚያ ወዲህ ደግሞ በቅርቡ የተመዘገቡትን ሁለት ፓርቲዎች ጨምሮ 11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ተካሂዷል:: በአጠቃላይ ከተመዘገቡት ፓርቲዎች ውስጥ በሀገር አቀፍ ፓርቲነት የተመዘገቡት 26 ሲሆኑ፣54ቱ ደግሞ በክልል ፓርቲነት የተመዘገቡ ናቸው::
የተመዘገቡት በሙሉ በቀድሞው አዋጅ 537 መሰረት ለመመዝገብ የቀረቡ መሆናቸውን ወይዘሪት ሶሊያና ጠቅሰው፤በዚሁ አዋጅ መሰረት ለመመዝገብ አመልክተው ሰርተፍኬት እየተጠባበቁ የሚገኙ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉም ገልጸዋል:: ቀደም ሲል በነባሩ አዋጅ መሰረት ለምዝገባ ወረቀት አስገብተው በሂደት ላይ ሆነው ሲጠብቁ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ በአዲሱ ህግ ወደኋላ ተመልሶ እንደማይታይ ተናግረዋል::
ከምዝገባ ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ችግሮች አሉ ወይ? ካሉስ እንዴት እየፈታችኋቸው ነው? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አማካሪዋ ፤ ‹‹እኛ ችግር አላጋጠመንም፤እንደሚመስለኝ ችግር አጋጥሞናል ካሉ ይህን መጠየቅ ያለባቸው ፓርቲዎቹ ናቸው፡፡›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል::ለምዝገባ የተቀመጠ የጊዜ ገደብ አለመኖሩንና ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በፈለገው ጊዜ መመዝገብ እንደሚችል አስታውቀዋል::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2012
አስናቀ ፀጋዬ