ሀገሪቱ እንደ ሀገር በተመሰረተች ማግስት እኤአ በ1949 ነው ይህችን ምድር የተቀላቀሉት።እትብታቸው የተቀበረው ደግሞ እንደቀደሙት ጠቅላይ ሚኒስትሮች በባእድ ሀገር ሳይሆን በዚያው በእስራኤል ምድር ነው።ሀገሪቱን ለበርካታ ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት በመምራት የሚደርስባቸው የለም።የሊኪዊድ ብሄራዊ ፓርቲ ንቅናቄ ሊቀ መንበርም ናቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታዲያ እንዲያ በናኙባት ሀገር ሰሞኑን ደግሞ ፍርድ ቤት በሚያቆማቸው የሙስና ቅሌት ተጠርጣሪ ሆነዋል፡፡
የእስራኤል ዋና አቃቤ ህግ አቪቻይ ማንዴልብሊት ባለፈው ሳምንት በይፋ የሰጡትን መግለጫ ዋቢ ያደረጉ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች እንዳመለከቱት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ፈጽመዋል ተብለው በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ለህግ ለማቅረብ ውሳኔ ላይ ተደርሷል።ክሱ በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ የተመሰረተም ነው፡፡
ኔታንያሁና ባለቤታቸው እስራኤላዊ ዜግነት ካለው የሆሊውድ ፊልም አምራች ኩባንያ ባለቤት አርኖን ሚልቻን እንዲሁም ኔታኒያሁ ለአውስትራሊያዊው ቢሊየነር ጀምስ ፓከር ባደረጉት የፖለቲካ ውለታ ተገቢ ያልሆነ ስጦታ ተቀብለዋል በሚል የሚከሰሱ ሲሆን፣ ስጦታዎቹ ሻምፓኝ እና ሲጋራን ያካተቱ ጭምር መሆናቸውም ተጠቁሟል።ሌላው ኔታኒያሁ የሚቀርብባቸው ክስ የእስራኤሉ እለታዊ ጋዜጣ ዬዲዮት አህሮኖስ ተፎካካሪ እየሆነ የመጣውን እስራኤል ሃዮም ጋዜጣን እንቅስቃሴ ለማቀዛቀዝ እንዲሁም ያልተገባ የሚዲያ ሽፋን ለማግኘት በሚል ከዮዲዮት አህሮኖስ ጋዜጣ ባለቤት ጋር ተደራድረዋል የሚለው ነው፡፡
በኔታኒያሁ ላይ ከሚቀርቡት ክሶች በጣም ከባድ የተባለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዜቅ የተሰኘው የሀገሪቱ የቴሌኮም ኩባንያ ከፍተኛ ባለአክሲዮን ሻውል ኤሎቪትች ጋር ኩባንያው ያልተገባ ጥቅም እንዲያስገኝ የሚያስችል ፖሊሲ እስከማዘጋጀት የዘለቀ ለግል ጥቅም ያደረ ተግባር ፈጽመዋል የሚለው መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ቤኒያሚን ኔታንያሁ ግን ክሱን መፈንቅለ መንግስት ከመሞከር ጋር በማመሳሰል አጣጥለውታል።‹‹መርማሪዎቹ ከእውነታው ጋር ሳይሆን ከእኔ ጋር ናቸው፡፡›› ሲሉም ተናግረዋል።አቃቤ ህጉ ጉዳዩን ይፋ ካደረጉ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለ15 ደቂቃ ባደረጉት ንግግር ውሳኔውን ‹‹በሀሰት ላይ የተመሰረተና የፖለቲካ ፍላጎት የተንጸባረቀበት›› ሲሉ ገልጸውታል። ‹‹የመርማሪዎቹ ዋና አላማ እሳቸው የሚመሩትን ፓርቲ ከመንግስት ስልጣን ማበረር ነው።››ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የፈለገውን ያህል የፖለቲካ ግፊት ቢደረግባቸውም፣ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ምልልስ እንደሚጠብቃቸው ቢገምቱም ስልጣናቸውን ግን በጭራሽ እንደማይለቁ አስታውቀዋል።ቅጥፈት እንዲያሸንፍ እድል እንደማ ይሰጡ፣ በሀገሪቱ ህግ መሰረት አሁንም መምራታቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በሀገሪቱ ህግ መሰረት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የፈለገውን ያህል ክስ ቢመሰረትም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲወርዱ የሚያስችል ሁኔታ እንደሌለ መረጃዎች ይጠቁማሉ።ተንታኞች፣የፓርቲያቸውና የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በበኩላቸው፤ ክሱ በሀገሪቱ ከፍተኛ አለመረጋጋትን ሊያስከትል እንዲሁም ምርጫ እስከማካሄድ የሚደርስ ሊሆን እንደሚችልም እያስገነዘቡ ናቸው፡፡
