ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ነጆ ከተማ ውስጥ ነው:: የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዛው ነጆ ከተማ በሚገኘው ሌተናል ኮሎኔል አብዲሳ አጋ ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በነጆ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል:: በ1984 ዓ.ም 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በከፍተኛ ውጤት በማለፍ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅለው በሥነ ማስተማር ትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል:: ከዚያ እንደወጡም በቀጥታ በመንግሥት ቀጥተኛ ስምሪት በመምህርነት ባሌ ቢመደቡም ለአራት ወራት ያህል ብቻ በመምህርነት እንዳገለገሉ ባሌ በሚገኘው የጊኒር ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሆነው ይሰየማሉ:: በዚህም ሃላፊነት ለሦስት ዓመት ተኩል ከሠሩ በኋላ የሮቤ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ሃላፊ እንዲሆኑ በክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት በቀጥታ ይሾማሉ::
ዕድላቸው ሆነና ለአንድ ዓመት በፕሪንስፓልነት እንዳገለገሉ ተቋሙን ከማሰልጠኛነት ወደ ኮሌጅነት ከፍ ማድረግ ቻሉና የኮሌጁ የመጀመሪያ ዲን ሆኑ:: ብዙም ሳይቆዩ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመማር ዕድል ይሰጣቸውና በትምህርት አመራር ዘርፍ ይሰለጥናሉ:: ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዳጠናቀቁ ግን የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ ሆነው ተሾሙ:: በመቀጠልም የከፍተኛ ትምህርት የአቅም ግንባታ ሃላፊ ሆነው እንዲሠሩ ተመደቡ:: እዛም እያሉ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በህንድ እንዲማሩ በመንግሥት ዕድሉ ተመቻቸላቸው:: በህንድ አገርም ትምህርታቸውን ተከታትለው እንደመጡ የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ:: ይሁንና በኢንስቲትዩቱ ለአንድ ዓመት ብቻ እንዳገለገሉ በወቅቱ የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አሁን ደግሞ የኮተቤ ሜትሮፖሊቲያን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲያገለግሉ ተመድበው እስካሁንም ዩኒቨርሲቲውን እየመሩ ይገኛሉ:: በትምህርቱ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱት ዶክተር ብርሃነ መስቀል ጠና የዛሬው የዘመን እንግዳችን ናቸው:: ከእርሳቸው ጋር በተለያዩ ወቅታዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል::
አዲስ ዘመን፡- ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካን በመወከል የእግር ኳስ ልዑካን ቡድንን ይዘው ወደ ቻይና ተጉዘዋል:: ተቋሙ ይህንን ዕድል ያገኘበትን አጋጣሚና የቻይና ቆይታችሁ ምን ይመስል እንደነበር ያብራሩልንና ውይይታችንን እንጀምር?
ዶክተር ብርሃነ መስቀል፡- ባለፉት ዓመታት በስፖርቱ መስክ የተሻለ መሥራት አለብን ብለን በቁርጠኝነት ሥንሠራ ቆይተናል:: በዚሁ መሰረት እንደምታስታውሱት መቀሌ ላይ በተደረገው የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የእግር ኳስ ውድድር ዩኒቨርሲቲያችን የአንደኝነት ደረጃ ነበር ያገኘው:: በዚህ ምክንያትም አፍሪካን በብቸኝነት ወክለን ቻይና ቤጂንግ ከተማ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የዩኒቨርሲቲዎች ውድድር ላይ እንድንሳተፍ ተመረጥን:: ቡድኑን በመሪነት ይዤ የሄድኩት እኔ ነበርኩ:: ዩኒቨርሲቲያችን በተለይ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሁከት ማዕከላት በሆኑበት ዘመን ከአገር አልፎ አህጉርን ለማስጠራት መቻሉ በግሌ ከፍተኛ ደስታ ነው የፈጠረልኝ:: ስለዚህ በውድድሩ ማሸነፍ ባንችልም እንኳ መሳተፋችን በራሱ እንደትልቅ ነገር ሊወሰድ የሚገባው ነው::
በተጨማሪም ከፍተኛ ልምድ የቀሰምንበትና ብዙ እውቀት ያገኘንበት መድረክ ነው:: ከዚህም በሻገር ከቻይና ጋር በነበረን ጨዋታ ዮናስ የተባለው የእኛ ተጫዋች ኮከብ ተጫዋችና ኮከብ ግብ አግቢ ተብሎ ተመርጧል:: ይህም ተጨማሪ ደስታ ነው የፈጠረልን:: እንደ አጠቃላይ በኢኮኖሚ ከበለፀጉትና ልምድ ካላቸው አገራት መካከል አፍሪካን ወክለን መገኘታችን በራሱ ለእኔ አገሬ ተስፋ ያላት መሆኑን ያመላክተኛል:: በተለይም በጨዋታዎች እና በጉዟችን ሁሉ የተለያዩ አገራዊ ህብረ ዝማሬዎችን እያዜምን አገራችንን ብሎም አህጉራችን ለተቀረው ዓለም ለማሳየት መቻላችን ኢትዮጵያ ፈጽሞ አትፈርስም የሚል እምነት እንዲኖረኝ አድርጓል::
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች ኢትዮጵያዊ አንድ የሚሆነው ከአገር ሲወጣ ብቻ እንደሆነ ይገልፃሉ፤ ከዚህ አንፃር ይህ ሁኔታ ምን ያህል እውነት ነው ይላሉ?
