አዲስ አበባ፡- ወደ ከፍታ መሰላል የሚወጡትን ጎትቶ ከማውረድ ይልቅ ገፍተን ጫፍ ለማድረስ ልንተጋ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ጠዋት ከኦስሎ አዲስ አበባ ሲገቡ የጀግና አቀባበል ተደርጎላቸዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፈው ማክሰኞ በኖርዌይ ኦስሎ በተከናወነው ስነስርዓት ላይ ተገኝተው የሰላም የኖቤል ሽልማታቸውን ከተቀበሉ በኋላ ትላንት ወደአገራቸው የተመለሱ ሲሆን፤በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለምአቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም አጋጣሚው ለመማር፣ ለመቀየር፣ አንድ ለመሆን፣ ለመሻሻልና በዓለም መድረክ በአዳዲስ ማንነቶች ከፍ ብለን ለመታየት እንድንጠቀምበት የሚያስችል ነው ብለዋል::
ኢትዮጵያ ውስጥ ትውልድ የሚበላውን ሾተላይ ማከም ያስፈልጋል፤ ወደ መሰላል የሚወጡ ልጆቻችን ካሉ ጎትቶ ማውረድ ሳይሆን ገፍተን ጫፍ እንዲደርሱ ማድረግም ከሁላችን ይጠበቃል ሲሉም ተናግረዋል::
ኢትዮጵያ ብዙ ጀግኖች ቢኖሯትም የሚወጣጡበት መሰላል ከሌለ ከጫፍ መድረስ አይቻልምና አንዱ አንዱን ደግፎ ከጫፍ ሲደርስ ቱሩፋቱ ለሁሉም መሆኑ ከሰሞኑ ሽልማት እንደተረጋገጠም ገልፀዋል::
የኖቤል ኮሚቴ የሚያየውንና የሚያውቀውን ጠርቶ የሸለመ ቢሆንም ሽልማቱ እውን እንዲሆን ብዙ እናቶች በጓዳ ያለቀሱ፣ የፀለዩ፣ የተጨነቁ እና ያማጡ እንዳሉ በውል ይታወቃል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ “በመሆኑም ሁሉንም ወክዬ ሽልማቱን የተቀበልሁ ብሆንም ሽልማቱ ለኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች፣ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ እና ለእኔ እንዲሁም ለተቀሩት የኢትዮጵያና ኤርትራ ወዳጆች ሁሉ የተሰጠ በመሆኑ እንደ መልካም እድል በመጠቀም ሌሎች ችግሮቻችንን ለመፍታት እንደመነሻ አድርገን የምንገለገልበት ይሆናል” ሲሉም ተናግረዋል:
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ደሀ ብንሆንም ታሪክና ባህል ያለን፣ ለሥራ የምንተጋ ህዝቦች መሆናችንና ከዚህ ቀደም ያልታወሱ ታሪኮቻችንን ሁሉ ለማንሳት እድል እንዳገኘን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊገነዘበው ይገባል:: ከ1500 ዓመት በፊት በክርስትና እንዲሁም ከ1400 ዓመት በፊት በእስልምና በርካታ ሰዎች የተቸገሩትን የምታቅፍና የሰላም አገር መሆኗን አምነው የተጠለሉባት ኢትዮጵያችን ከ1 ሺህ ዓመት በኋላ ታሪኳ እየቀጨጨና እየሳሳ ቢመጣም ተመልሶ የሚታደስበት እድል በመገኘቱ በተባበረ ክንድ እና በተስማማ ማንነት ሀገራችን ካለችበት ሁኔታ ወደ ብልፅግና እንድትሸጋገር በጋራ መትጋት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል::
የሽልማት ፕሮግራሙን ከ1ነጥብ5 ቢሊዮን በላይ ህዝብ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ስለመከታተሉ መረጃ እንደደረሳቸው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እድሉ ቱሪስቶችን ለመሳብ፣ ኢንቨስትመንት ለማምጣት፣ ሥራ አጥነትን ለመቀነስ እና ወደ ብልፅግና ለመሸጋገር የምንጠቀምበት እንዲሆን መላው የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ ህዝብ በትብብር እንዲሠራ አሳስበዋል::
የጦርነትና የግጭት ታሪኮች አብቅተው በመተባበርና በመስማማት ሀገርን የመቀየርና እኛም እንደሌሎቹ መርዳት የምንችል እንድንሆን ሰላምና ፍቅር ለኢትዮጵያ በእጅጉ አስፈላጊ ነገሮች ናቸው ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፣ በወንድማማችነት ስሜት ከምቀኝነትና ስድድብ በመራቅ ወደኋላ የሚያስቀሩንን እኩይ ድርጊቶች በጋራ ማሸነፍ እንደሚገባም ገልፀዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው በቅርቡ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተገናኝተው ድሉን በጋራ እንደሚያከብሩ ተናግረው፣ ለኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች እንዲሁም ለፕሬዚዳንቱ ምስጋናቸውንና የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::
በአቀባበል ስነስርዐቱ ላይ ሚኒስትሮች፣ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች፣ የመከላከያ ኃይል አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አርቲስቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በቦሌ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል ያደረጉ ሲሆን የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ነዋሪዎች ደግሞ እስከ ቤተመንግሥት ድረስ ድጋፍና ደስታቸውን ገልፀዋል::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3/2012
ድልነሳ ምንውየለት