አዲስ አበባ፡- ከሀገር ውስጥ ዋጋ በታች በሆነ ዋጋ ለውጭ ገበያ ምርታቸውን የሚያቀርቡ የቅባት እህል ላኪዎችን ለማስቆም ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመም ማህበር አስታወቀ።
አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ኃይሌ በርኼ እንደገለጹት፤ ቀደም ባሉ ጊዜያት የቅባት እህል ላኪዎች ከሀገር ውስጥ ገበያው ጋር ሲወዳደር የ20 በመቶ እና 30 በመቶ ቅናሽ በማድረግ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሲሸጡ ነበር። ይህንን አይነት አካሄድም የነጻውን ገበያ አካሄድ በማይጎዳ መልኩ ቁጥጥር እየተደረገበት ይገኛል።
እንደ አቶ ኃይሌ ገለጻ፤ የምግብ ዘይት አምራቾች ግብዓት የማግኘት ችግር አለባቸው። ይህም የተፈጠረው ላኪዎች ከስረውም ቢሆን ለውጭ ገበያ የቅባት እህሎችን ስለሚያቀርቡ ጭምር ነው። በዚህም ምክንያት ሀገር ውስጥ የሚመረተው ዘይት ከውጭ ሀገራት የሚመጣው ዘይት ዋጋው ይጨምራል። በአሁኑ ወቅት ግን ይህ አካሄድ እንዲቆም እየተደረገ ሲሆን የነጻ ገበያውንም ስርዓት በማያፋልስ መልኩ የቅባት እህል ምርቶቹን ለሀገር ውስጥ ፈላጊዎች የሚያቀርቡበት ሁኔታ ላይ እየተሰራ ይገኛል።
የሀገር ውስጥ ዘይት አምራቾች መንግስት ያልተመጣጠነውን የግብይት ስርዓት በማስተካከል የሀገር ውስጥ ምርት አቅርቦቱን ለማሳደግ የጀመረው ጥረት ለዘርፉ እድገት ወሳኝነት እንዳለው የገለጹት አቶ ኃይሌ፤ ከዚህ በተጨማሪ ለዘጠነኛ ጊዜ የተዘጋጀው የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች ዓለም አቀፉ ጉባዔ ሰሞኑን ስለሚጀመር በፕሮግራሙ ላይ አምራች እና ተቀባይ ያለደላላና ሌሎች ጣልቃ ገብነት በቀጥታ መገበያየት የሚችልበት እድል እንደሚፈጥሩ ገልፀዋል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የውጭ ንግድ ማስፋፊያ ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ሙሉጌታ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰሊጥ ምርት ወደ ዘይት ቀይሮ መስራት የሚችል የቴክኖሎጂ፣ ዕውቀትና ገንዘብ አቅም አልተፈጠረም፤ ያሉትም አበጥረው በመላክ ላይ ብቻ ነው ያተኮሩት። በዚህም ምክንያት እንደ ጎመን ዘር እና የተለያዩ ምርቶችን ለዘይት ጥቅም ላይ ይውላሉ። በመሆኑም አቅሙ እስኪፈጠር ድረስ ሰሊጥን ወደውጭ ሀገራት የመላኩ ስራ ይቀጥላል። ይሁንና ሌሎቹን የቅባት እህሎች ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ ማዕከላት በማስገባት ለዘይት አምራቹ የሚደርስበትን መንገድ እየተፈለገ ነው።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ጋር በመተባበር በየዓመቱ የሚያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመም ጉባኤ ለዘጠነኛ ጊዜ በሸራተን አዲስ ሆቴል ከህዳር 19 እስከ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2012
ጌትነት ተስፋማርያም