ዶክተር ብርሃነ መስቀል፡- እንዳልሽው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በውጭ ሳለ በአገሩ ጉዳይ ላይ አይደራደርም:: በጉዟችንም ያስተዋልኩት ይህንን ነው:: ነገር ግን እኔ ከቻይናውያን ብዙ ልንማራቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ አምናለሁ:: ቻይናውያን ሃይማኖት ወይም ብሔር ሳይሆን አጀንዳቸው ሥራ ብቻ ነው:: ዋነኛ አጀንዳቸው ሥራ እና ሥራ በማድረጋቸው ብልጽግና ማምጣት ችለዋል:: ያሉት እየኖሩ፥ የወደፊቱን እያሰቡ ራሰቸውን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማሸጋገር ችለዋል:: እኛ የወደፊቱን ማሰብ ላይ በጣም ይጎድለናል:: እንደተባለው ከአገር ስንወጣ አማራጭ የለንም:: አማራጫችን አንድ መሆን ነው:: ምክንያቱም እኔ የምታወቀው በኦሮሞነቴ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነቴ ነው:: ስለዚህ ይዤ የምሄደው የኢትዮጵያዊነት መታወቂያዬን ነው:: እዚህ ስንመለስ ግን በየጉራንጉር ውስጥ እየተገባ ወደአልተፈለገ ሁኔታ ውስጥ ገብተን እንገኛለን:: እኔ ቻይና በነበረኝ ቆይታ አንዳንድ ሰዎችን ስጠይቅ የተረዳሁት አንድ ነገር በቻይና አብዛኞቹ አካባቢዎች የሚታየው ብልጽግና እና የተረጋጋ ሁኔታ የመጣው ህዝቡን ከማህበራዊ ሚዲያዎች እንዳይጠቀም በማቀብ ፊቱን ወደ ሥራ ብቻ እንዲያዞር በመደረጉ ነው:: በተቃራኒው ደግሞ በሆንግ ኮንግ ማህበራዊ ሚዲያው በነፃነት በመለቀቁ ሰዎች ከሥራ ይልቅ ለብጥብጥ እንዲነሳሱ ምክንያት ሆኗል:: እኛም በልተን ሳንጠግብ፤ ቆርሰን ሳንበላ፤ ቁርሱን በልቶ ምሳውን የማይደግም፤ ምሳውን በልቶ እራቱን ለማግኘት የሚቸገር ህዝብ ይዘን በፖለቲካ አዙሪት ውስጥ ገብተን እንራወጣለን:: የፖለቲካ ሸቀጥ ማራገፊያ በመሆናችን ነው አንድም ወደኋላ የቀረነው::
በሁለተኛ ደረጃ ለፖለቲካ ነጋዴዎች እንጀራ ለመሆን ብለን እኛ እየጠፋን እንደሆነ ነው የሚሰማኝ:: ቻይኖቹ ጋር ያየነው ነገር እያንዳንዱ ዜጋ ዋናው አጀንዳው ሥራ ብቻ መሆኑን ነው:: አገር አንድ ሆኖ ሲቆም ልማቱም፥ ዕድገቱም ብልጽግናውም እንደሚመጣ በአግባቡ የተረዱ ህዝቦች ናቸው:: እነሱ ከምንም በፊት አገር ሲቀድም ወደየት ሊያደርስ እንደሚችል ተረድተዋል፤ እኛ ግን አልተረዳንም፤ ማሰብም አንፈልግም:: የሚገርመው አገር ከሌለ የዚህ ብሔር ጥቅም ተጓደለ፤ የዚህኛው አልተጠበቀም ማለት እንኳን አንችልም:: አገር ሲኖረን እኮ እንኳን በምድር ላይ በህዋ ላይ ሳይቀር መደራደርም ሆነ መጠቀም እንችላለን:: አገር ከሌለ እኔም አንቺም ላንኖር እንችላለን:: አይበለውና ነገ እኮ ልጆቻችንን የምናገኘው ከህንፃ ፍራሽ ሥር ሊሆን ይችላል:: ወደቻይና ለእግር ኳስ ብለን ነው የሄድነው፣ ነገር ግን ብዙ ተምረን ነው የመጣነው:: ከሌሎች አገራት የመጡት ተጫዋቾች ሲበሉ፣ ሲጓዙ አንድ ላይ ነው፤ ሲነጋገሩ እንኳ መሪያቸውን ያዳምጣሉ፤ ሌላው ይቅርና ሲጓዙ እንኳን እንደጉንዳን አብረው ነው የሚተሙት:: ይህ ሁኔታ ያስቀናሻል:: ይህ ስሜት እኛ ጋር እንዲመጣ ነበር እኛም ጥረት ስናደርግ የነበረው:: ቻይናዎች ጋርም ሆነ ሌሎች አገራትን መታዘብ እንዳልኩት አንዱ አንዱን አሳልፎ አይሰጥም አገሩን አይሸጥም:: ወደ እኛ ስንመጣ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል:: የምንለው ነገር ሁሉ የሚያልፍ ግን ዋጋ የሚያስከፍለን ነገር ነው:: እንዴት አድርገን ወደአገራችን ማምጣት አለብን የሚለው ነገር ያሳሳበኛል:: ውስጤ ይጨነቃል::
አዲስ ዘመን፡- ይህንን የሚሉት አንድነታችን ከልብ የመነጫ አይደለም ብለው ስለሚያምኑ ነው?
ዶክተር ብርሃነ መስቀል፡- የእኔ ሥጋት አሁን ያለው የአገራችን ሁኔታና የፖለቲካ አለመረጋጋት የዘመነ መሳፍንት ዘመን እንዳይደገም ነው:: ከዚህ ሁኔታ በፍጥነት መውጣት መቻል አለብን:: ለዚህ ደግሞ ቁጭ ብለን እየተወያየን በአስተሳሰብ የበላይነት መንፈስ እያሳደግን ካልሄድን አደጋ ነው የሚል ሥጋት አለኝ:: እንደምሁር ከእኔ በማይጠበቅ ቋንቋ ልናገር ካልኩ ግን ሀገሬን መንገድ ወይም የባቡር ሃዲድ ከምትዘረጋልኝ አልያም ህንፃ ከምትገነባልኝ አንድነታችን የሚያጠፋውን አካል የምታጠፋበትን ሥርዓት ብትዘረጋልኝ እምርጣለው:: ይህንን ስል ልማት አያስፈልግም ማለቴ እንዳልሆነ እንድትገነዘቢልኝ እፈልጋለሁ:: ግን ከልማት በፊት ልማት አጥፊውን መርዝ ማስወገድ አስፈላጊ ነው:: ቆሻሻውን ሳናደርቀው በቆሻሻው አረንቋ ላይ ህንፃ ብንገነባ፤ የባቡር ሐዲድ ብንዘረጋ አረንቋው ያሰምጠዋል:: ይህ አረንቋ ደግሞ ለእኔ ማህበራዊ ሚዲያው ነው::
ስለዚህ ልማት ማካሄድ ያለብን እነሱን ባጠፋንበት መደላደል ላይ ነው መሆን ያለበት:: ይህንን እውነታ ነው ከቻይና የተማርኩት:: እኛ ቻይናን ፀረ ዲሞክራሲ አገር ናት ልንላት እንችላለን:: ነገር ግን እየጠፋን ስለዲሞክራሲ ማውራት አንችልም:: እኔ ከፊት ለፊታችን የሞት ጥላ እያጠላብን፥ ውድመትና እልቂት ከፊታችን ከበሮ እየጎሰመብን እኔ ስለልማት ስለዲሞክራሲ ስለነፃነት ማውራት አልችልም:: ይህም ሲባል ግን ያለፈው ነገር መመለስ አለበት ማለቴ አይደለም፤ ሰው ባሰበው ነገር ብቻ ቃሊቲ የሚበሰብስበት፤ እግሩ የሚቆረጥበት የሚገደልበት ሁኔታ ደግም እንዲመለስ አልሻም:: ነገር ግን ነፃነት በገደብ መሆን አለበት:: መንግሥት በግልፅ መንቀፍ አለበት:: ዙሪያ ዙሪያውን የሚሄድበትን መንገድ ማረም አለበት:: መጠየቅ ያለበት መጠየቅ አለበት:: ይሄ የእሽሩሩ ነገርና የፓርቲ ጋጋታ ሀገርን እንዳያጠፋ እሰጋለሁ::
አዲስ ዘመን፡- ነፃነት መገደብ አለበት ሲሉ ምን ማለቶ እንደሆነ ትንሽ ቢያብራሩልኝ?
