አዲስ አበባ፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 140 የቀንድ ከብቶች የተዘረፉባቸው የዳንጉር ወረዳ አርሶ አደሮች መፍትሄ እንዳላገኙ ገለጹ::
የዳንጉር ወረዳ አርሶ አደሮች በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከ140 በላይ የቀንድ ከብቶቻቸው እንደተዘረፉባቸው አስታውሰው፣ በወቅቱ ንብረት አስመላሽ ኮሚቴ ተዋቅሮ መፍትሄ ይሰጣል ቢባልም የተዘረፉ የቁም እንስሳትንም ሆነ የጠፉ ንብረቶችን ከመመዝገብ ባለፈ እስከ አሁን ድረስ ዞሮ የጠየቃቸው አካል እንደሌለ በምሬት ተናግረዋል::
አርሶ አደሮቹ እንዳሉት የቀንድ ከብቶቹ የሚገኙባቸውን አካባቢዎች በማጠያየቅ ለሚመለከተው አካል በየጊዜው መረጃ እያደረሱ ቢሆንም የወረዳው አመራር አስፈላጊውን የጸጥታ ሀይል በመመደብና እኛንም በማሳተፍ ለማስመለስ ከመጣር ይልቅ ብቻውን “እያጣራሁ ነው” የሚል ምላሽ እየሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል::
‹‹እኛም ሆንን ቤተሰቦቻችን ችግር ላይ መውደቃችንን ወረዳው አልተረዳልንም›› ሲሉ ቅሬታቸውን የሚያቀርቡ አርሶአደሮቹ ‹‹ከብቶቻችን በአጎራባች ሁለት ወረዳዎች መኖራቸውን እያወቅን ማስመለስ ባለመቻላችን ለከፋ ችግር ተዳርገናል›› ሲሉም አክለዋል::
67 የቀንድ ከብቶች እንደተዘረፉባቸው የሚናገሩት የማንቡክ ከተማ ነዋሪው አቶ ወርቄ አህመድ እንደሚሉት፣ባለፈው ግንቦት ወር ካገኟቸው 13 ከብቶች በስተቀር ቀሪዎቹን ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል::
1500 የቀንድ ከብቶች አንዛጉና እና ትወን በሚባሉ የገጠር ቀበሌዎች እንደሚገኙ መረጃ ደርሷቸው ለወረዳው አመራሮች አሳውቀው እንደነበረ የሚገልጹት አርሶ አደር ወርቄ፤ የወረዳው አመራር ከጸጥታ አካላት ጋር ብቻቸውን ሂደው ዘራፊዎቹን ብቻ ይዘው በመምጣት እንዳሰሯቸው ገልጸው፣ የቀንድ ከብቶቹን ለማስመለስ ከዚያ ያለፈ ጥረት ሊደረግ ይገባ እንደነበረም አንስተዋል::
አርሶ አደር ታረቀኝ አባቡ በበኩላቸው 43 የቀንድ ከብቶቻቸው በዘራፊዎች የተወሰዱባቸው መሆኑን ገልጸው፤ እስከአሁን ጥብቅ ክትትል በማድረግ የቀንድ ከብቶቹ የሚገኙባቸውን ወረዳና ቀበሌዎች መረጃ በመስጠት እያገዙ ቢሆንም ፋይዳ ማጣታቸውን አስረድተዋል::
ከብቶቻቸው አጎራባች በሆኑት ማንዱራ ወረዳ ግድም ዳፍሊ ቀበሌ እና ፓዊ ወረዳ አባወረኛና በለስ ቀበሌዎች እንደሚገኙ ለመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አመልክተው እንደነበር የሚናገሩት አቶ ታረቀኝ፤ ዋና አስተዳዳሪውም ለሚመለከታቸው የወረዳ አመራሮች ትዕዛዝ የሰጡ ቢሆንም እስከአሁን ድረስ ከብቶቻቸውን የሚያስመልስላቸው አካል ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል::
ሌላው 43 የቀንድ ከብቶቻቸውን ማስመለስ እንዳልቻሉ የተናገሩት አርሶ አደር ማህሙድ አብደላ ናቸው::እርሳቸው እንደሚሉት ‹‹ከብቶቻችን በማንዱራና ፓዊ ወረዳዎች ስር በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች እንደሚገኙ መረጃው አለን፤ ሂደን ማምጣት ነው›› ያልቻልነው ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል::በዚህ ዓመት ማረስ አለመቻላቸው ሳያንሳቸው እስከአሁን ድረስ አቤቱታ በማሰማት እየተንገላቱ እንደሚገኙም ተናግረዋል::
