እንደ ኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር 1888 ዓ.ም ዓድዋ፣ የቅኝ ግዛት ፍላጎቱን ለማሳካት ኢትዮጵያን የወረራው ዒላማ አድርጎ ገስግሶ የመጣው የኢጣሊያ መንግሥት ሠራዊት በኢትዮጵያውያን ልዩና ታሪካዊ አንድነት በተሰጠ ምላሽ የሽንፈት ማቁን ተከናነበ። ጣልያኖች ዓድዋ ላይ ድል ከሆኑ በኋላ ለአጭር ጊዜ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ የሚከተሉትን የመስፋፋት ፖሊሲ እንደመግታት ብለው ነበር።
ከሽንፈቱ በኋላ አዲስ የተሾመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዲ ሩዲኒ ቀዳሚው ፍራንችስኮ ክሪስፒ ያራምድ የነበረውን ፖሊሲ ሽሮታል፤ ለቅኝ ግዛት ማስፋፊያ የተመደበውን በጀት በግማሽ ቀነሰው፤ ከዓድዋ ጦርነት በፊት አንገቱን ደፍቶ የነበረው የፀረ-ኮሎኒያሊስት ቡድን አሁን የልብ ልብ አግኝቶ ኢጣሊያ ከነአካቴው የአፍሪካን ምድር ለቃ እንድትወጣ ለመጠየቅ ተዳፈረ። ይህ ሁሉ ግን የቆየው ለአጭር ጊዜ ነበር።
ከእንግሊዝ ቀጥሎ ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም የጋራ ድንበር ያሏቸውን ቅኝ ግዛቶች የምታስተዳድረው ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ችላ ብላ መኖር አልቻለችም። ከዓድዋ ሽንፈት 30 ዓመታት በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው አምባገነኑ የፋሺዝም አቀንቃንኝ ቤኒቶ ሙሶሊኒ፣ ራሱን እንደ ሮም የቀድሞው ንጉሥ ጁሊየስ ቄሳር በመቁጠርና “የኢጣሊያን ክብር ለዓለም አሳያለሁ” በሚል የረጅም ጊዜ ተስፋ የቅኝ ግዛት ዘመቻውን ሊያሳካ ላይ ታች ማለቱን ተያያዘው።
ነገሩ ይህ ብቻ አልነበረም፤ ኢጣሊያውያን በውስጥ ችግሮቻቸው ላይ የነበራቸውን ትኩረት ለማስቀየር፣ እየጨመረ ለመጣው የኢጣሊያ ህዝብ የማስፈሪያ ቦታ ለመፈለግ እንዲሁም በአውሮፓ መድረክ የከሸፈበትን የመስፋፋት ፖሊሲ ለማካካስ ቅኝ ግዛትን አማራጭ አድርጎ ተነሳ። ከሁሉም በላይ ግን ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን ሽንፈት ለመበቀል ሙሶሊኒ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ አዞረ።
ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን ሽንፈት ለመበቀል ለአርባ ዓመታት ያህል ስትዘጋጅ ከኖረች በኋላ በየጊዜው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በባህል መስክ የተፈራረመቻቸውን የሰላምና የትብብር ውሎችና በመንግሥታቱ ማኅበር አባልነቷ የገባቻቸውን ዓለም አቀፍ ግዴታዎች ሁሉ በጠመንጃ አፈሙዝ በመቅደድ ‹‹ከእንግዲህ አላውቃችሁም›› አለች። ከብዙ ጊዜያት ዝግጅትና የጠብ አጫሪነት እንቅስቃሴዎች በኋላ፣ ፋሺስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ወረረች። በነማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ እየተመራች አሰቃቂ ወረራ በመፈፀም ኢትዮጵያን ቅኝ ተገዥዋ ለማድረግ ጥረት አደረገች።
