የተክለሃይማኖት አካባቢ ነዋሪው አቶ ጥላሁን ወልደዳዊት፣ ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩት በድለላ ሥራ ነበር፤ አንድ ምሽት ግን ወደ ቤት እየሄዱ ሳለ መኪና ይገጫቸዋል። በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በአቤት ሆስፒታል አልጋ ከያዙም ሦስት ወር ሆኗቸዋል። ከጉልበታቸው በታች በደረሰባቸው ጉዳትም በመታከም ላይ ይገኛሉ።
ታካሚው፣ በመዲናዋ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን በአስፓልት መዘርጋትና የትራፊክ መጨናነቁን ማስወገድ ይገልፃሉ። አሽከርካሪዎችም ተጠንቅቀው መንዳት፣ ከመጠጥና ጫት እንዲሁም መሰል ሱሶችም መቆጠብ እንዳለባቸው ያስረዳሉ። መንግሥት በመኪና አደጋ ለተጎዱ ነፃ ህክምና በመፍቀዱ በህክምና ወጪ ስጋት የሆነባቸው ችግር እንደሌለም ነው የሚናገሩት።
በደብረብርሃን ከተማ ነዋሪ የሆነችው ወይዘሪት ዕሴት አዲሱ በበኩሏ፤ በከተማው በአንድ ምግብ ቤት በአስተናጋጅነት ትሠራ ነበር፤ ከሥራ ቦታዋ ከምሽቱ 4፡00 አካባቢ ወደ ቤቷ ለመሄድ በመንገድ ማቋረጫው ስትሻገር ነው በፍጥነት የመጣ መኪና የገጫት። በአካባቢው ባለ የህክምና ተቋም መጠነኛ ህክምና ተደርጎላት ወደ አቤት ሆስፒታል በሪፈር እንደተላከችና እግሯ ላይ የተወሰነ ጉዳት እንደደረሰባት ትናገራለች። አደጋው የደረሰባት ጥቅምት 17 ቀን ሲሆን፣ በሆስፒታሉ አልጋ ይዛ ህክምና ከጀመረች ከአንድ ወር በላይ ሆኗል።
የላዳ ታክሲ አሽከርካሪ አቶ አበበ ፋንታ በመርካቶ ጎጃም በረንዳ አካባቢ በብዛት ከቀኑ ስድስት ሰዓት እስከ ምሽት ስድስት ሰዓት ይሠራሉ። የትራፊክ አደጋ ችግር ከሆኑት መካከል ዋናው ፍጥነት መሆኑን በመጥቀስ፤ ሱሰኝነትና ግዴለሽነት እንዲሁም የተሽከርካሪ ማርጀት ብሎም ትርፍ መጫንና የትራፊክ ቁጥጥር ማነስ እንደሆነ ያመለክታሉ።
በትራንስፖርት ሚኒስቴር የኮሙዩኒክሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ጸጋዬ፣ ‹‹በያዝነው የኅዳር ወር ሀገር አቀፍ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ንቅናቄ ‹‹እንደርሳለን›› በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ መሆኑንና ዋና ዓላማው በሰውና በንብረት ላይና በሰው አካል ላይ ጉዳት እያደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ከመከላከልና ከመቀነስ ጋር የተያያዘ ነው›› ሲሉ ጠቅሰው፤ የአሽከርካሪዎች ፍጥነት በህይወትና በንብረት እያደረሰ ያለውን አደጋ ለመቀነስና ግንዛቤ ለመስጠት እንደሆነ ተናግረዋል።
እርሳቸው እንደገለፁት፤ ትራንስፖርት ትልቅ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ እንዳለው ሁሉ አጠቃቀሙም ጥንቃቄ ከጎደለው ከፍተኛ አደጋ የሚያደርስ ነው። እስካሁን ድረስ በ10ሺ ተሽከርካሪ 43 ሰው እየሞተ ያለውን ወደ 27 ሰው ለማውረድ ታቅዶ አልተሳካም፤ ስለዚህ አደጋን ሊቀንሱ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ በተሽከርካሪዎች፣ በተሳፋሪዎችና በእግረኞች ላይ የተሽከርካሪ ብቃት ላይ መሠረት ያደረገ ሀገራዊ ንቅናቄ ማድረግ ይገባል።
በተለይም ፍጥነት ትልቁ ቁጥር አንድ ገዳይ እንደመሆኑ የፍጥነት ወሰንን የሚገድብ መመሪያና ደንብ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም አሽከርካሪ የሚጠቀመውን የመቀመጫ ቀበቶን ሁሉም ተሳፋሪዎች የሚጠቀሙበት መመሪያንም ተግባራዊ ማድረግ እየታሰበ መሆኑን አቶ እንዳልካቸው አስታውቀዋል።
‹‹በሀገራችን በአንድ ዓመት ውስጥ እስካሁን ባለን መረጃ 5ሺ ያህል ዜጎች በትራፊክ አደጋ ሲሞቱ፣ እስከ 15ሺ የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ይደርስባቸዋል። በሚሊዮኖች ብር የሚገመት ንብረትና የመንገድ መሠረተ ልማቶችም ይወድማሉ፤ በዚህ ከቀጠለ ከየትኛውም ገዳይ በሽታ በላይ ሆኖ ነው የሚታየው›› ይላሉ።
ባለፉት 11 ዓመታት በፍጥነት በማሽከርከር ብቻ 936 ሺ 13 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ 872 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ንብረት መውደሙን የጠቆሙት አቶ እንዳልካቸው፣ በአዲስ አበባ፣ በጅማ፣ በባህርዳርና በመቀሌ ከተሞች ከ10 ሺ ሰዎች በላይ በነቂስ ወጥቶ የሚሳተፉበት ሀገራዊ ንቅናቄ እንደሚካሄድም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 23/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