አዲስ አበባ፡- በ2011 በጀት ዓመት 19 ሺ 739 አባወራዎች ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ቅጥያ ተሰርቶላቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ በተያዘው በጀት ዓመትም 12 ሺ 201 አባወራዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩንም አመልክቷል፡፡
የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን የሥራ ሂደት መሪ ወይዘሮ ሰርካለም ጌታቸው በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ከሚሰራቸው ሥራዎች መካከል ፍሳሾችን ከህብረተሰቡ ሰብስቦ በማጣራት መልሶ የመጠቀም ሥራ አንዱ ነው፡፡ በዚህም በ2011 ዓ.ም ላይ 19 ሺ 739 አባወራዎች ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ቅጥያ ተሰርቶላቸው ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ ሰርካለም ገለፃ፤ ህብረተሰቡ የቤት ለቤት ቅጥያ በስፋት ያለመሳተፍ ችግር ቢኖርም በተያዘው በጀት ዓመት በዋነኝነት ትኩረት በማድረግ 12 ሺ 201 አባ ወራዎችን የቅጥያ ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ተይዟል፡፡
ባለፉት አራት ወራትም የክረምት ወቅት በመሆኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሲከናወን ነበር:: በቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ውስጥ 689 አባወራዎች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
በቀጣይ በመካኒሳ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶና በአዲስ ከተማ ቅርንጫፎች ሰፊ ሥራ ለመስራት እቅድ መያዙን የጠቆሙት ወይዘሮ ሰርካለም፤ ከዚህ ቀደም ሶስት ሺ 460 ተሰርቶ ህብረተሰቡ ደጃፍ ላይ ቢደርስም ቅጥያ ያልተሰራላቸውን ማጠናቀቅ እንዲሁም በፕሮጀክት ጽህፈት ቤቶች እየተሰሩ የሚገኙ አምስት ሺ 526 ቅጥዎች ለማጠናቀቅ ይሰራል ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡ ሴፍቲ ታንከሩን ላለማፍረስ የፍሳሽ ማስወገጃ ቅጥያ ደጃፋቸው ደርሶ የማይጠቀሙበት ሁኔታ መኖር፣ የመስመር ክዳን ስርቆት፣ በመስመሮች ውስጥ የፕላስቲክ ጠርሙሶች እና የጫት ገረባና ቆሻሻዎችን መክተት እንዲሁም በህገወጥ መንገድ የፍሳሽ ማስወገጃ ቅጥያ የሚያደርጉ ግለሰቦች ለሥራው ተግዳሮት መሆናቸውን የገለፁት ወይዘሮ ሰርካለም ዘመናዊ የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓት ወጪ ቆጣቢ በመሆኑ ህብረተሰቡ በአግባቡ መጠቀም እንዳበትም አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 22/2012
መርድ ክፍሉ