ይሁን እንጂ መቼውንም ቢሆን በአገሩና በነፃነቱ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የፋሺስትን አገዛዝ ‹‹አሜን›› ብሎ አልተቀበለውም። ይልቁንም ጨርቄን ማቄን ሳይል ‹‹ጥራኝ ዱሩ›› ብሎ ለነፃነቱ መፋለም ጀመረ። ኢትዮጵያ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ጀግኖችን ያፈራች አገር ናትና የኢጣሊያ ወራሪ ኃይልም አንዲትም ቀን እንኳን እፎይ ብሎ ሳይቀመጥ ከአምስት ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ሌላ የሽንፈት ማቅ ለብሶ ከኢትዮጵያ ምድር ተባረረ። ታዲያ በዚህ አስገራሚና አኩሪ የመስዋዕትነት ጉዞ ውስጥ ደማቅ የጀግንነት ታሪክ ከፃፉና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ከተጋደሉ እልፍ የኢትዮጵያ ጀግኖች መካከል አንዱ ያልተዘመረላቸው ደጃዝማች በቀለ ወያ ናቸው።
በቀለ ወያ ነሐሴ 21 ቀን 1902 ዓ.ም ተወለደ። ሕፃኑ በቀለ አማረኛ መማር እንዳለበት ያመኑት ቤተሰቦቹ፣ መምህር ተቀጥሮለት ቤቱ ውስጥ አማረኛን ተምሮ አጠናቀቀ። እድሜው 16 ሲሆንም ወደ አጎቱ ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ ዘንድ ሄዶ እንዲኖር ስለተወሰነ ወደ አጎቱ ዘንድ ሄደ። በሥነ-ሥርዓት አክባሪነቱ፣ በቅንነቱ፣ በጨዋነቱ፣ በእርጋታውና በአስተዋይነቱ የአጎቱን የደጃዝማች ገብረማርያምን ቀልብ ለመሳብ ጊዜ አልፈጀበትም። እድሜው ከፍ ሲልም የአጎቱ እልፍኝ አስከልካይ ሆነ።
ደጃዝማች ገብረማርያም የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ በነበሩበት ወቅት በቀለ ‹‹ሻቃ›› የሚል የማዕረግ ስም ተሰጥቶት በረዳት ወታደርነትና በአስተዳደር ሥራ አገልግሏል። በኋላም ደጃዝማች ገብረማርያም የአገር ግዛት ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ በቀለ አብሯቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የታንክ መስበሪያ መሣሪያ አጠቃቀምን ተማረ። የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን መውረር ሲጀምር ወጣቱ በቀለ አገሩን ከወራሪ ኃይል በመከላከል ሉዓላዊነቷን የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ለእናት አገሩ ክብር ለመፋለም ታጠቀ።
