አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች በባለሙያዎች ሥነ ልቦና ላይ ጫና ማሳደሩን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። በሩብ ዓመቱ የጤናውን ዘርፍ ሊያጎለብቱ የሚችሉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውንና ይህም በቀጣይ ለሚሠሩ ሥራዎች መሰረት እንደሚሆንም ተጠቁሟል።
በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሳ የሩብ ዓመት አፈፃፀምና አጠቃላይ የሚኒስቴሩን ሥራ አስመልክቶ ትናንት መግለጫ የሰጡ ሲሆን፤ ከጋዜጠኞች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ዳይሬክተሩ በመግለጫው ወቅት እንዳሉት፤ አልፎ አልፎ በተከሰቱ የፀጥታ ችግሮች የጤና ባለሙዎችን የማስፈራራትና በሥነ ልቦና ጫና ማሳደሩን ጠቁመዋል። ይህም በሥራው ላይ እክል መፍጠሩን ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ ባለሙያዎቹ ወደ ሥራ አካባቢ እንዳይቀርቡ በማድረግም ተፅዕኖ መፈጠሩን አብራርተዋል። ይሁንና በባለሙያዎችም ሆነ በጤና ተቋማት አሊያም ሆስፒታሎች ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን አረጋግጠዋል።
ዶክተር ተገኔ እንዳሉት፤ በሩብ ዓመቱ የእናቶችን ጤና ለማሻሻል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የታሰበው የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ባለፉት ሁለት ወራት 67 ከመቶ እንዲሁም የቅድመ ወሊድ ክትትልም 65 ከመቶ መድረሱን ጠቁመዋል። አንድ ዓመት ያልሞሉ ህፃናትም የፀረ አምስት ክትባት በሩብ ዓመቱ ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ ማግኘት ከሚገባቸው ህፃናት መካከል 93 ከመቶ ለሚሆኑት ተደራሽ ሆኗል።
ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለደረሱ 1ነጥብ1 ሚሊዮን ልጃገረዶች የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ለመስጠት ታቅዶ 90 ከመቶ ማሳካት ተችሏል። በሩብ ዓመቱን 443ሺ339 ነፍሰ ጡር እናቶች የኤች አይ ቪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን፤ ይህም ከእቅዱ 78 ከመቶ ይሸፍናል። ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ለተገኘ 3ሺ 545 ደግሞ የፀረ ኤች አይ ቪ ህክምና ተሰጥቷቸዋል።
የወባ ትንኝን ለመቆጣጠርና የወባ በሽታን ለመከላከል ሦስት ሚሊዮን 189ሺ617 አጎበር በግዢ ሂደት ላይ መሆኑን 3 ነጥብ5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመርጨት የሚያስችል የፀረ ወባ የኬሚካል ግዥ በሂደት ላይ መሆኑን ገልፀዋል። 8ሺ55 የርጭት መሳሪያዎች ደግሞ ለወረዳዎች ተሰራጭተዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ የትራኮማ የዓይን ቀዶ ሕክምናን በተመለከተ ደግሞ በአማራ፣ በደቡብ ብሄር በሄረሰቦችና ህዝቦች እና ኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ 6ሺ400 ሰዎች የዓይን ቆብ የማስተካከል ሕክምና አገልግሎት ተሰጥቷል። 14 ሆስፒታሎች የቀዶ ህክምና አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋትም በሩብ ዓመቱ ውስጥ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ተብራርቷል።
በሩብ ዓመቱ 77ሺ 625 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ 67ሺ79 ከረጢት ደም መሰባሰቡን የገለፁት ዶክተር ተገኔ፤ ይህም የእቅዱን 86 ከመቶ ሸፍኗል። በማዕከል ደረጃ ባለው ብሄራዊ የደም ባንክ አገልግሎት 25ሺ ዪኒት ደም ለማሰባሰብ ታቅዶ 32ሺ943 ዪኒት ደም ተሰብስቧል። በአንድ ቀን 10ሺ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ የነበረ ሲሆን ከእቅዱ በላይ 14ሺ ዩኒት ደም መሰብሰቡን አስረድተዋል። በተጨማሪም 47 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ስር የሚገኙ 10 ዋርዶችን ጉድለታቸውን በማስተካከል ለአገልገሎት ብቁ ማደረጉን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር