አዲስ አበባ፡- የኢህአዴግ ምክር ቤት በስራ አስፈጻሚው የተመራለትን ውህደት በሙሉ ድምጽ አጸደቀ።
የኢህአዴግ ምክር ቤት ትናንት ውይይት ሲያካ ሂድ የዋለ ሲሆን፤ የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ፈቃዱ ተሰማ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፤ ምክር ቤቱ በደንቡ መሰረት ምልአተ ጉባኤውን አሟልቶ በውህደቱ ላይ ከመከረ በኋላ ውህደቱን በሙሉ ድምጽ እጽድቆታል።
እንደ አቶ ፈቃዱ ገለፃ፤ በምክር ቤቱ ውይይት ላይ የኢህአዴግ ኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን የውህደቱ አስፈላጊነት፤ ህጋዊ አሰራርና ከደንብ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችንም በተመለከተ በዝርዝር ጥናት አቅርቧል። የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው ውህደቱ ኢህአዴግ አሁን ባለው ቁመና አገራዊ ለውጡን ለመምራትና መሰረት ለማስያዝ ብሎም የህዝቦችን ሁለንተናዊ ብልጽግና እንዲያረጋግጥ የሚያስችለው ስለሆነ አስፈላጊነቱን ገልፃዋል። ህገ ደንብና ሥርዓት ከመከተል አኳያ በደንቡና በህጉ መሰረት የተከናወነ ሆኖ በመገኘቱ ውህደቱ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።
የአዲሱ ውህድ የብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራምን ምክር ቤቱ ተመልክቷል። ፕሮግራሙ አራት ክፍሎች ያሉት ሲሆን በፖለቲካ ፕሮግራም ህብረ ብሄራዊ፤ ህገ መንግስታዊና ፌዴራላዊ ሥርዓት ለመገንባትና የብሄር ብዝሀነትና ሀገራዊ አንድነት አስታርቆ ለመቀጠል ብሎም የግለሰብና የቡድን መብትን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል መሆኑ ታይቷል።
በኢኮኖሚ ዘርፍ የህዝቡን ኑሮ ለመቀየር እንዴት መንቀሳቀስ እንደሚገባ እንዲሁም በማህበራዊና የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ላይም ውይይት ተካሂዷል፡፡ እስካሁን ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸውን ድሎች የሚያስቀጥል፤ የተሳሳቱትን የሚያርምና የቀጣዩ ትውልድ ብልጽግናን የሚያረጋግጥ እንዲሁም አሁን አገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበ ግራ ዘመምም ቀኝ ዘመም ያልሆነ የፖለቲካ ፕሮግራም መዘጋጀቱን አስመልክቶ ውይይት መካሄ ዱንም አቶ ፈቃዱ አስታውቀዋል።
አስራ አንደኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ውህደቱን ለማጽደቅ ለኢህአዴግ ምክር ቤት ሙሉ ውክልና ስልጣን መስጠቱን አስታውሰው፤ የአጋር ድርጅቶች አመራሮች እስከ ውህደቱ ድረስ በስራ አስፈጻሚና አመራር በኢህአዴግ ምክር ቤት እንዲሳተፉና ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ውህድ ፓርቲው እንዲቀላቀሉ አቅጣጫ መቀመጡን አውስተዋል። በዚህ መሰረት ባለፉት ወራት በአጋር ድርጅት ምክክር ተደርጎ ከስምምነት መደረሱና፤ ከህዳር ስድስት እስከ ስምንት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ባደረገው ስብሰባ የውህደቱ አስፈላጊነት ጥናትና ቅርጽ ለምክር ቤቱ መርቶ እንደነበር ይታወሳል።
ስብሰባው ነገ የሚቀጠል ሲሆን የብልጽግና ፓርቲ መተዳደተሪያ ደንብ ረቂቅ ላይ ውይይት ያካሂዳል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