አዲስ አበባ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከትናንት በስቲያ የተቀበሉት የሰላም የኖቤል ሽልማት ብዙ ኃላፊነቶችን ለመሸከም አቅም የሚፈጥር መሆኑ ተገለጸ፡፡
አስተያየታቸውን ለአዲስ ዘመን የሠጡት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የሽልማት ሥነሥርዓቱ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ሀገራዊ ስሜትን የፈጠረ መሆኑን ገልጸው፣ይበልጥ ለመስራት ኃላፊነት የሚያሸክምና አቅም የሚፈጥር መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማትና በሥነ ሥርዓቱ ዙሪያ አስተያየታቸውን ከሰጡን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አርበኛ መሪጌታ አምዴ ወልደጻዲቅ፤ ‹‹ሽልማቱ ታሪክ ነው፡፡ የእኛም የሀገርም ሽልማት ነው፡፡ ይሄን የምለው መሪዎች ያለ ህዝብ ድጋፍ የትም መድረስ ስለማይችሉ ነው፡፡
በብዙዎች ድጋፍ ነው ለውጤት የበቁት›› ይላሉ፡፡ ሽልማቱ ብዙ ኃላፊ ነቶችንም ለመሸከም አቅም የሚፈጥር እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
የሽልማት ኮሚቴውም ለሽልማት ሲያጫቸው ትክክለኛ መሪ መሆናቸውን አይቶ እንደሆነ የሚናገሩት አርበኛ መሪጌታ
አምዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገር ውስጥም በሰላም ዙሪያ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ተሸልመው ለመከላከያ ሚኒስትሩ ለማ
መገርሳ መልሰው መሸለማቸውን አስታውሰው፣ ይሄም ወድማማችነትን ፍቅርንና አንድ ጽዋ መጠጣትን እንደሚያሳይ
ተናግረዋል።
ሽልማቱን እያንዳንዱ ዜጋ በተለይም ወጣቱ በቀላሉ ሊያየው እንደማይገባና ለሰላም ዋጋ እንዲሰጥ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
‹‹የራስ ሀገር ዜጋ ትልቅ ለሆነ የክብር ሽልማት ሲበቃ ደስ የማይለው ሰው ቢኖር እጅግ በጣም ጥቂት ነው ።እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ደስ ብሎኛል››ያሉት ደግሞ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ናቸው።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የነበረው ክብርና ዝና የሚያመጣውን ኃላፊነት መሸከም ከባድ እንደሆነ ጠቅሰው፣ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጫዊ ሰላም ያደረጉትን ሀገር ውስጥ ያለውን ሰላም ከፍ በማድረግ፣ የህዝቦች ወድማማችነት እንዲጠናከር፣ ሰው በነፃነት ወጥቶ እንዲገባ፣ የህግ የበላይነት እንዲከበር በማድረግ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ከጎረቤት ሀገራትና ከሌላው አልምም ጋር መልካም ግንኙነት ማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም አሁን በሀገር ውስጥ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አስተማማኝ የሆነ ዘላቂ ሰላም እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አቶ በቀለ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱ ያሸከማቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ፈጣሪ ይርዳቸው ሲሉም መልካም ተመኝተውላቸዋል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር በሽልማት ሥነሥርዓቱ ላይ በራስ መተማመንና በብቃት ያደረጉት ንግግር መልዕክት ስቧቸው እንደተከታተሉት ይናገራሉ።ሀገርንም የሚያኮራ መልዕክት አስተላልፈዋል ብለውም ያምናሉ።
ሽልማቱ በኢትዮጵያና በኤርትራ ሀገራት መካከል የነበረውን ችግር
በመፍታታቸው ብቻ ሳይሆን፣በሌሎችም አስተዋጽኦዎች ጭምር እንደሆነ ይናገራሉ።ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ባለሙያዎችና መሪዎች
አንዱ መሆናቸውና ሽልማቱም በዘፈቀደ
የተሰጠ እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊያዝ እንደሚገባ ገልጸዋል።ስሙ እንዲህ ገኖ ሲወጣ የማያስደስተው ኢትዮጵያዊ ሊኖር አይገባም ብለዋል።
ይሁን እንጂ አሉ ፕሮፌሰሩ ፤በሁለቱ ሀገራት ሰላም ቢሰፍንም በሰነድ የተደገፈ ስምምነት አለመኖሩ ወደፊት የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው፣ህዝብን ይዘው ሀገርን ማረጋጋት፣ዜጎች በሀገራቸው እንዳይፈናቀሉ እነዚህንና ሌሎችንም ተግባራት ለማከናወን ሽልማቱ የሞራል ግንባታ እንደሚሆንላቸው አመልክተዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ወይዘሮ ስፍራሽ ብርሃኔ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሸለሙት የሰላም ኖቤል ሽልማት የኢትዮጵያን ታሪክ ከፍ ያደረገበት እንደሆነ ጠቁመው፣ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗ ‹‹እኛም ኢትዮጵያዊ ነን›› የሚል ስሜት መፍጠሩ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።ይህ ደግሞ ለመላው ኢትዮጵያዊ ኩራት ሊሆን ይገባዋል ብለዋል።
ህዝቡም ይህን ተገንዝቦ ሽልማቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እውነት ይገባቸዋል የሚለውን ለማረጋገጥ ከጎናቸው መሆን እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።በሰላም የተገኘው ሽልማት በልማትም እንዲደገም ከዜጎች ብዙ እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 2/2012
ለምለም መንግሥቱ