አዲስ አበባ፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ባለሥልጣን በተያዘው በጀት እየሰፋ ከመጣው ከተማና ከህንፃዎች ዕድገት ጋር የሚሄዱ 200 የእሳት ማጥፊያ መሣሪያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታወቀ።
የባለሥልጣኑ የእሳትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር ተሰማ ነጋሽ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት የእሳት ማጥፊያ መሣሪያዎቹ (ሃይ ድራንት) በ 8ሚሊዮን 740 ሺ ብር የተገዙ ሲሆን፣ ከከተማዋ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣንና መንገዶች ባለሥልጣን ጋር በመቀናጀት በተመረጡ ቦታዎች ይተከላሉ።
የእሳት አደጋ ቃጠሎ በተነሳ ጊዜ ውሃ የምናገኝበት ሁኔታ የነበረ ቢሆንም ብቁ ስላልሆነና የከተማው መስፋፋትም የእሳት ማጥፊያ መሣሪያዎች ያልተተከለባቸው በርካታ አካባቢዎች ስላሉ ቦታዎች ተለይተው እንደሚተከሉና በዋናነት ብዙ ነዋሪዎች ባሉባቸው ሠፋፊ የጋራ መኖሪያ ህንፃዎች፣ በትላልቅ ሆቴሎች አካባቢ እና ፋብሪካዎች ያሉበት አካባቢ ከሚተከሉባቸው ዋናዎቹ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ቀደም ሲል ከተተከሉት መካከል አንዳንዶቹ የውሃ ኃይላቸው ያነሰ ውሃ መስጠትም ያልቻሉ በመኖራቸው ከመንገዶች ባለሥልጣንና ከውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ጋር እየተነጋገርን ይሄንን እናስተካክላለን ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር በተለያዩ ቦታዎች ተተክለው የነበሩትን የእሳት ማጥፊያ መሣሪያዎች የማደስና አገልግሎት የማይሰጡትን አገልግሎት ወደ ሚሠጡበት በመውሰድም የሚሠሩበትን ሁኔታም እንደሚመቻችና አምስት የእሳት መከላከያ ማሽነሪዎችም መገዛታቸውንም አክለው ገልፀዋል።
በመዲናችን ከፍታ ያላቸው ህንፃዎች ግንባታ እየተስፋፋ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ለእዚህም እስከ 72 ሜትር ከፍታ ያላቸው የእሳት መከላከያ ማሽኖች መኖራቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ አመልክተዋል። ማሽነሪዎቹን ገጥሞ ለመጠቀም ግን ህንፃዎች ያሉበት ቦታ እነሱን መያዝ የሚችል የተስተካከለ ሰፋ ያለ አስፋልት መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።
ከማሽነሪዎች መሟላት ጋር ተያይዞ አባሎችን በየጊዜው በሥልጠና የማዳበር ሥራ እየተሠራ መሆኑንና በየጊዜው በተለይም በህንፃዎች ከፍታ ላይ ሥልጠናዎች እየተሰጠ መሆኑን አስታውቀው፣ ሥራው በአንድ ሥልጠና ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን ሁል ጊዜ ልምምድ የሚያስፈልገው ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 23/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