አዲስ አበባ፡- የዶክተር ዐብይ አህመድ የኖቤል ሰላም ሽልማት አገሪቷ ለሰላም የሚተጉ ዜጎችን ማፍራት የምትችል መሆኗን ያሳየና በዓለም አደባባይ ለኢትዮጵያውን ከብርን ያጎናፀፈ መሆኑን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አረና)ፓርቲ ገለፁ::
የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ እና የአረና ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ በየበኩላቸው በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ዶክተር ዐብይ የኖቤል የሰላም ሽልማቱን በዓለም መድረክ ቀርበው በተቀበሉበት ወቅት የተሰማቸው ታላቅ ደስታ ነው:: አገሪቱ ለሰላም የሚተጉ ዜጎች ማፍራት የምትችል መሆኗንም አስመስክራለች::
አቶ ቶሌራ እንዳሉት ‹‹ሽልማቱ በዓለም ላይ ካሉ ሽልማቶች ሁሉ የላቀ እውቅና ያለው ታላቅ ሽልማት ነው::ለዶክተር ዐብይ እውቅና የሰጠ ብቻ ሳይሆን የአገሪቷን ስም በዓለም ደረጃ ከፍ ያደረገ ነው›› “ጎረቤትህ ሰላም ከሆነ አንተም ሰላም ታገኛለህ” የሚለውን የኦሮሞዎች አባባልም በትግባር ያሳየ ነው ብለዋል::
ዶክተር ዐብይ እዚህ ላይ በመመስረት የኢትዮጵያ ሰላም አስተማማኝ የሚሆነው ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለው ግንኙነት ሰላማዊ ሲሆንና ጎረቤት አገሮችም ሰላም ሲኖራቸው ነው በሚል በመስራታቸው ከኤርትራ ጋር የነበረው ፍጥጫ ተቋጭቶ ወደሰላምና መልካም ጉርብትና እንዲመለስ ማስቻላቸውን አስረድተዋል::
እንደ አቶ ቶሌራ አደባ ገለፃ፤ የኢትዮጵያ ሰላም መሆን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮችም ሰላም ማግኘት አለባቸው ከሚል አኳያ በጅቡቲና በኤርትራ መሃል፣ በሶማሊያና ኬንያ መሃል እንዲሁም በደቡብ ሱዳን ውስጥ ያለውን የእርስ በእርስ ግጭት በማስወገድና በተጨማሪም በሱዳን የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ ሰላማዊ ሽግግር እንዲኖርና ሰላም እንዲረጋገጥ ላደረጉትም አስተዋፅኦ ሽልማቱ ተሰጥቷቸዋል::ይህ እጅግ የሚያስደስት ነው::
ስለሆነም ይህ የተሰጣቸው ሽልማት በፈፀሙት ሥራ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም በርትተው እንዲሰሩም የሚያበረታታቸው ነው:: በተለይ ደግሞ በአገር ውስጥ ሰለምን ለማረጋገጥ የበለጠ በትጋት እንዲሰሩና በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲገኝ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ያደርጋል የሚል እምነት አላቸው::
አቶ ቶሌራ፣ ‹‹እኛ በአብዛኛው በዓለም ዘንድ ያለን እውቅና በአትሌቲክሱ ነው፤ከዛ ውጭ ያለው ስማችን በድርቅ፣ በረሃብና በጦርነት የሚታወቅ ነው:: በአሁኑ ሰዓት ግን በሰላም መንገድ ታላቅ ሽልማት በማግኘት በዚህ ስንታወቅ የኢትዮጵያን መጥፎ ገፅታ የቀየረ በመሆኑ በግሌ ደስታ ተሰምቶኛል:: ይህ ሰላም ቀጣይ እንዲሆን ለአገሪቱም ትኩረት ሰጥተው እንደሚተጉ አምናለሁ››ብለዋል::
አቶ አብረሃ በበኩላቸው ‹‹በመጀመሪያ ደረጃ ሽልማቱ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ እንደተሰጠ ነው የምቆጥረው›› ሲሉ ጠቅሰው፤ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሽልማቱን በኢትዮጵያ ስም መቀበላቸውን ገልፀዋል:: በመሆኑም ‹‹ሽልማቱ ለኢትዮጵያ ክብር ለሁላችን ደግሞ ኩራት ነው::እኛ ኢትዮጵያውያን ሰላም ወዳድ ህዝብ ነን››ብለዋል::
አቶ አብረሃ፣ ‹‹መሪያችን የሰላም ሽልማት ተቀብለዋል::ስለዚህ አሁንም ደግሞ በአገር ውስጥ ያለውን አለመረጋጋት የፈጠረውን ድባብ ብሎም እርስበእርስ የመጠራጠር ነገር በሰላማዊ መንገድ እየፈታን አገራችንን ሰላም እንድትሆን የምናደርግበት ከመሆኑም በተጨማሪ ሰላም ለማስፈን እድል ይፈጥርልናል ብዬ አምናለሁ::››ሲሉ ተናግረዋል::
ዶክተር ዐብይ ሽልማታቸውን ሲቀበሉ እርሳቸውም እንደማኛውም ኢትዮጵያዊ የተሸለሙና ስማቸው የተጠራ ያህል ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል:: በአገራቸውም መኩራታቸውን ጠቅሰው፤ ይህን በጎ ነገር በአገር ወስጥም ባለው ሁኔታ ላይ እንደሚደገም ተስፋ ማድረጋቸውን አመልክተዋል::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3/2012
አስቴር ኤልያስ