ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የፖለቲካ፣ የሀይማኖትና የብሄር መልክ ያላቸው ግጭቶች ሲከሰቱ ይስተዋላል።የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴርም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል። ከዚህ ጎን ለጎን ግን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በአካባቢ ማህበረሰብ አቀፍ ስራዎች ተማሪዎች እንዲሳተፉ በማድረግ ተማሪዎችና የአካባቢው ማህረበሰብ ግንኙነት እንዲጠናከር እየሰሩ ይገኛሉ። ሰሞኑንም በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ለአርሶ አደሩ ያደረጉት ድጋፍ የዚህ አንድ ማሳያ ነው። ይህ ደግሞ በዩኒቨርስቲዎች ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የማድረግ በጎ ጅምር እንደሆነ የዩኒቨርስቲዎቹ አመራሮች ይናገራሉ።
በወራቤ ዩኒቨርስቲ የውጭና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አባስ አብዱ ሙሳ እንደሚናገሩት፤ በዩኒቨርስቲው ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ የአገር ሽማግሌዎችና የፀጥታ አካላት ከተማሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል። በዚህም በተቋሙ ትምህርት ሳይቋረጥ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የመማር ማስተማሩ እንቅስቃሴ እንዲቀጥል ማድረግ ተችሏል።የማህበረሰብ አገልግሎትም በቅንጅት ሲሰራ የቆየ ሲሆን በተለይ የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብና እገዛ የማድረግ ስራ ተከናውኗል። በዚህም ሰላምን የማስጠበቅ ስራ ስኬታማ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል። በአገልግሎት አሰጣጥ ላይም ቀደም ሲል የነበሩ ክፍተቶች ተለይተው እንዲስተካከሉ ተደርጓል።
በቅርቡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ከተከሰቱ ግጭቶች ጋር ተያይዞ በወራቤም የተወሰኑ መነሳሳቶች ነበሩ ያሉት አቶ አባስ፤ የሰላም መደፍረስ እንዳይከሰት በጋራ ምክክር መደረጉን ይናገራሉ። በአካባቢው በአየር መዛባት ምክንያት የደረሱ ሰብሎች እንዳይጎዱ ተማሪዎቹ በራሳቸው ተነሳሽነት ስምንት ሄክታር ላይ የሚገኝ ሰብልን የመሰብሰብ ስራ ሰርቷል።በቀጣይነትም ተመሳሳይ ስራዎች ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል። ይህ እንቅስቃሴ ለሌሎች ተቋማት ጥሩ ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል ይገልፃሉ። በዚህ ስራ ላይ ከሁሉም ክልሎች የመጡ ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በስራቸው ከማህበረሰቡ ጋር የመቆራኘት ነገር መፍጠሩንና ከየትኛውም ክልል ተማሪዎች ቢመጡም በአንድነት ሆነው ማህበረሰቡን ማገልገሉ አንድምታው ከፍተኛ መሆኑን ያመለክታሉ።
እንደ አቶ አባስ ገለፃ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲከፈቱ ለመማር ማስተማር፣ ለማህበረሰብ አገልግሎትና ለምርምር ስራዎች ነው። ማህበረሰቡም ከተቋማቱ የሚኖረው ተጠቃሚነት እያደገ ይመጣል።በዚህ ደግሞ የህብረተሰቡን ችግር ቀስ በቀስ መፍታት ያስችላል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ብጥብጥና ሁከት እየበረከተ ይገኛል የሚሉት አቶ አባስ በተቋማት ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች መደጋገፍና ተባብሮ መስራት ሲጠበቅባቸው ግጭት ውስጥ መግባታቸው ስህተት ነው ይላሉ። “ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፖለቲካ ማዕከልና ቅስቀሳ የሚደረግበት ቦታ እየሆነ መጥቷል።በተጨማሪም ሀሰተኛ መረጃዎችን ወደ ተቋሙ የሚያሰራጩ ግሰቦች እየበዙ ይገኛሉ። እነዚህ ነገሮች ተማሪዎች በአግባቡ ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ አድርጓቸዋል።መፍትሄ ሊሆን የሚችለው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወደ መደበኛ ስራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ መፍጠር ነው።