የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪው ኢንጂነር ሺበሺ ካሳ ከዚህ በፊት የጤና ምርመራና ህክምና ለማድረግ የግል ጤና ተቋማትን እንደማይደፍሩ ይናገራሉ። ለዚህም ምክንያታቸው ተቋማቱ ለምርመራና ህክምና የሚያስከፍሉት ገንዘብ ከፍተኛ መሆኑ ነው። የግል ጤና ተቋማት ነፃ የጤና ምርመራና የህክምና አገልግሎት ከሰሞኑ በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚሰጡ ሰምተው በስፍራው ተገኝተዋል።
የአይን ምርመራ በማድረግም እይታቸው ያለበትን ደረጃ አውቀዋል። ለማንበብ ብቻ መነፅር እንደታዘዘላቸው በቀጣይም ምን አይነት ጥንቃቄ ለአይናቸው ማድረግ እንደሚገባቸው በሃኪሞች ተገቢውን ምክር እንዳገኙም ይገልፃሉ።
በግል ጤና ተቋማት የተጀመረው የነፃ ጤና ምርመራና ህክምና አገልግሎት ይበልጥ ሊበረታታ እንደሚገባው የሚናገሩት ኢንጂነር ሺበሺ፤ እንዲህ አይነቱ አገልግሎት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ቢቻል በየአራት ወሩ ቢሰጥ ተገቢ መሆኑን ይጠቁማሉ። አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኝ ከመሆኑ አኳያና በግል ጤና ተቋማት ከፍሎ የመመርመርና የመታከም እድል አያገኝም ይላሉ።
በጤና ተቋማቱ በኩል የተጀመረው አገልግሎት ብዙሃኑን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ያብራራሉ። የግል ጤና ተቋማትም እያደረጉ ያለው አስተዋፅኦ መደነቅ ያለበትና በመንግስት ድጋፍ ሊያገኝ እንደሚገባም ያመለክታሉ።
በዳልያ ልዩ የአይን ክሊኒክ የአይን ሃኪም ወይዘሪት ሄኖን ወልዴ እንደሚሉት ፤ በግል ጤና ተቋማት አማካኝነት የተዘጋጀው ነፃ የጤና ምርመራና ህክምና አገልግሎት ሁሉንም በተለይም ከፍለው አገልግሎቱን ማግኘት የማይችሉ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል።
ከነፃ የጤና ምርመራና ህክምና አገልግሎቱ ባሸገርም ተቋማቱ የደረሱበትን የህክምና ደረጃ ለተጠቃሚዎቻቸው የሚያሳዩበት እድል ይፈጠራል። የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችም በምን አይነት የህክምና መሳሪያዎች ምን አይነት ህክምናና የት ሄደው መታከም እንዳለባቸው መረጃ ማግኘት ያስችላቸዋል።
እንዲህ አይነቱ አገልግሎት የግል ጤና ተቋማት እየተወጡ ያሉት ማህበራዊ ሃላፊነት የሚያሳይና በቀጣይም ጉዳዩ ሊበረታታ ይገባል ያሉት ወይዘሪት ሄኖን፣ ከነፃ የጤና ምርመራና ህክምና አገልግሎት በተጨማሪ የተካሄደው ኤግዚቢሽንና ኤክስፖም የመጀመሪያ ከመሆኑ አኳያ በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ይላሉ።
የዓይን ህክምና ማእከሉም በተመሳሳይ መድረኮች ላይ በመሳተፍ የደረሰበትን የህክምና ደረጃ ለህብረተሰቡ በማስተዋወቅ የነፃ ጤና ምርመራና ህክምና አገልግሎቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጤና ማጎልበትና በሽታ መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌቱ ቢሳው እንደሚሉት፤ እንዲህ አይነቱ የጤና ኤክስፖና ኤግዚቢሽን ህብረተሰቡን ለጤና ምርመራና ህክምና አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል። የግል ጤና ድርጅቶችም አገልግሎታቸውን በተመለከተ ለህብረተሰቡ ስለተቋማቸው በቂ መረጃ ለመስጠት ያስችላቸዋል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ መድረኩ የግል ጤና ተቋማት በተለይም ከፍለው የጤናቸውን ሁኔታ ማወቅና መታከም ለማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ነፃ የጤና ምርመራና ህክምና አገልግሎት በመስጠት ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፣ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባውና መንግስትም ለግል ጤና ተቋማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 23/2012
አስናቀ ፀጋዬ