የማንዱራ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ቢምር አምሳያ በበኩላቸው አርሶ አደሮቹ ቅሬታ ማቅረባቸውን አምነው፤ የማን እንደሆኑ ያላረጋገጥን ቢሆንም በወረዳችን ስር በሚገኙ ቀበሌዎች በርካታ የቀንድ ከብቶች ይገኛሉ የሚል መረጃ እንደደረሳቸው ይገልጻሉ::
የወረዳው አመራር በስምሪት ወደየቀበሌዎቹ ተሰማርቷል፤ በመሆኑም ይሄን መረጃ አጣርተው እንዲመጡ ተልዕኮ ሰጥተናል የሚሉት የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ፤ የተገኘውን መረጃ ገምግመን ምን ያህል የቀንድ ከብቶች በቁም እንደሚገኙ የምናሳውቃቸው ይሆናል::በዚህ መሰረትም ወደ ቦታው ሂደው የራሳቸውን ለይተው ማጣራት የሚችሉ ይሆናል በማለት ለቀረቡት ቅሬታዎች ምላሽ ሰጥተዋል::
የፓዊ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ብርሃኑ አሰፋ በበኩላቸው “መረጃውን ይዘን እያጣራን እንገኛለን::ከብቶቹ አሉ በተባሉባቸው ቀበሌዎች አጣርተን ቅሬታ ላቀረቡት አርሶ አደሮች እና ለሚመለከታቸው አካላት የምናሳውቅ ይሆናል” ብለዋል::
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ
ግርማ ታደሰ በበኩላቸው አርሶ አደሮቹ በተደጋጋሚ ቅሬታ ማቅረባቸውን አረጋግጠው “ጉዳዩን ችላ አላልነውም::አልፎ
አልፎ በአንዳንድ ቀበሌዎች የሰላም ስጋቶች ቢኖሩም የቀንድ ከብቶቹ አሉ በተባሉባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ የወረዳ
አመራሮች
ጋር እየተገናኘን በቅርበት እየሰራን ነው” ብለዋል::
ሕዳር 19/2012 ዓ.ም አርሶ አደሮቹን ከማንዱራ ወረዳ አመራሮች ጋር በማገናኘት አጠቃላይ በሂደቱ ላይ መረጃ የተለዋወጥን ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ውጤት አልተገኘም ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በቀጣይ በዞን ደረጃ ይሄን ጉዳይ ብቻ ተከታትሎ በማጣራት መፍትሄ ላይ ሊያደርስ የሚችል አካል በማዋቀር እንሰራለን ብለዋል::
የቤኒሻንጉል ክልል የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ባየታ በበኩላቸው የተዋቀረው የንብረት አስመላሽ ኮሚቴ እየተከታተለ ሰፊ ስራ እየሰራ እንደነበረ በማስታወስ አሁን ላይ የጠራ እና ወቅታዊ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል::
‹‹የተዘረፉብን 140 የቀንድ ከብቶቻችን መኖራቸውን እያወቅን የወረዳው አመራር ቀና ትብብር እያደረገልን ባለመሆኑ ማስመለስ አልቻልንም›› በሚል ርዕስ የዳንጉር ወረዳ አርሶ አደሮች ቅሬታን አስመልክቶ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ነሐሴ ሁለት ቀን 2011 ዓ.ም በሰራው ዘገባ የክልሉ የሠላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ መፍትሄ እንደሚሰጥ ገልጾ እንደነበር ይታወሳል::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3/2012
ሙሐመድ ሁሴን