ዶክተር ብርሃነ መስቀል፡- መንግሥት በላቀ ደረጃ አገርን መምራት አለበት ብዬ አስባለሁ:: ከፊት ለፊታችን ያለው
ምርጫ ራሱ ያሳስበኛል:: አሁን ባለንበት ሁኔታ የሚካሄደው ምርጫ ምን መዘዝ ይዞ ሊመጣ ይችላል የሚለው ነገር ያሳስበኛል:: ሰው
ወደ ጎጡ ተመልሶ እኔ የተወለድኩበት ቀበሌ ልጅ ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ የሚል እሳቤ ጨብጧል:: በዚህ ሁኔታ በመንደር ላይ ተመስርተን
የምናደርገው የምርጫ ሂደት ምን አልባትም መንግሥት ለማቋቋም የምንቸገርበት ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል:: ከዚህም አልፎ ሁሉም ወደ
ራሱ የመጎተቱ ሂደት ሲጠናከር ወደ ጉልበት እርምጃ የምንሄድበት ሁኔታ እንዳይፈጠር ሥጋት አለኝ:: ይህ ሁኔታ መልሶ የአገር ፀር
ሆኖ እንዳይመጣ እፈራለሁ:: አገሪቱ ተመልሳ መቆም ወደማትችልበት ሁኔታ እንዳያመራት መንግሥት በላቀ አስተሳሰብ ማሰብና መሥራት
አለበት:: አሁን ምርጫው ደርሷል፤ እነማናቸው የሚመረጡት? እነማናቸው እጩ ሆነው የሚቀርቡት? የሚለው ነገር በአግበቡ ባልተለየበት
ሁኔታ ሁሉም ከበሮ እየጎሰመ ያለው በእርግጥ አሸንፎ
መንግሥት ለመሆን ነው:: የሚገኘው አብዛኛው ነጋሪት ጎሳሚ ይህንን አገር እንዴት እመራለሁ ብሎ ከማሰብ አንፃር መምራት የሚያስችለውን ሰነድ ያለመዘጋጀቱ ነው:: ስለሆነም ብዙ ችግሮች ተከታትለው እንዳይመጡ መንግሥት በጣም በላቀ አመራርና አስተሳሰብ ምርጫውን መምራት አለበት የሚል ነው እምነቴ:: ምርጫው ራሱ ከመልካም ጎኑ መጥፎ ጎኑ እንዳያዘነብል፤ ሥጋቶችን ሊቀንስ በሚችል መልኩና አገርን የማቆም ዕድሉን ሊያሰፋ በሚችል መልኩ ማስኬድ ይገባል የሚል እምነት አለኝ::
አዲስ ዘመን፡- እርስዎም እንዳነሱት አገሪቱ አሁን ላለችበት የፖለቲካ ትርምስ ትልቁን ሚና እየተጫወቱ ያሉት ፅንፈኛ የሆኑ አክቲቪስቶች እንደሆኑ ይታመናል:: ከዚህ አንፃር እነዚህን አካላት በምን መልኩ ሥርዓት ማስያዝ ይገባል ይላሉ?
ዶክተር ብርሃነ መስቀል፡ – እኔ አክቲቪስቶችን በሁለት መልኩ ነው የማየው፤ አንደኛው ነፃነት እኩልነት መረጋገጥ አለበት ብለው የሚሠሩትን አበረታታለሁ:: ነገር ግን ደግሞ የራሳቸውን ቤተሰብ ነቅለው፤ ውጭ አስቀምጠው፤ ኑራቸውን አደላድለው፤ ግን ደግሞ ይህች አገር ሺህ ጊዜ እንደሰዶምና ጎሞራ ብትነድ እኔ ምንም አልሆንም የሚሉ፤ ራሳቸው ከዳር ቆመው ሌላውን ህዝብ በርታ፣ ግደል፣ ቁረጥ፣ ጨፍጭፍ ብለው በየማህበራዊ ሚዲያው ዱላ በሚያቀብሉ ሰዎች አዝናለሁ:: እነዚህ ሰዎች ምንም ቢሆን እትብታቸው እዚህ ስለተቀበረ ነገም ደግሞ ማለፋቸው ስለማይቀር መቀበሪያ እንዳያጡ ሥጋት አለኝ:: ምክንያቱም ሰው ሁሉ ዘላለማዊ አይደለም እና ነው:: ይህንን እውነታ ሊዘነጉት አይገባም ባይ ነኝ::
እኔ መቀመጫውን የት እንዳደረገ የማላውቀው ሰው እኔና ወንድሜን ሲያጋድለን፣ ህዝብና ህዝብን ሲያባላ ዝም ሊባል አይገባም ባይ ነኝ:: ይህንን ስል ግን ያለውን መንግሥት ሙሉ ለሙሉ መደገፍ አለበት ማለቴ አይደለም:: ነገር ግን በአስተሳሰብ፣ ወይም በፖሊሲ ደረጃ እንቃወመው የሚል እምነት ነው ያለኝ:: የለውጥ ስትራቴጂ ነድፈን እንቃወመው የሚል አቋም ነው ያለኝ:: ነገር ግን ምንም ነገር ሳናዘጋጅ ሳናመርት በጠቅላይ ሚኒስትር ወንበር ላይ ብቀመጥ ምን ላመጣ እችላለሁ ብሎ ማሰብና ራስን መጠየቅ ይገባል:: እናም የተሻለ ለመሥራት ካሰብኩኝ የተሻለ የሚያሠራኝን ነገር ለህዝቤ እያሳየሁ ለውድድር ራሴን ማዘጋጀት አለብኝ:: አብዛኞቹ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች በስድብና በውርጅብኝ ተከታይ የማሰባሰብ እንጂ አገርን የማሸጋገር አላማ የላቸውም:: አገሬ መሸጋገር አለባት፣ ህዝቤ ነፃነቱን ማግኘት አለበት በኢኮኖሚው ማደግ አለበት፤ በቀን ሦስት ጊዜ መብላት ቢያቅተው በቀን ሁለት ጊዜ እንዲበላ ማድረግ አለብን:: አሁን አሁን አርሶአደራችን እያረሰ ነው ወይ? ከደረሰ እርሻ ላይ እህል እየተሰበሰበ ነው ወይ? ጎተራችን ሙሉ ነው ወይ? ይህ ጉዳይ በጣም ያሳስበኛል:: ዛሬ ላይ አርሶ የሚያበላን፣ የወለደን፣ አርሶአደር በቤቱ በነፃነት እያደረ ነው ወይ? ለምንድን ነው የሥጋት ምክንያት የምንሆነው? ለምንድን ነው የወለዱን ወላጆች ላይ የሥጋት ነጋሪት የምንጎስመው? ይህ መሆን የለበትም ባይ ነኝ:: ይህን ስል የዶክተር አብይን መንግሥት የግድ መደገፍ አለብን ማለቴ አይደለም፤ ነገር ግን አገርን መታደግ ይገባናል የሚል ፅኑ እምነት ስላለኝ ነው?
አዲስ ዘመን፡- በተለይም ደግሞ ያለፈ ትርክትን እያነሱ ህዝብንም ከህዝብ እያባሉ ያሉ ልዩነቶች እንዲሰፉና ብጥብጡ እንዲነግሥ እያደረጉ ያሉ ምሁራንና አክቲቪስቶች በምን አይነት የሕግ ልጓም ሊገደቡ ይገባል ይላሉ?
ዶክተር ብርሃነ መስቀል፡- እኔ የዛሬ መቶ ዓመት የነበረን ታሪክ ልጆቼ አያውቁትም የሚል እምነት አለኝ:: የእኔ ልጆች መጠየቅ ያለባቸው ዛሬ እነሱ በሚፈጥሩት ችግር ብቻ ነው:: እኔም ብሆን ያንን ዘመን አላውቀውም፤ ያወቅሁት በተፃፈ ታሪክ ነው:: ታሪክ ደግሞ እንደጸሐፊው የሚወሰን ነው የሚሆነው:: በማላውቀው ዘመን ላይ ቆሜ ታሪኩን በታሪክነት ይዤ (ልክም ይጻፍ ልክም አይጻፍ) ያነበብኩት ላይ ያለው ታሪክ እንዳይደገም ነው እኔ መሥራት ያለብኝ:: ታሪክ እያወራሁ ታሪክ ሳልሠራ እንዳላልፍ ነው ልጠነቀቅ የሚገባኝ:: የድሮ ታሪክ እያወራሁ እኔ በእኔ ዘመን ታሪክ ሳልሠራ እንዳላልፍ ነው ልጠነቀቅ የሚገባኝ:: ያለፈን ታሪክ እያብጠለጠልን የራሳችን ታሪክ ሊኖረን አይችልም:: እስከዛሬ ያለው መሪ የራሱ መልካም ሥራዎች ሠርቷል፤ የራሱ መጥፎ ሥራዎች ሠርቷል፤ አንዱን ነገር ስንነቅፍ እኛ ራሳችንን ያንን ነገር ላለመድገማችን ማረጋገጥ አለብን:: እኔ በአንቺ ላይ የምጠላውን ነገር በአንቺ ላይ ከደገምኩት አንቺን የምነቅፍበት ሞራል ሊኖረኝ አይችልም:: ስለዚህ አዲስ ታሪክ መሥራት እችላለሁ፤ ልማት የሚመጣበት፤ ህዝብ ተጠቃሚ የሚሆንበት ያ ቆሻሻ ያልነው ታሪክ በፅዱ ታሪክ የሚተካበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል:: እኔ የሆነ አካል ሐውልት ሲቆም ከሐውልቱ ጀርባ የዛን ሐውልት መልካም ጎን ብቻ ሳይሆን መጥፎ ነገሩንም እንዳስብ ያደርገኛል:: እኔ መደመርን እሳቤ በዚህ መልኩ ነው የምረዳው:: መልካሙንም ክፉንም ነገር አንድ ላይ ጨርግጄ የምጥል ከሆነ ይሄ ግብታዊነት ነው::
ለምሳሌ ያህል አፄ ምኒልክ የሠሩት መጥፎ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ በርካታ መልካም የሚባሉ ሥራዎችን ሠርተዋል:: በተመሳሰይ አፄ ሃይለሥላሴ፣ ደርግም ሆነ ኢህአዴግ በየዘመናቸው የሠሩት መልካምም መጥፎም ነገር አለ:: ሁሉም የሚወደሱበት የሚነቀፉበትን ነገር ሠርተዋል:: አሁንም ዶክተር አብይ የሠራቸው መልካም ጎኖች እንዳሉ ሁሉ ነገ ታሪክ የሚነቅሰው ህፀፆች ሊኖሩት ይችላሉ:: ወቅቱ ሲደርስ እሱን ደግሞ በተራው የምንነቅፍበት ሁኔታ ይፈጠራል:: ለእኔ የፈጣሪ ሥራ ብቻ ነው ከስህተት የፀዳው:: ስለዚህ ከሰው ፍፁምነት ልንጠብቅ አይገባም ባይ ነኝ:: በመሆኑም ጎዶሎ ነገሮችን ከምናጎላ መልካም መልካሙን አጉልተን በጎደሉት ላይ መሥራት ነው ያለብን:: በሆነ ስርዓተ መንግሥት ላይ የነቀፍነውን ነገር በእኛ ዘመን እንዳይደገም ዋስትና የሚሆነን ርዕዮተ ዓለም መቅረፅ እና ፖሊሲ መንደፍ አለብን:: የድሮውን ህፀፅ ብቻ እያላዘንን የምንሄድ ከሆነ አገራችንን ወደ ከፍታ ማማ ልናሻግራት አንችልም:: በተለይ ደግሞ በአዲሱ ትውልድ ንፁህ አዕምሮ ላይ መጥፎ ነገር ላለመጻፍ መጠንቀቅ ይገባናል:: ሁላችንም ልጆቻችን መልካሙን ነገር ብቻ እንዲወርሱና አገርን ማሻገር እንዲችሉ መሥራት አለብን:: እኔ መደመርን አስተሳሰብ የምረዳው በዚህ መል ክ ነው::
