• የዓለም የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች ቀን ተከብሯል
የመንገድ ትራፊክ አደጋ የሚያስከትለውን የህይወት መጥፋት፤ የአካል መጉደል እና የንብረት ውድመት ለመቀነስ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቅንጅታዊ አሰራርን በመዘርጋት እየሰራ መሆኑን የኢፌዴሪ ትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የዓለም የመንገድ ትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች ቀን ትናንት በኢትዮ-ኩባ አደባባይ ተከብሯል፡፡
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢፌዴሪ ትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፣ የቀኑ ማስታወሻነት በየዓመቱ ህዳር ወር በገባ በሶስተኛው እሁድ የዓለም የመንገድ ትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች ቀን ሆኖ እንዲከበር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ነው፡፡
እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ከመቀነስ አንጻር ጉዳቱን እና ተጎጂዎችን ለአንድ ቀን ብቻ አስቦ መዋሉ የሚኖረው ፋይዳ ዝቅተኛ ነው ያሉት ወይዘሮ ዳግማዊት “በህዳር ወር የሚገኙትን ቀናቶች በዋናነት “እንደርሳለን” በሚል መሪ ቃል ፍጥነትን ባለመቆጣጠር፤ ተሽከርካሪን በአግባቡ ባለማስመርመር እና ባለማስጠገን፤ የደህንነት ቀበቶን ሁል ጊዜ እና በአግባቡ ባለመጠቀም፤ በግንዛቤ እጥረት፣ የሚወጡ ህጎችን በአግባቡ ባለመተግበር እና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች የተነሳ እየተከሰተ የሚገኘውን የትራፊክ አደጋ ለመቀንስ እና የህብረተሰቡ ግንዛቤ ለማሳደግ እየሰራን እንገኛለን” ብለዋል፡፡
መስሪያ ቤቱ ከጳጉሜ 2011 ዓ.ም እስከ ህዳር 2012 ዓ.ም ድረስ ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር በህብረተሰቡ ዘንድ ስለአደጋው አስከፊነት ሁሉን አቀፍ የግንዛቤ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ ከዚህም በተጨማሪ የመንገድ ደህንነት ትምህርት በመደበኛ ካሪኩለም እና በጎልማሶች የትምህርት ማዕቀፍ ውስጥ እንዲካተት ለማድረግ፤ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ፤ የተሽከርካሪ ምርመራ እና የትራፊክ ቁጥጥር ለማዘመን እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ለአደጋ አጋላጭ የሆኑ 2000 ኪ.ሜ መንገዶች ተለይተው የማሻሻያ ሥራ እየተሰራ እንዳለም ጠቁመዋል፡፡
የተለያዩ ተቋማትን እና ማህበራት ወክለው በበዓሉ ላይ የተሳተፉ አካላትም ህብረተሰቡ ከትራፊክ አደጋ ራሱን እንዲጠብቅ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ሁሉም የድርሻቸውን ለመወጣም ቃል ገብተዋል፡፡
በመንገድ ትራፊክ አዳጋ በ2011 ዓ.ም ብቻ 4ሺ597 ሞት፤ 7ሺ047 ከባድ እና 5ሺ949 ቀላል የአካል ጉዳት እና ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ የንብረት ውድመት መከሰቱን ከተቋሙ የፌስቡክ ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 22/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር