አዲስ አበባ፡- የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ህዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም የኖቤል የሰላም ሽልማትን በኦስሎ ተገኝተው መቀበላቸውና በመድረኩ ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ዘገባዎቻቸውን ሰርተዋል፡፡
‘‘የኖቤል ሽልማት አሸናፊው ሰላም የፍቅር ውጤት ነው’’ አሉ ሲል በፊት ገፁ ያስነበበው ቢቢሲ፣ በዘገባው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላምን ዘላቂ ማድረግ ከባድ ሥራ ነው፤ ጦርነትን ለመዋጋት ጥቂት ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም ሰላምን ለመገንባት ግን ህዝብ እና መንደርን በፍቅር ማስተሳሰር ይጠይቃል” ሲሉ በሽልማቱ ወቅት መናገራቸውን አትቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ምንጭ ጠቅሰው “የጥላቻ እና የመከፋፈል ሰባኪዎች ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በህብረተሰባችን ላይ ከፍተኛ ውድቀት እያደረሱ ነው’’ ሲሉ በንግግራቸው ውስጥ ማካተታቸውን ጨምሮ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ ድምፅ የአማርኛው አገልግሎት በበኩሉ ‘’ኢትዮጵያ በኖቤል የሰላም ኮሚቴ ሊቀመንበር ተወደሰች’’ ብሎ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከተበረከተላቸው የዓለም የሰላም የኖቤል ሽልማት በተጨማሪ ከኮሚቴው ከፍተኛ ሙገሳና ምስጋና ተቸሯቸዋል ሲል ዘግቧል።
በሽልማት ሥነ- ሥርዓቱ ላይ ንግግር አድርገው ሽልማቱን ያበረከቱላቸው የኖቤል የሰላም ኮሚቴ ሊቀመንበር ቤሪት ሬይሳ አንደርሰን፤ በንግግራቸው ኢትዮጵያን አወድሰዋል ያለው ቪኦኤ፤ “ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ከመሆኗ አንፃርም ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን” በማለት አዳራሹን በጭብጨባ እንዳስደመቁት ገልጿል፡፡
ሊቀመንበሯ ኢትዮጵያ በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ያልወደቀች አገርም እንደሆነች ተናግረው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስልጣን በያዙ በ100 ቀናት ውስጥ ብዙ ለውጦችን በአገር ውስጥ ማስመዝገባቸውን በመናገር፤ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ከመመለስ ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚጠብቁ ብዙ ሥራዎች እንዳሉም መጠቆማቸውን ቪኦኤ በዘገባው አካቶ አቅርቧል፡፡
‘‘ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት ሜዳሊያን ሲቀበሉ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ አቀረቡ’’ ሲል በአርእስተ ዜናው ያስነበበው ሲኤንኤን፤ ብዙ የምዕራባውያን ኃይሎች ወታደራዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን ሲያሰፉ እና አሸባሪ ቡድኖች በቀጣናው ውስጥ የእራሳቸውን አቋም ለመመስረት ሲሞክሩ ቀጣናው “የጦር ሜዳ” አለመሆኑን ማሳወቅ አስፈላጊ ነው ማለታቸውን አስነብቧል፡፡
የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ሊቀመንበር ቤሪት ሬይስ አንደርሰን ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ መሠረታዊ የፖለቲካ ማሻሻያዎችን በመተግበሩ ረገድ ባስመዘገቡት ውጤት ምስጋናቸውን እንዳቀረቡ የዘገበው ሲኤንኤን፤ ይህም በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን ነፃ በማውጣት እና በካቢኔያቸው ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ሴቶችን መሾምን ጨምሮ ሌሎች አበረታች ሥራዎችን መስራታቸውን በመድረኩ ስለመናገራቸው ገልጿል፡፡
‘‘ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኢትዮ ኤርትራ ወደ ሰላም መምጣት ዋናው መሃንዲስ ተብለው ተሞግሰዋል።’’ ብሎ ዘገባውን የጀመረው የጀርመን ድምፅ ሬዲዮ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱን የአፍሪቃ ህዝቦችና የዓለም ህዝቦችን ወክዬ ነው የምቀበለው ሲሉ ባሰሙት ንግግር ለኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሰላም ቁርጠኝነት ወሳኝ እንደነበር አለመሸሸጋቸውንም ገልጿል።
ከ20 ዓመታት በፊት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የሬድዮ ኦፕሬተር እንደነበሩ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ የሁለቱ አገራት ጠብ መቆም እንዳለበት መወሰናቸውንና ከ 18 ወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሆኑ በኢትዮጵያና ኤርትራ ያለውን ውጥረት መለወጥ አስፈላጊ መሆኑ ስለተሰማቸውና በሀገራቱ መካከል ያለው ሰላም እሩቅ እንዳልሆነ በማመን ከአጋራቸው ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የሰላም ድልድይን መገንባት እንደጀመሩ ስለመናገራቸው በዘገባው አስፍሯል፡፡
መደመር አገር በቀል ሀሳብና በጋራ ብልጽግና ላይ ያተኮረ ፍልስፍና ስለመሆኑና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በመደመር ጽንሰ ሃሳብ ‹‹እኛና እነሱ›› የሚባል ነገር የለም ሲሉ በኖቤል ሽልማት ሥነ ስርዓት ላይ የነበረውን ተጋባዥ እንግዳ አስደምመዋል ሲልም የጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ዘግቧል፡፡
የኬንያው ዴይሊ ኔሽን ‘‘አብይ የኖቤል የሰላም ሽልማት ተቀበለ’’ በሚል አርዕስት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያመጡትን ሰላም በማንሳት ፅፏል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ1998-2000 የነበረውን የድንበር ግጭት ተከትሎ በደረሰው ጥፋት የተጎዱት ሁለቱ ሀገሮች እንደነበሩና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እ.ኤ.አ. ሐምሌ 9 ቀን 2018 በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ባደረጉት ታሪካዊ ስብሰባ ሰላም መውረዱን ነው ዴይሊ ኔሽን ያስነበበው፡፡
ለሁለት አሥርት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደስልጣን ከወጡ ከሦስት ወር በኋላ ዳግም ወደነበረበት መመለስ መቻሉንም ዴይሊ ኔሽን በዘገባው አካቶ አውጥቷል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 2/2012
ድልነሳ ምንውየለት