– በሲዳማ ክልል የፓርቲው ቅርንጫፍ እንደሚከፈት አስታወቁ
አዲስ አበባ፡- የብልጽግና ፓርቲ እየተበራከቱ የመጡ የህዝብ ፍላጎቶችን መመለስ በሚያስፈልግበት ወቅት የተወለደ ፓርቲ መሆኑን የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ፡፡ የሲዳማ የክልልነት ሂደት ሲጠናቀቅም በክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት እንደሚከፈት አስታውቀዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው አቶ ደስታ ሌዳሞ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት በርካታ የህዝብ ፍላጎቶች ታይተዋል፤ ጥያቄዎችም ተነስተዋል፡፡ ይህን ሊመልስ የሚችል ቁመና ያለው ፓርቲ አስፈላጊ እንደመሆኑም የብልጽግና ፓርቲ ወቅቱ የፈጠረው ፓርቲ መሆኑ እሙን ነው፡፡ የብልጽግና ፓርቲን በመመስረት ሂደትም የሲዳማ ተወላጅ የደኢህዴን አባላት ተሳታፊና የውሳኔው አካል እንደመሆናቸው የሲዳማ የክልልነት ሂደት ሲጠናቀቅ በፓርቲው ሕገ ደንብ መሰረት የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በክልሉ ይኖራል፡፡
እስካሁን የመጣንበት ሁኔታ አገራችንን እዚህ ደረጃ አድርሷል›› የሚሉት አቶ ደስታ፤ ከዚህ በኋላ የአደረጃጀትና የፕሮግራም ለውጥንም ጨምሮ መሄድን የሚጠይቅ የህዝብ ፍላጎት ላለፉት ሶስት ዓመታት መታየቱን ገልጸዋል፡፡
አገራዊ አንድነትንና ብሔራዊ ማንነትን አስጠብቆ መጓዝ በሚያስችለው መልኩ የተደራጀ የፖለቲካ ድርጅት እንደሚያስፈልግ የገለፁት አቶ ደስታ ለዚህ ደግሞ ኢህአዴግ ራሱን ቀይሮና ማሻሻያዎችን አድርጎ ዝግጁ መሆኑንና በውህደቱ የተፈጠረው ብልጽግና ፓርቲም ወቅቱ የወለደው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከዚህ አኳያ በፓርቲው መርህ መሰረት የሚያሻሽላቸው የተዛነፉ ተግባራት ብቻ ሳይሆን የሚያሳካቸው ተጨማሪ ግቦችም ስላሉት፤ የሲዳማ የክልልነት ሂደት ሲጠናቀቅ ይሄንን የሚመጥን አደረጃጀት ፈጥሮ በክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ እንደሚከፈት አስታውቀዋል፡፡
እንደ አቶ ደስታ ገለጻ፤ እስካሁን በደቡብ ክልል ገዢ የሆነው ፓርቲ ደኢህዴን ነው፡፡ በዚህ ፓርቲ ውስጥ ደግሞ የሲዳማ ተወላጅ የድርጅቱ አባላት በመኖራቸው ደኢህዴን የብልጽግና ፓርቲ አባል ለመሆን ሲወስን አብረው ወስነዋል::
ሲዳማ ክልል ሲሆን ደግሞ በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት በየክልሎቹ በሚኖረው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት መሰረት የሚቀጥል ሲሆን፤ በደኢህዴን ውስጥ ያሉ የሲዳማ ተወላጆች ክልሉን የሚመጥን አደረጃጀት ፈጥረው በብል ጽግና ፓርቲ ውስጥ የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡
የድርጅቱ የእስካሁን ጉዞ ከነበሩ ጥንካሬዎችም ሆነ ድክመቶች ትምህርት የሚወሰድበት ሲሆን፤ የብልጽግና ፓርቲም ድክመቶችን አርሞ፤ መልካም ተሞክሮዎችን ደግሞ አጠናክሮ ህዝቡን አሳትፎ ሊሄድ እንደሚችል በማመን፤ አሁን ላይ ወቅቱ የሚጠይቀውን አደረጃጀትና አሰራር፤ የፕሮ ግራም ማሻሻያም ጭምር አካቶ ለመጓዝ አገራዊ
ከሆነው የብልጽግና ፓርቲ ጋር መሄዱ አዋጪ መሆኑ ላይ መስማማታቸውንም አቶ ደስታ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ፓርቲው በሲዳማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሲከፍት ተገቢው አመራር ተመድቦ ከብልጽግና ፓርቲ አገራዊ ጽህፈት ጋር ግንኙነት እየፈጠረ፤ በወረዳዎችና በዞኖችም ማስተባበሪያ ኖሮት አባላቱን አቅፎ እንደሚንቀሳቀስ አስተዳዳሪው ገልፀዋል:: ለዚህ እንዲያመች ደግሞ ወሳኙ አባላት ስለሆኑ አባላቱን በፈቃደኝነታቸው ላይ ተመስርቶ እንዳለ ይዞ የመቀጠል ሁኔታ ነው ያለው ብለዋል::
ለዚህም ቀጣይ ውይይቶችን በማድረግ አባላትን የመገንባት ስራ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፤ የሚፈጠረውን አሰራርና አደረጃጀቱን ተከትሎም አባላቱን በማንቀሳቀስ ከፍ ላለ ስራና ሃላፊነት የሚዘጋጅ ይሆናል ብለዋል፡፡
ውህድ ፓርቲው በአሉባልታ እንደሚባለው አሃዳዊነትን የሚያመጣ፣ ፌዴራሊዝምን የሚያጠፋና ብዝሃነትን የሚጨፈልቅ ወይም የብሔር ብሔረሰቦችን ጥቅም የሚያጠፋ አይደለም የሚሉት አቶ ደስታ፤ ይልቁንም በህገ ደንቡ እንደሚታየው ህብረ ብሔራዊነትን የሚያጠናክር፣ ፌዴራሊዝምንም የሚያጎለብት፣ ሚዛናዊነትን የሚያሰፍን፣ እንዲሁም አንድ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ማህበረሰብ ግንባታውን የሚያፋጥን መሆኑን አቶ ደስታ አብራርተዋል፡፡
ይህ ደግሞ እዚህም እዚያም የሚታዩ ቀውሶችን የሚያስወግድ፤ ፓርቲውም ይሄንን ለማድረግ ሚዛናዊ ቁመና እንዲኖረው የሚያደርግ ነው ያሉት አቶ ደስታ ይሄንንም የፓርቲው አባሎችና ደጋፊዎች የማስረዳት ሰፊ ስራ እንደሚከናወን ጠቁመው፤ አባላትና ደጋፊዎችም የጠራ መረጃ እንዲይዙ የሚደረግ መሆኑን አውቀው በተዛባ መልኩ በሚደርሷቸው መረጃዎች ሳይደናገሩ እንዲጠብቁ መክረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 22/2012
ወንድወሰን ሽመልስ