– ከኮድ 1 ውጭ የታክሲ አገልግሎት መስጠት አይቻልም ተብሏል
አዲስ አበባ፡-የኤሌክትሮኒክስ የታክሲ ስምሪት አገልግሎት ለመስጠት ጥያቄ ካቀረቡት 22 ድርጅቶች መካከል መስፈርቱን ላሟሉ ስድስት ድርጅቶች ፈቃድ መስጠቱን የአዲስ አበባ መንገድ ትርንስፖርት ባለስልጣን ገለጸ:: ከኮድ 1 ውጭ የታክሲ አገልግሎት መስጠት አይቻልም ተብሏል።
የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮማንደር አህመድ መሀመድ እንደገለጹት፤ የኤሌክትሮኒክስ ታክሲ ስምሪት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ፈቃድ ወስደው ሥራ መጀመራቸው በከተማዋ የሚታየውን የተበላሸ የትንስፖርት አገልግሎት ለማዘመን ያስችላል፤ ተጠቃሚውም የተሻለ ደህንነት እንዲሰማው ያደርጋል፤ በተመጣጣኝ ዋጋ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠትም ያስችላል::
የኤሌክትሮኒክስ ታክሲ ስምሪት አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው ከሁለት ዓመት እንደማይበልጠው የገለፁት ኮማንደር አህመድ፤ ቴክኖሎጂው የትራንስፖርት ስርዓቱን ለማዘመንና ስርዓትን ባለው መልኩ እንዲመራ ለማድረግ በ2011 ዓ.ም መጨረሻ ላይ መመሪያ እንደወጣለት ተናግረዋል::
በመመሪያው መሠረትም መስፈርቱን ላሟሉ ስድስት ድርጅቶች ባለስልጣኑ ፈቃድ የሰጠ መሆኑን አመልክተው ቀሪዎቹ መስፈርቱን አሟልተው ሲቀርቡ ፈቃዱ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ የኤሌክትሮኒክስ ታክሲ ስምሪት አገልግሎት በተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን የገለጹት የቤዛ ራይድ ትራንስፖርት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጁኔይዲ ባሻ፤ ቤዛ ራይድ ከባለስልጣኑ ፈቃድ አግኝቶና አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቆ ከተወሰኑ የታክሲ ማህበራት ጋር አገልግሎቱን ለማዘመን አብሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል::
በኮድ-2ና ኮድ-3 የኤሌክትሮኒክስ የታክሲ ስምሪት ቴክኖሎጂ ተገጥሞላቸው የታክሲ አገልግሎት መስጠታቸው የታክሲ ማህበራትን ከገበያ እያስወጡን ነው፤ በየቦታው ተንቀሳቅሰን መስራት አልቻልንም፤ ሌሎች ታክሲዎች ይህ የኛ ክልል ስለሆነ እዚህ ቦታ አገልግሎት አትሰጡም የሚል ቅሬታ ስለሚያቀርቡ ባለስልጣኑ ምን ለማድረግ አስቧል?፡ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ኮማንደር አህመድ በሰጡት ምላሽ፤ ከአሁን ወዲህ የራይድ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡት ኮድ-1 ብቻ ናቸው ብለዋል::
በዚህ አግልግሎት መሰማራት የሚፈልግ ኮዱን መቀየር ይችላል እንጂ በኮድ-2 ወይም ኮድ-3 አገልግሎት የሚሠጥ ከሆነ ህገ ወጥ ተግባር ስለሆነ ከዚህ በኋላ የጸጥታ ሀይሎችና ትራፊክ ፖሊሶች ህግ የማስከበር ሥራ ይሰራሉ ብለዋል::
ታክሲዎች በአዲስ አበባ ክልል ውስጥ የትም ቦታ ተንቀሳቅሰው መስራት እንደሚችሉ መመሪያው ላይ ተቀምጧል ያሉት ኃላፊው፤ ይህን የማያከብር አካል ካለ ለጸጥታ አካላት በማሳወቅ መፍትሄ ማግኘት ይቻላል ብለዋል::
ፈቃድ ያገኙት ማህበራት አዲካ፣ ቤዛ ራይድ፣ አልታ፣ኢታ ሶሉሽን፣ ሊጋባ እና ዛይቴክ መሆናቸውም ያገኘነው መረጃ ያሳያል::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3/2012
በጌትነት ምህረቴ