ከዚህ አንፃር ምሁራን በርካታ ሥራ መሥራት ይገባቸዋል የሚል እምነት አለኝ:: አሁን አሁን አንዳንዶቹ ምሁራን ምሁር ስለመሆናቸው በራሱ ጥያቄ ይፈጥርብኛል:: በእኔ እምነት አንድ ምሁር የህብረተሰብን ችግር ፈቺ እንጂ ችግር ፈጣሪ መሆን አይገባውም:: አሻግረው ተመልካች መሆን ይጠበቅባቸዋል:: ሌላው ቢቀር እነሱ የወለዱት ልጅ አለ፤ ለዚያ ልጅ መልካሙን መሻገሪያ መንገድ ማሳየት ይገባቸዋል:: የሚያባሉን መሆን አይገባቸውም:: ለማባላትማ መማር አያስፈልጋቸውም!:: ስለዚህ ምሁሮቻችን ቁጭ ብሎ የተሻለውን አማራጭ ለመንግሥት የሚያሳዩ ነው መሆን ያለባቸው:: ሁሉም በአንድ ጊዜ መንግሥት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን አይችልም:: ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የሚችለው አንድ ሰው ብቻ ነው:: ዶክተር አብይ ቢወርድ አንድ ሰው እንጂ አስሩም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መንበሩን ሊጨብጥ አይችልም:: ፈጣሪ አገር እንዲመራ ዕድሉን ለሰጠው መሪ ግብዓት ልንሆን ይገባል ባይ ነኝ:: መንገድ ልናሳየው ይገባል:: መሪዎችም ደግሞ አድማጭ ነው ሊሆኑ የሚገባው:: ምክር አድማጭ ሊሆኑ ይገባል:: መውሰድ የሚገባው ግን በልኩ ነው :: አንድ መሪ እኔ ስለነገርኩት ብቻ ሁሉን አይወስድም:: ነገር ግን ጆሮዎቹ ህዝቦቹ ላይ መሆን አለባቸው:: ከቤተመንግሥት እስከ ቀበሌ ድረስ የተዘረጋ ሥርዓት ሊኖር ይገባል:: የመረጃ ሥርዓት መኖር አለበት:: አሁን አለን ወይ ብለሽ ከጠየቅሽኝ ለእኔም ጥያቄ ነው:: የሚናቅ ሃሳብ ሰጪ መኖር የለበትም፤ ሃሳቦች ይምጡ፤ ይንሸራሸሩ፣ እንፋጭ፥ እንነጋገር መልካሙን ነገር እንያዝ ምሁራን በዚህ መልኩ የማያስቡ ከሆነ ያሳስበኛል:: የምሁር መለኪያው አስተሳሰቡ ነው መሆን ያለበት:: ምሁር ሆኖ እያለ የጎደለ አስተሳሰብ ይዞ ሲመጣ አንዳንድ ጊዜ ስለመማሩ እጠራጠራለሁ:: ሁሉም ምሁር ደግሞ ፖለቲከኛ መሆን አይችልም:: ሙያ ለባለሙያው ሊተው ይገባል:: አንዳንድ ጊዜ ጆግራፊ የተማረው፣ ሂሳብ ያጠናውም፤ በፊዚክስ የተመረቀውም ፖለቲከኛ መሆን ይፈልጋል:: የዛሬ ምሁሮች ልካችንን ገደባችንን ልናውቅ ይገባናል ባይ ነኝ:: እኔ መተንተን የምችለው ስለትምህርት ብቻ ነው፤ ሁሉንም መተንተን ብችል ኖሮ የሁሉም ዘርፍ ዶክትሬት ዲግሪ ለእኔ ይሰጠኝ ነበር:: ደግሞም የምንሰጠው ሃሳብ ገንቢ ይሆን አፍራሽ ጥናት ባለደረገልን ሁኔታ እንደመጣልን የምንናገረው ነገር አገር ከማጥፋቱም በዘለለ የምሁርነት ልኩን እናወርደዋለን:: ም ሁ ር ነ ታ ች ን ን ም እናስገምተዋለን::
አዲስ ዘመን፡ -አንዳንድ ምሁራን ሰሞኑን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ልዩነት እየጎለበተ መምጣቱ፤ በተለይ ደግሞ ከውህደቱ ጋር ተያይዞ በህውሃትና በሌሎች አባል ድርጅቶች መካከል እንዲሁም በኦዴፓ አባላት መካከል መግባባት ያለመኖሩ በቀጣዩ ምርጫ ላይ ተጨማሪ ሥጋት ይፈጥራል የሚሉ ወገኖች አሉ፤ እርስዎ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ?