ወረራው እንደተጀመረ ሻቃ በቀለ ወደ ሰሜን ግንባር ዘመተ። በመቀጠልም በንጉሠ ነገሥቱ ትዕዛዝ ወደ ደቡብ ግንባር በመሄድ ከአጎቱ ከደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ ጋር በጠላት ላይ አንጸባራቂ ድሎችን መቀዳጀት ቻለ። በወቅቱ ደጃዝማች ገብረማርያም ጦራቸውን አሰልፈው ወደ ሰሜን አቅጣጫ በመጓዝ ቆቦ ደርሰው ቦታውን ከተቆጣጠረው ግንባር ቀደም የጠላት ኃይል ጋር ውጊያ ገጥመው የጠላት ጦር ለቀጣዩ ውጊያ እንዲረዳው በማሰብ የዘጋውን በር ማስከፈት የቻሉ ቢሆንም በደቡብ በኩል የነበረው የጠላት ወረራ የበረታ ስለነበር ደጃዝማች ገብረማርያም ከሰሜን ወደ ደቡብ ሄደው ከራስ ደስታ ዳምጠው ጋር ሆነው ጠላትን እንዲመክቱ በንጉሠ ነገሥቱ በመታዘዛቸው ወደ ደቡብ ግንባር ሄደው ነበር።
በግንቦት 1928 ዓ.ም ደጃዝማች ገብረማርያም ድኑን በተባለ አካባቢ በጠላት ጦር ላይ የሁለት አቅጣጫ ጥቃታቸውን አፋፍመው ድል ሲቀዳጁ አብረዋቸው ከተሰለፉት የጦር አዝማቾች መካከል አንዱ ሻቃ በቀለ ነበር። በዚህ ጦርነት ላይ የደጃዝማች ገብረማርያም ታላቅ ወንድም ደጃዝማች ኡርጋ ጋሪ እና ፊታውራሪ ተሰማ አብዲ አብረው ነበሩ። በዚህ ጦርነት ድል የጨበጠው የደጃዝማች ገብረማርያም ጦር የፋሺስት የጦር መኮንኖችንና ወታደሮችን ከመደምሰሱም በተጨማሪ መትረየሶችን መማረክ ችሏል።
አርበኛና የታሪክ ጸሐፊ ቀናዝማች ታደሰ ዘወልዴ ‹‹ቀሪን ገረመው›› በሚለው የአርበኞች ታሪክ መጽሐፋቸው ላይ በቀለ ወያ በወቅቱ ስላከናወነው አኩሪ የጀግንነት ታሪክ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል …
‹‹ … የጠላት ታንክ የወገንን ጦር በማጥቃቱ ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ በጣም ያዝኑ ነበር። አንድ ቀን አምስት ታንኮች በመደዳ ሆነው ጦሩን እያጠቁ ሲመጡ ‹በቀለ ያንተ ብልሃት ለመቼ ሊሆነን ነው?› እያሉ ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ ሲያዝኑ በቀለ ዝም ብሎ ይመለክት ነበር። ታንኮቹ ጠጋ ብለው በደንብ ሲታዩት በመድፍ የመጀመሪያውን አኮማተረው፤ ደግሞ የኋለኛውን ደገመው። እንደዚሁ አድርጎ በአምስት ደቂቃ ውስጥ አምስቱንም ታንኮች አቃጥሎ ሲነዱ ‹ደጃዝማች ሄደው እሳት ይሙቁ› አሏቸው … ›› በማለት የወቅቱን የጀግንነት ሥራውን በከፍተኛ አድናቆት ጽፈዋል።
በመቀጠልም ከሰኔ 1928 ዓ.ም. እስከ የካቲት 1929 ዓ.ም ድረስ በብዙ የጦርነት ዘመቻዎች ላይ ተሳትፎ ድሎችን አስመዝግቧል። ለአብነት ያህል በአለታ ወንዶ አካባቢ ተፈሪ ኬላ በተባለው ቦታ፣ በአርቤጎና፣ በዳኤላ ጭሪ፣ አርሲ ውስጥ ሂበኖ በተባለው ቦታ፣ በሶዶ እና በዝቋላ አካባቢዎች በተካሄዱ ውጊያዎች ከጠላት ጦር ጋር እልህ አስጨራሽ ፍልሚያዎችን አድርጓል። በተለይም ደባ ስሬ በተባለው አካባቢ በተካሄደው ጦርነት አጎቱ ደጃዝማች ገብረማርያም ቢቆስሉም ሻቃ በቀለ በርካታ የጠላት ታንኮችን በመድፉ በማውደም የማይረሳ የጀግንነት ታሪክ ሠርቷል።