በአውሮፓ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት የእስ ራኤልና ፍልስጤም ጉዳይ ተንታኙ ሁግህ ሎቫት፣ እስራኤልም ለመጪዎቹ ወራት በፖለቲካ መቻቻል ላይ ማተኮር እንዳለባት ለአልጀዚራ ጠቅሰው፤ ‹‹ወቅቱ ኔታኒያሁ ለራ ሳቸው የፖለቲካ ህይወትና ህልውና ብቻ ግብግብ የሚያደርጉበት ነው፡፡›› ይላሉ፡፡
ባለፈው መስከረም የተካሄደውን ምርጫ ተከ ትሎ ኔታኒያሁም ሆኑ ዋና ተፎካ ካሪያቸው ቤኒይ ጋንትዝ ጥምር መንግስት ለመመስረት ቢስማሙም ሀገሪቱ አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ ምርጫ ለማድረግ እየዳዳት መሆኑ ተጠቁሟል።አልጀዚራ እንደዘገበው፤ የጋንቴዝ የሰማያዊና ነጭ ፓርቲ ግን ይህን አይነት ቅሌት ውስጥ ከሚገኝ መሪ ጋር እንደማይሰራ ከወዲሁ አስታውቋል።ክስ ለመመስረት ውሳኔ ላይ መደረሱ እንደ ተሰማ ተፎካካሪ ፓርቲው ‹‹አፍንጫው ድረስ በሙስና ቅሌት የተዘፈቀ ጠቅላይ ሚኒስትር ምንም አይነት ህዝባዊም ሆነ ሞራላዊ ተክለ ሰውነት ኖሮት በእስራኤል የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ሊወስን አይችልም፡፡›› ሲል አስታውቋል።
የእየሩሳሌም ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰር ጊዲኦን ራሃት ለዥንዋ በሰጡት አስተያየት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥፋተኛ እስከሚባሉ ድረስ በስልጣናቸው ላይ ሆነው ህዝቡን ከደሙ ንጹህ ነኝ እያሉ ሊይዙ እንደሚችሉ ጠቅሰው፣ ‹‹እሳቸው ግን አሁን ለግል ህይወታቸው ነው የሚፋለሙት፤ ቀጣዩ ጥያቄ የሚሆነው ደጋፊዎቻቸው ምን ያህል አብረዋቸው ይዘልቃሉ የሚለው ነው፡፡››ሲሉ ያብራራሉ፡፡
የኔታንያሁ የሊኩድ ፓርቲ እና የቀኝ ዘመም ክንፍ የፖለቲካ አቅም ጠንካራ መሆኑ ጥርጥር እንደሌለው ራሃት ተናግረው፣ ኔታንያሁ ይህን አቅማቸውን አሟጠው በመጠቀም እስር ቤት ከመወርወር ለመዳን መፍጨ ርጨራቸው እንደማይቀር ያመለክታሉ። እርሳቸውን ሊተካ ይችላል ብለው ያሰቡትን እጩ ለመቆጣጠርም ጥበብ የተሞላበት ተግባር ከማከናወን እንደማይቦዝኑም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ሌላው በኒዮርክ ታይምስ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲ የህግ ባለሙያ ጊዲኦን ሳአር፣ በኔታኒያሁ የቀኝ ዘመም ሊኩድ ፓርቲ ውስጥ አለመረጋጋት እንደሚታይ ይጠቁማሉ።‹‹ኔታኒያሁ ባለፉት ሁለት ምርጫዎች መንግስት ለመመስረት የሚያስችላቸውን ድምጽ ማግኘት ተስኗቸዋል፤ ለሶስተኛ ጊዜ በሚካሄድ ምርጫ ያሸንፋሉ ብሎ መጠበቅ አይገባም፤ አሁን ደግሞ በሙስና ቅሌት ውስጥ ተዝፍቀዋል፡፡›› ሲሉም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ሳአር ክስ ለመመስረት ውሳኔ ላይ መደረሱ ይፋ ከተደረገ በኋላ በሰጡት አስተያየት፤ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመወዳደር ፍላጎቱ እንዳላቸው ፍንጭ ሰጥተዋል።ለጀሩሳሌም ፓስት ኮንፈረንስ በሰጡት አስተያየትና በኒዮርክ ታይምስ ላይ በወጣው ዘገባ ‹‹የሊኩድ ፓርቲን አመራር በቅድሚያ ማዘጋጀት ይኖርብናል፡፡›› ሲሉ ጠቁመው፤ በዚህም መንግስት ለመመስረት እችላለሁ፤ ይህን በማድረግም ሀገሪቱን አንድ እንደማድረግ ይሰማኛል፡፡›› ሲሉ አስታውቀዋል።
የሙስና ክሱ የኔታኒያሁ ፓርቲ ተቀናቃኙ ለሰማያዊና ነጩ ፓርቲ መልካም አጋጣሚ እየፈጠረለት ነው የሚሉ ወገኖችም አሉ።የሰማያዊና ነጩ ፓርቲ መሪ ሚስተር ጋንቴዝ ያለፈውን ሀሙስ ‹‹በእስራኤል ታሪክ አሳዛኙ ቀን›› ሲሉ ገልጸውታል።የፓርቲው ሁለተኛ ከፍተኛ ባለስልጣን ያኢር ላፒድ፣ ‹‹ኔታኒያሁ ለሀገሩ የሚቆረቆሩ ከሆነ ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቅ አለባቸው፡፡›› ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
ክስ ለመመስረት የተደረሰበት ውሳኔ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የያዙት አቋም እንዲሁም ከተለያዩ ወገኖች እየሰጡ የሚገኘው አስተያየት መቋጫ ምን ሊሆን ይችላል? በቀጣይ የምናየው ይሆናል።
ኃይሉ ሣህለድንግል