ዶክተር ብርሃነ መስቀል፡- አሁን የተፈጠረው ነገር በተከሰተበት ወቅት እኔ ከአገር ውጭ ነበርኩ፤ ማህበራዊ ሚዲያውንም የመከታተል ዕድሉ ብዙም አልነበረኝም:: ከመጣሁ በኋላ ግን የተወሰኑ ነገሮችን ለማንበብ ሞክሬያለሁ:: በህውሓትና በሌሎች አባል ድርጅቶች መካከልም ይሆን በኦዴፓ አባላት መካከል የተፈጠረው ነገር አገርንም ማዕከል ያደረገ ከሆነ የማይፈታ ነገር የለም:: ውይይት ይፈታዋል:: ትግል መሆን ያለበት በጉልበት አይደለም:: ትግል መሆን ያለበት በአስተሳሰብ የበላይነት ነው:: ቀርቦ በመወያየትና በመነጋገር ነው:: በእኔ እምነት ሚዲያዎች ካላስጮኹት በስተቀር ያን ያህል ችግር አለ ብዬ አላምንም:: ለምሳሌ በኦዴፓ ውስጥ ተፈጠረ የሚባለው ነገር እኔ ውሃ የሚያነሳ ነው ብዬ አላምንም:: ዶክተር አብይና አቶ ለማ ብዙ አብረው የታገሉ፤ አሁን ያየነውን ለውጥ መሰረት የሆኑ ሰዎች ናቸው:: ነገር ግን ሁለት እግር አብሮ እየተጓዘ፤ እድሜውን ልክ ላይለያይ እንኳ ቁርጭምጭሚት ለቁርጭምጭሚት ይጋጫል::
ሊቋሰሉም ይችላሉ:: ነገር ግን ተመልሰው አብረው ይጓዛሉ:: ለምሳሌ ሰሞኑን አቶ ለማ በአገር ጉዳይ ላይ ለመወያየት አሜሪካ ሄደዋል፤ ይሄ ለእኔ የግጭት ምልክት አይደለም:: ይልቁንም አገርን በጋራ የመምራት ምልክት ነው:: እኔ የሚያሳስበኝ ጥላቸው ላይ ብቻ ፀሐይ እንዳይወጣ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ምን ማለት እንደሆነ ትንሽ ሊያብራሩልኝ ይችላሉ?
ዶክተር ብርሃነ መስቀል፡- አለመስማማታቸው ላይ ፀሐይ አይውጣበት ስል ችግሮቻቸውን በፍጥነት ለመፍታት ወደ ውይይት መምጣት አለባቸው ማለቴ ነው:: ቶሎ ከተወያዩ ህዝባቸውን ብቻ ማዕከል አድርገው ከሠሩ፤ ከእኔ በስተጀርባ ስንት ተከታይ አለ የሚለውን ነገር ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ መድረክ አምጥተው ሐሳባቸውን በነፃነት ሀገርና ህዝብን አስቀድመው ከተወያዩ በአንድ ቀን ሊፈቱት ይችላሉ የሚል እምነት ነው ያለኝ:: በጥቅሉ በኦዴፓ አመራሮች መካከል ሚዲያው በሚያራግበው ልክ ልዩነት አለ ብዬም አላምንም:: በሌላ በኩል ህውሓት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ለዚህች አገር እዚህ መድረስ የራሱ አስተዋጽኦ አለው:: አስተዋጽኦውን ዜሮ ማድረግም የለብንም:: በዚያው ልክ ደግሞ በድርጅቱ ውስጥ አስነቃፊ ደግሞ አለ:: አስነቃፊውን እየለዩ፣ ነገር ግን ደግሞ አገርን እያስቀደሙ፤ ጉዳዩን ወደ መድረክ እያመጡ ከሄዱ እኔ አሁንም እሱም መፍትሄ ያጣል የሚል እምነት የለኝም:: መፍትሄ የሚያጣው ዘራፍነት ከታከለበት ነው::
አዲስ ዘመን፡- እንዴት?
ዶክተር ብርሃነ መስቀል፡- ይህም ሲባል እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን፤ እኔ ያልኩት ካልሆነ አገር ትጠፋለች የሚል አስተሳሰብ ከመጣ ከየትኛውም ወገን ማለት ነው:: ወደ መሐል ሜዳ ካልመጣን ሀገር ማስቀጠል አይቻልም:: በአንድ ወገን ብቻ የሚደረግ ጨዋታ ያጠፋፋናል:: ከ80 በላይ ብሔረሰብ ባለበት አገር ውስጥ፤ የተለያየ ሃይማኖት ባለበት አገር ውስጥ ፤ እንዲህ አይነት መቋሰልና አልፎ ተርፎም እስከመጠፋፋት የደረሰ ቁርሾ በተፈጠረበት አገር ውስጥ እኔ ብቻ እመራለሁ የሚል ካለ ማሰቢያ የተነፈገው ነው ማለት ይቻላል:: ስለዚህ መግባባት የሚቻለው ወደ መሐል ሜዳ በመምጣት በውይይት ለመፍታት ስንወስን ነው:: ይህ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ:: እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን የሚለው ሰው አድሮ ሲነሳ ሂሳቡ አደገኛ እንደሆነ ይረዳል ብዬ አምናለው:: ሂሳብ አወራረዱም ጥሩ አይሆንም:: መጠፋፋት ያመጣል:: ወደዚያ ግን መሄድ የለብንም:: በአንድም በሌላ መንገድ እርስ በርስ የተዋለድን የተሳሰርን እንደመሆናችን ልዩነታችንን አጥብበን ወደ ጋራ ነገር መምጣት አለብን:: ከዚህ አንፃር በሁሉም ብሔረሰብ ውስጥ ያሉ ምሁራን ድርሻቸው ከፍተኛ ነው:: ሳይንሳዊ ጫናም መፍጠር አለባቸው::
አዲስ ዘመን፡- የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውህደት አህዳዊ ሥርዓትን ይመልሳል ብለው የሚከራከሩ ሰዎች አሉ፤ በሌላ በኩል ህዝቡን አስቀድሞ ማወያየት ይገባው ነበር ብለው የሚወቅሱ አካላት አሉ:: እርሰዎ እነዚህን ሐሳቦች ይቀበላሉ?
