አዲስ አበባ፡-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሰላም የኖቤል ሽልማትን ተቀብለው ወደ አገር መመለሳቸውን ተከትሎ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የደስታ መግለጫ ስነ ስርዓቶች ተካሂደዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው የደስታ መግለጫ መርሐ ግብሩ ትናንት ከማለዳው ጀምሮ በሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ፣ በሐረሪ ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ ክልል በቢሾፍቱ፣ በአዳማ፣በሰበታ፣ በጅማ ከተሞች፣በአማራ ክልል በደብረ ማርቆስ ከተማ፣በደቡብ ክልል በወላይታ ሶዶ፣ በሐዋሳ፣ ከተሞችና በሌሎች አካባቢዎች ተከናውኗል::
በጅማ ከተማ በተካሄደው የጅማ ዞን እና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የመከላከያ ሰራዊት አባላት እንዲሁም የከተማዋ እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
በስነ ስርዐቱ ላይ የተገኙት የጅማ ከተማና የአካባቢዋ ነዋሪዎች፥ ሽልማቱ አንድነታቸውን እንደሚያጠናክርና በመከባበርና በሠላም አብሮ የመኖር እሴታቸውን እንደሚያጎለብት ተናግረዋል።
በሀዋሳ ከተማ የዓለም የሠላም ኖቤል ተሸላሚ ለሆኑት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የደስታ መግለጫ መርሐ ግብር ሲካሄድ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የክልሉ የፖሊስ ማርሽ ባንድ እንዲሁም በከተማው የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞችና ነዋሪዎች መሳተፋቸው ታውቋል።
በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ጥላሁን ከበደ ሽልማቱ ለአገራችን ሠላም እና የሕዝባችን አንድነትን እንደሚያጠናክርና በመከባበርና በሠላም አብሮ የመኖር እሴቶቻችንን እንደሚያጎለብት ተናግረዋል::
በሐረር ከተማ በተካሄደው የደስታ መግለጫ መርሐ ግብር የሐረሪ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች ወጣቶችና ሴቶች ተገኝተዋል::የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች የሰላም ኖቤል ሽልማት ላገኙት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የደስታ መግለጫ ስነ ስርዓት አካሄደዋል። በዚህ ስነስርዓት ወቅት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሸነፉበትን የሰላም ኖቤል ሽልማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ክብር አብራርተዋል።
“በሰላም እና መረጋጋት ያገኘው አንፀባራቂ ድል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁላችንም በጋራ መስራት ይገባናል” ብለዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ የኖቤል ሰላም ሽልማት ለሀገራችንና ለመላው አፍሪካ ከፍተኛ ኩራትና ደስታን የፈጠረ መሆን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥትም ገልጿል::
በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ማርቆስ ከተማ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የዓለም የኖቤል ሽልማትን አስመልክቶ ውይይት ተካሂዷል::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3/2012