ኅዳር 8 ቀን 1929 ዓ.ም ደጃዝማች ገብረማርያም በመትረየሳቸውና ‹‹ገላግሌ›› በሚባለው ባለጋሻ መድፍ እየታገዙ በጠላት ላይ ጥቃት ከፈቱ። በዚህ ጥቃት ከመቶ የሚበልጡ የጣሊያን ወታደሮች ሲደመሰሱ ጫካውን ተገን አድርጎ ካመለጠው የአገር ተወላጅ ባንዳ በስተቀር አብዛኛው ባንዳ እዚያው ጫካ ውስጥ ቀርቷል። በኋላ እንደተረጋገጠው ደግሞ አንድ የጣሊያን የጦር ጀኔራልም በውጊያው ሞቷል። ከዚህ ውጊያ በኋላ የጣሊያን ጦር የማጥቃት ዘመቻ ቢያደርግም ምንም ውጤት ስላላመጣለት በቦታው የነበረው ጦር አዛዥ ጀኔራል ጀሎዞ ለማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ ‹‹የተፈሪ ኬላን በር ጥሼ ወደመሐል አገር ወደ ይርጋለም ማለፍ አልቻልኩም፤ ስለዚህ ወታደሮቼን ይዤ ወደኋላ ማፈግፈግ ግድ ሆኖብኛል›› በማለት መልዕክት ልኮለት ነበር።
በደጃዝማች ገብረማርያም የማጥቃት እርምጃ የተጎዳው የጣሊያን ጦር እንደገና ተጠናክሮ ማጥቃት ጀመረ። ደጃዝማች ገብረማርያምም በወንድማቸው ቀኛዝማች ኡርጋ ጋሪና በሻቃ በቀለ ወያ ታግዘው የሲዳሞን ጦር ይዘው የጠላትን እግረኛ ጦር ለአራት ተከታታይ ቀናት መመከት ችለዋል።
በሰሜንና በምስራቅ በኩል የማጥቃት ዘመቻ የከፈተው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ዋና ከተማው አዲስ አበባ ድረስ ዘልቆ መግባት ቢችልም በደቡብ በኩል የነበረው ጦር ግን ከነራስ ደስታ ዳምጠው እና ከነደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ በኩል በገጠመው የመከላከልና የማጥቃት ዘመቻ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ መድረስ ስላልቻለ የግንባሩ ጦር አዛዥ ጀኔራል ጀሎዞ እና ዋናው የአስተዳደሩ ተወካይ ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ ለራስ ደስታና ለደጃዝማች ገብረማርያም ልመና፣ ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ የተቀላቀሉባቸው ደብዳቤዎችን ጽፈውላቸው ነበር።
ጥር አንድ ቀን 1929 ዓ.ም ሻንቆ በተባለው ቦታ ላይ በተደረገው ውጊያ ኢትዮጵያውያን በጠላት እግረኛ ጦር ላይ ከፍተኛ ድል ቢቀዳጁም የጠላት ጦር በአውሮፕላን የሚያዘንበውን ቦምብና መርዝ ግን መቋቋም አልተቻለም። በመሆኑም አርቤጎናን በመልቀቅ ብዙ የወገን ጦር ወዳለበት ወደ ባሌ ግዛት ለመሄድ ተወሰነ። ውጊያው በመንገድ ላይም አላባራም ነበር። የወገን ጦር መንገድ የዘጋበትን የፋሺስት ጦር በመውጋት መንገድ እያስከፈተ ዘለቀ።