ዶክተር ብርሃነ መስቀል፡- በመጀመሪያ ደረጃ ህዝብ አልተወያየም የሚለው ነገር ለእኔም ግራ የሚያጋባ ነው:: በመሰረቱ እንዴት ነው ፓርቲ ህዝብን የሚያወያየው? መንግሥት እኮ አይደለም፤ ፓርቲ የሚያወያየው አባላቱን እንጂ ህዝብን አይደለም:: ከዚያ በኋላ ነው ወደ ህዝብ ሊሄድ የሚችለው:: ህዝቡም የማይቀበለው ከሆነ በድምፁ ይጥለዋል:: እኔ አሁንም አልገባ ያለኝ ነገር የሚመለከታቸው ሰዎች እያሉ እዚህ ፓርቲ ውስጥ አባል ያልሆነ አካል ተቆርቋሪ ሆኖ ሃሳብ መስጠቱ ነው:: እስቲ ምን አገባቸው? በጣም ይገርመኛል! ለምሳሌ ቅንጅት ስለአዴፓ ምን አገባው፤ ይልቁንም ተፎካካሪ ሆኖ ለመምጣት ራሱን ማጠናከር ነው የሚጠበቅበት:: እንዴያውም የኢህአዴግ መዳከም ለዚህኛው ፓርቲ ዕድል ሊሆነው ይችላል:: ብልጽግና የፈለገውን ቢሆን መጨነቅ የሚገባው አባል ድርጅቶቹ ናቸው::
ስለዚህ እኔ እንደምሁር አህዳዊ ሥርዓት ይመጣል የሚለው ነገር ሊሆን ቀርቶ ይታሰባል የሚል እምነት የለኝም:: ከዚህ በኋላ ከ80 በላይ ብሔረሰብ ውስጥ ሆነ የነቃና መብቱን የሚጠይቅ ህዝብ ይዘን ህብረብሔራዊ ፌደራሊዝም ብቸኛው አማራጭ ነው የሚል እምነት አለኝ:: ሁላችንም ስንግባባ አገር እንሆናል፤ ሳንግባባ ሀገር ይፈርሳል:: ስለዚህ ማንም እኔንም አንቺም ጨፍልቆ አህዳዊ ሥርዓት እፈጥራለሁ ቢል አንቺንም በራስሽ መንገድ ትሄጂያለሽ እኔም በመሰለኝ እሄዳለሁ፤ አገር የምትባል ነገር አይኖረንም ማለት ነው:: ስለዚህ ይሄ አስተሳሰብ የማይመስልና ሊሆንም የማይችል ነው:: በአጠቃላይ አንዱ በሌላው ተጨፍልቆ የቀደመው ሥርዓት ይመለሳል የሚል እምነት የለኝም::
አዲስ ዘመን፡-በአገር ውስጥ ያለው የፖለቲካ ትኩሳት ወደ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተሻገረ ቁጥር የትምህርት ሂደቱ ላይ አሉታዊ ሚና ማሳረፍ ከጀመረ ውሎ አድሯል፤ እርሰዎ እንደ አንድ አካል ይህ ችግር በዘላቂነት በምን መልኩ ሊፈታ ይገባል ይላሉ?
ዶክተር ብርሃነ መስቀል፡- በመጀመሪያ ደረጃ ማንም ፖለቲካ እንቅስቃሴውን የሚጀምረው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ነው:: ምክንያቱም በተቋሙ ውስጥ ያሉት አፍላ ወጣቶች ነገሮችን በስሜት ተነስተው ይከተላሉ ብሎ ስለሚያምን ነው:: ለምን ከምሁሩ ወይም ከባለሀብቱ አይጀምርም? ወጣትን የሚመርጠው በቀላሉ ስስ ብልቱን ነክቶ ወደአልሆነ ሁኔታ መግፋት ይቻላል ብለው ስለሚያምኑ ነው:: ከዚያም አልፈው ምንም የማያውቁ የ1ኛና የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎችን ሲይዙ አይተናል:: ይህንን ተግባር የሚፈፅሙት ሞራል አልባዎች ናቸው ባይ ነኝ:: በሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቶቻችን በጥቃቅን ነገሮች የሚባሉ ሳይሆኑ ሁሉንም ብሔር የእኔ ብለው ተቀብለው እንዲኖሩ ነው ማስተማር የሚገባን::
እኔ ማኔጅመንት የማስተምረው ልጅ ተመልሶ መንደሩን እንዲመራ ሳይሆን አገርን ብሎም አለምን እንዲመራ ነው:: ልጆቻችን በመንደር እንዲቀሩ አይደለም ማስተማር ያለብን:: ስለዚህ ከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን በአስተሳሰብ የበላይነት፣ በእውቀት የበላይነት የምንፋተግባቸው፤ ችግሮች ሲመጡ ግጭትን እንዴት ማስወገድ እንደምንችል የምንማርባቸው ቦታዎች ነው ሊሆኑ የሚገባው:: ይሁን እንጂ በትንንሽ ነገሮች እኛ ራሳችን ግጭት ፈላጊዎች ከሆንን የመማራችን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይገባል:: ነገ አገር እንደአገር ይቀጥላል:: እኛ ግን መንገዳችን ይደናቀፋል:: ምንአልባት በኛ መንገድ መደናቀፍ ተጠቃሚ የሚሆኑ አካላት ሊኖሩ ይችላሉ:: ስለዚህ ማን ምን አስቦ ነው ይህንን አጀንዳ ይዞ የመጣው የሚለውን መፈተሽ ይገባናል:: ስለዚህ መምህሮቻችን ተማሪዎቻቸውን ቁጥር መደመርን እንዲያውቁ ከማድረግ ባለፈ ባለራዕይ እንዲሆኑ መቅረፅ ይገባናል::
አዲስ ዘመን፡-አሁን ደግሞ እርሰዎ ወደሚመሩት ወደ ዩኒቨርሲቲ ጉዳይ እንመለስ፤ ኮተቤ ሜትሮፖሊቲያን ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ ከሚባሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንዱ ቢሆንም የእድሜውን ያህል ስመገናና መሆን ያልቻለበት ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ? እርሰዎ ወደተቋሙ ከመጡ በኋላ ይህንን ስሙን ለመቀየርና መፍትሄ አምጪ ተቋም ለማድረግ ምን ያህል ሠርተዋል?
