አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት (ኢ.ኢ.ግ.ል.ድ) በጨው አቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ መግባቱ የግብይት ሰንሰለቱን በማራዘም በኢንዱስትሪዎችና በጨው አቅራቢዎች ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ::ኢ.ኢ.ግ.ል.ድ በበኩሉ በመንግሥት በተሰጠው ተልዕኮ መሰረት ገበያውን ለማረጋጋትና ኢንዱስትሪዎችን ለማገዝ በጨው አቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ መግባቱን ጠቁሟል::
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅትን የአምስት ወራት አፈጻጸም ትናንት በገመገመበት ወቅት እንደገለጸው፤ የጨው ምርት እጥረት በሌለበት ሁኔታ በመደበኛ የግብይት ስርዓት ጨው ለኢንዱስትሪዎች ተደራሽ ማድረግ እየተቻለ ድርጅቱ ግብይት ውስጥ መግባቱ ሰንሰለቱን እያራዘመው ነው::
በሀገሪቱ ከፍተኛ የጨው ምርት መኖሩን የገለጹት የቋሚ ኮሚቴው አባላት ድርጅቱ በእሴት ሰንሰለቱ ውስጥ በመግባቱ ምክንያት በአንድ በኩል የጨው አምራቾች ያመረቱትን ተረካቢ አጥተው በመጠባበቅ ላይ ሲሆኑ፣ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ጨው አጥተው እየተቸገሩ ናቸው ብለዋል::
ተቋሙ ከአምራቾች ጨው በሚገዛበት ወቅትም አድሏዊነት እንዳለበት የተናገሩት የቋሚ ኮሚቴው አባላት፤ ከአንዳንዶቹ ጨው እየገዛ ከሌሎቹ ያለመግዛት ችግር መኖሩን ተናግረዋል:: በዚህም ምክንያት ጨው አምራቾች ዘንድ ቅሬታ መፈጠሩን ገልጸዋል:: ድርጅቱ የሚገዛም ከሆነ ከአድሏዊ አሠራር በጸዳ መልኩ ግዢ መፈጸም እንዳለበት አባላቱ ጠቁመዋል::
እንደ ቋሚ ኮሚቴው አባላት ገለጻ፤ ድርጅቱ በመሃል በመግባቱ የጨው ዋጋ እንዲንር እያደረገ ነው::በተጋነነ ዋጋ እየሸጠ መሆኑን በደረሰኝ አስደግፈው ቅሬታ ያቀረቡም አሉ:: የኢንዱስትሪ ጨው ለምግብ እየቀረበ ስለመሆኑም ጥቆማዎች ደርሰዋል::
የተቋሙ ኮርፖሬት ሰርቪስ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደጀኔ ገ/ማሪያም በበኩላቸው፤ድርጅቱ የሚሸጠውም ሆነ የሚገዘው በንግድ ሚኒስቴር በተተመነ ዋጋ መሆኑን ጠቁመው፣በተጋነነ ዋጋ ይሸጣል በሚል የሚቀርበው ክስ ሀሰት እንደሆነ ገልጸዋል::ገበያውን ለማረጋጋት በመንግሥት በተሰጠው ተልዕኮ መሰረት በተመጣጣኝ ዋጋ ለኢንዱስትሪዎች ጨው እንደሚያቀርብ አመልክተዋል::
“የኢንዱስትሪ ጨው ለምግብ እየቀረበ ነው የሚለውም ተራ ስም የማጥፋት ዘመቻ ነው” ያሉት አቶ ደጀኔ፣ ምርቱን ለምግብ ፍጆታ ለማቅረብ ቀርቶ ለኢንዱስትሪዎችም በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል::ከአምራቾች እንደተረከበ መጋዘን ሳይገባ ለኢንዱስትሪዎች እንደሚያቀርብ ገልጸዋል::
ችግሩን ለመቅረፍ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየተሠራ መሆኑን የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንዳለ ሀብታሙ አስታውቀዋል::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2012
መላኩ ኤሮሴ