ከሀይማኖትና ከብሄር ጋር የሚፈጠሩት ችግሮች ተገቢ አለመሆኑንም ግንዛቤ መስጠት ይገባል” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ የውጭና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ግርማ አሸብር እንደሚገልፁት፤ በተያዘው በጀት ዓመት በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ የተከሰተ የሰላም መደፍረስ የለም።ለዚህ ደግሞ የተቋሙ አመራሮች ቅድመ ጥንቃቄ አድርዋል። በተጨማሪም ከአካባቢው ማህበረሰብ፣ ከተማሪውና ከተቋሙ አመራር የተውጣጣ የሰላም ኮሚቴ እንዲቋቋም ተደርጓል። ኮሚቴው በሌሎች ተቋማት በምን ምክንያት የሰላም መደፍረስ እንደተከሰተ ክትትል በማድረግ በደብረ ማርቆስ ቅድመ ጥንቃቄ ስራ አከናውኗል።
እንደ አቶ ግርማ አባባል፤ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ የሚማሩ ተማሪዎች ወላጆች ስጋት ውስጥ እንዳይገቡ ለማድረግ ቅድመ ጥንቃቄ ስራው ጠቅሟል። ወቅትን ጠብቀው የሚነሱ ግጭቶች ላይ የተቋሙ አመራሮች ቡድን ሰርተው ግቢውን ይጠብቃሉ። የአካባቢው ፀጥታ አካላትም የተቋሙን የፀጥታ ሁኔታ እያስጠበቁ ይገኛሉ።ተማሪዎቹም በአካባቢው ያለውን ባህል ጠብቀው ማህበረሰቡን አክብረው ልምድ እንዲወስዱ እየተሰራ ይገኛል።
በአገር አቀፍ የተፈጠረው ችግር ተቋሙ ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር ጥረት ቢደረግም አንዳንድ መገናኛ ብዙሀን ብሄር ከብሄር በሚያጋጭ መልኩ ዘገባዎችን እየሰሩ እንደሚገኙ ያመለከቱት አቶ ግርማ፤ “መገናኛ ብዘሀኑ ተማሪዎችን ቃለመጠይቅ በማድረግ ብጥብጥ እየፈጠሩ ይገኛሉ” ብለዋል። መገናኛ ብዘሀኑ ላይ መንግስት እርምጃ መውሰድ ካልቻለ ተቋማቱን በሰላም ማስቀጠል ከባድ እንደሚሆንም ያስረዳሉ። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብጥብጥ በተፈጠረ ቁጥር የማረጋጋት ስራ ላይ ሲጠመዱ መደበኛ ስራቸውን እየዘነጉ መምጣታቸውንም ይገልፃሉ። በሌላ በኩል በከፍተኛ ባለስልጣናት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን አስመልክቶ የሚሰጡት መግለጫዎች ጊዜያዊ ማብረጃዎች እንጂ ዘላቂ መፍትሄ አለመሆናቸውንም ይናገራሉ።
እንደ አቶ ግርማ ገለፃ፤ በአካባቢው ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ምክንያት እህል እንዳይበላሽ ተማሪዎች በራሳቸው ተነሳሽነት አርሷአደሩን በማገዝ ምርት በመሰብሰብ ላይ ይገኛሉ። ይህ የሚያሳየው ሰላማዊ መማር ማስተማር እንዳለና ተማሪዎች ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ነው። ተማሪዎቹ ለሰብል ስብሰባ ሲወጡ የአካባቢው ማህበረሰብ እንደ አጋዥ እና እንደ ልጅ ይመለከታቸዋል።ተማሪዎች ተሰባስበው እንደዚህ አይነት ተግባር መፈፀማቸውም ለሌሎች ተቋማት ጥሩ ትምህርት ይሆናል።
ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በወቅታዊ የዩኒቨርሲቲዎች አለመረጋጋትና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚታየው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት መስተጓጎል መንስኤዎችን ከመለየት፣ የቦርዶችና የየተቋማቱ አመራሮች ችግሮችን እየለዩ በወቅቱ ከመፍታትና በሁከቱ ውስጥ ተሳታፊ በነበሩ አካላት ላይ እርምጃ እየወሰዱ ከመሄድ አኳያ ምን እየተሰራ እንደሚገኝ ትኩረት ተሰጥቶበታል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማሪያም፤ ተማሪዎች በሀገሪቱ ውስጥ የተዘራው የፖለቲካና የሃይማኖት አሉታዊ ዜና ሰለባ በመሆናቸው ችግሩን ለመፍታት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ይናገራሉ። በሀገሪቱ ውስጥ ካሉት 45 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ችግሩ የተከሰተባቸው 25 መሆናቸውንና ችግሩን ለመቅረፍ በተሰራው ስራ አብዛኞቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወደ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራቸው እንደተመለሱም አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 22/2012
መርድ ክፍሉ