ዶክተር ብርሃነ መስቀል፡- ተቋሙ እድሜው 70 ዓመት ነው:: በዚህ ልክ ደግሞ በየጊዜው ጀርባዬን እከከኝ የሚል አዛውንት ነው:: በአንድ በኩል ሜትሮፖሊቲያን ስንል ገና ድክ ድክ በማለት ላይ ያለ የሁለት ዓመት ተኩል ልጅ ነው:: ሊወቀስም ሊወደስም የሚያስችለው እድሜው አይደለም:: በሌላበኩል ደግሞ ከጣሊያን ወረራ ጀምሮ የመጣ ተቋም ነው:: ሁሉ ነገሩ አሮጌ ነው፤ አሮጌ ህንፃ፣ አሮጌ አስተሳሰብ ያረጀ ዛፍ ነው ያለው:: በ70 ዓመት የደነደነ ችግር በሰባት ወራት ወይም በሰባት ዓመት መቀየር አዳጋች ነው:: በዚህ ጊዜ ውስጥ ብዙ ነገር መቀየር በጣም አስቸጋሪ ነው:: ከዚህ አንፃር ለረጅም ዓመታት ትኩረት ተነፍጎት የቆየ ተቋም ነው:: ሲፈለግ ትምህርት ቢሮ ውስጥ ይወተፋል፤ ከዚያ ደግሞ ከዚያ ይውጣ ሌላ ቦታ ይደረጋል፤ መሪውን ማን እንደሚመራውና ማን ሃላፊ እንደሆነው የማይታወቅበት፣ ግለሰቦች በጎ ፍቃዳቸውን የሚያንፀባርቁበት ተቋም ነበረ:: ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባትም ወደ ዩኒቨርሲቲው ከመጣን በኋላ ተጠሪነቱ ለአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እንዲሆን ተደረገ::
በወቅቱ ትህምርት ቢሮው ይህንን ተቋም ለመምራት የሚያስችል ብቃት የለውም ብለን ጮኸናል:: ቢሮው ራሱ እኛ ጋር መጥቶ ለመምራት ተቸግሮ ነበር:: እኛም ወደ ሌላ እንዳንሄድ በደንብ ታስረን ቆየን:: ስለዚህ ከትምህርት ቢሮ ምንም ሳናገኝ ከ1ዓመት ተኩል በላይ አለፈ:: ከዚያ በኋላ ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ እንደምንም በከንቲባ ጽህፈት ቤት ሥር እንዲገባ አደረግን:: የሚገርመው ግን በሦስት ዓመት ውስጥ ሦስት ጊዜ ነው ቦርድ የተቀየረው:: በከንቲባ ጽህፈት ቤት ሥር እያለን በርካታ የጀመርናቸው ሥራዎች ነበሩ:: በተለይም እኔ ወደ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትነት ስመጣ ከራሴ አቅም በላይ ፈጣሪ እንደሚያግዘኝ እምነት ነበረኝ:: ተቋሙ ሜትሮፖሊቲያን ከሆነ በኋላ ትልልቅ ሥራዎችን ሠርተናል:: አንድ ተቋም ነበር የተረከብኩት አሁን ግን ወደ አራት ማሳደግ ችለናል:: 150 ሠራተኞችን ነበር የተቀበልኩት አሁን ወደ 600 ሠራተኞች ከፍ ብለዋል:: የመምህራኖቻችንም የትምህርት ደረጃ ሁለተኛ ዲግሪ ብቻ ነበር:: አሁን ዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው በርካታ መምህራን አሉን:: የትምህርት ፕሮግራሞቹ በጣም ውስን ነበሩ አሁን በጣም በርካታ ናቸው:: ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ መሥራት ችለናል:: ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በማካሄድ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት የበኩላችንን ሚና ተጫውተናል::
አሁን ደግሞ ወደ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እየሄደ ነው:: ይህም አንድ ተስፋ ሰጪ ነገር ነው:: ምክንያቱም በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እይታ ውስጥ የመግባት ዕድል ይኖረናል:: ከዚህ አንፃር አሁን ላይ አሮጌ ህንፃዎች አሉ፤ ሬጅስትራር አገልግሎት የሚሰጠው አሁንም በአንዲት በተጨናነቀች ክፍል ውስጥ ነው:: ህንፃ እንገንባ ብለን ስንት ጊዜ ዲዛይን ሠርተን አቀረብን፤ የግንባታ ጉዳይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽን ቢሮ ሥር እንዲሆን ተደረገ በዚህ ምክንያት የዛሬ አምስት ዓመት የተጀመረ አንድ ህንፃ እስካሁን አላለቀም::
አዲስ ዘመን፡- ለዩኒቨርሲቲው አለማደግ የከተማ አስተዳደሩ በሚገባ አለመደገፍ ነው እያሉ ነው?
ዶክተር ብርሃነ መስቀል፡- በእኔ እምነት አደረጃጀቱ ነው ዋነኛ ምክንያት:: ስለዚህ ከተማ አስተዳደሩን እንዳንነቅፈው በአንድ በኩል እያገዘን ነው:: አሁን እንኳ ወደ ሚኒስቴሩ ሥር እንድንሄድ የከንቲባው ከፍተኛ ድጋፍ ታክሎበታል:: ይህ የለውጥ አስተሳሰብ ነው:: በአጠቃላይ ግን አሠራሩ እና አደረጃጀቱ የሚያሠራ አልነበረም:: ተቋሙን ሊያራምደው አልቻለም:: ጠርንፎ ነው የያዘው:: በዚህ ምክንያት ማኔጅመንቱ ሊወቀስ አይችልም:: እንዳውም በአስር ዓመት የሚሠራ ሥራ በሁለት ዓመት ተሠርቷል:: አሁን ትልቁ ፈተና የሆነብን ነገር ደመወዙ ሳቢ ባለመሆኑ ሦስት ጊዜ ማስታወቂያ አውጥተን የሚወዳደር ሰው አጥተናል:: ሠራተኛ መቅጠር አልቻልንም:: ሌላው ቢቀር በአሠራሩ ምክንያት የተሻለ ጥበቃ ማምጣት አልቻልንም:: እነዚህ ነገሮች ተደምረው እኛ ልንሮጥበት በምንፈልገው መጠን ሊያስሮጡን አልቻሉም:: ህንፃ ተከራይተን ነው እያስተማርን ያለነው:: ለምንስ ነው የመንግሥት ገንዘብ ለህንፃ ኪራይ የሚወጣው? ብለን ተሟግተናል:: አሁን ግን ይህንን ችግር ሊፈታ በሚችል መልኩ አደረጃጀታችን በሚኒስቴሩ ሥር እንዲሆን ተደርጓል:: የፋይናንስ ግንኙነታችንም በቀጥታ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ስለሚሆን ብዙ ነገሮች እንሠራለን ብለን እናምናለን:: በአጠቃላይ አሁን ያለው ነገር ተስፋ ሰጪና ተቋሙን ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እኩል ለመወዳደር የሚያስችለው ነው ባይ ነኝ:: በተለይም ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ከከተማዋ አልፎ ለአገሪቱ ችግር ፈቺ ሥራዎችንና ምሁራንን በማፍራት አዎንታዊ ሚና ይኖረናል የሚል እምነት አለኝ::
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቤዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ:: ዶክተር ብርሃነ መስቀል፡- እኔም አመሰግናለሁ::
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ህዳር 27/2012
ማህሌት አብዱል