ጥር 20 ቀን 1929 ዓ.ም ራስ ደስታ ዳምጠው፣ ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ፣ ደጃዝማች በየነ መርዕድ፣ ደጃዝማች በዛብህ ስለሺ እና ፊታውራሪ ሽመልስ ሀብቴ ጦራቸውን ይዘው እነርሱም መድፍ ጠምደው በተሰለፉበት ውጊያ ላይ ሻቃ በቀለ፣ ከአጎታቸው ከደጃዝማች ገብረማርያም ጋር ሆነው ታላቅ የጀግንነት ሥራ ሠርተዋል። የሚያስገርመው ነገር በዚህ ጦርነት ላይ ደጃዝማች ገብረማርያም በወቅቱ አመርቅዞ እየጠዘጠዘ ያሰቃያቸው የነበረውን ቁስላቸውን ከምንም ሳይቆጥሩ የታጠቁትን ሱሪ ወደላይ በመሰብሰብ ያለጫማ እየተራመዱ በያዙት ግንባር በኩል በግራና በቀኝ እየተሸከረከሩ ዝናር ሙሉ ያጎረሱትን መትረየስ በጠላት በኩል በማስገባት በር ማስከፈታቸውና በጠላት ጦር ላይ ትልቅ ጉዳት ማድረሳቸው ነው። በዚህ ተጋድሎ እነሻቃ በቀለና ተዋጊዎቻቸው አካባቢው በጠላት እጅ እንዳይወድቅ ከማድረጋቸውም ባሻገር በጠላት ጦር ላይ ከበድ ያለ ጉዳት ማድረስ ችለዋል።
የካቲት 10 ቀን 1929 ዓ.ም ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ ወደ ቡታጅራ በሚወስደው መንገድ ላይ በሚገኘው የፋሺስት ጦር ላይ ጥቃት ተከፈተ። ጠላት ያላሰበው ጥቃት ስለነበረም ክፉኛ ተጎዳ። ለበቀል እርምጃ የተነሳው የጠላት ጦር እርምጃ መውሰድ ሲጀምር እልህ አስጨራሽ ውጊያ ተካሄደ። ራስ ደስታ ዳምጠው ጥቂት ወታደሮችን ይዘው ወደ መስቃን ሄዱ። ቀኛዝማች ኡርጋ ጋሪ፣ ቀኛዝማች በየነ ጉደታ እና ሻቃ በቀለ ወያ ያሉበት ቀሪው ጦር ደጃዝማች ገብረማርያምን አጅቦ ወደ ማረቆ ወደሚገኘው ጎጌቲ ገብርኤል ሲያመራ የጠላት ጦር ክትትሉን ስላላቋረጠ ጎጌቲ ገብርኤልን ከብቦ ያዘ።
ደጃዝማች ገብረማርያምም እየመከቱ ሚልኮ ማርያም ደረሱ። ይህ ውጊያ የመጨረሻው እንደሚሆን ቀድመው ያወቁት የዓድዋው ጀግና ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ አብረዋቸው የነበሩት አርበኞች ለኢትዮጵያ ነፃነት እንዲፋለሙ ተናገሩ። ሻቃ በቀለ ወያንና ቀኛዝማች በየነ ጉደታን አቅርበው በምንም ዓይነት ሁኔታ እጃቸውን እንዳይሰጡ መክረውና መርቀው ካሰናበቱ በኋላ የጠላትን ወታደር ሲያጋድሙ ውለው የካቲት 13 ቀን 1929 ዓ.ም ከጠላት ጦር በተተኮሰ ጥይት ተመትተው ወደቁ።
ሻቃ በቀለ የደጃዝማች ገብረማርያም ሞት ክፉኛ ቢያስደነግጣቸውና ቢያሳዝናቸውም ጦሩን የመምራት ኃላፊነታቸውን ተቀብለው ፍልሚያውን ቀጠሉ። በየካቲት ወር 1930 ዓ.ም በሶዶና በሜጫ ወሰን ላይ ሁለት ባታልዮን የጠላት ጦር ገጥመው ድል በማድረግ ጀግንነታቸውንና ጥንካሬያቸውን አስመስክረዋል። በዚሁ ወር ተከታታይ ጦርነቶችን ያካሄዱ ሲሆን፤ በተለይም አገምጃ ላይ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በአውሮፕላንና በመድፍ ከታገዘው የወራሪው ጦር ጋር ያደረጉት ፍልሚያ የሚዘነጋ አይደለም። በዚህ ውጊያ ላይ ብዙ አርበኞች ቢረግፉባቸውም የማታ ማታ ድሉ የእርሳቸው ሆኗል። የጀግናውም ሻቃ በቀለ የጀብዱ ሥራ ከቀን ወደ ቀን እያደገና እየጎላ በመምጣቱ የአገር ነፃነት የጠማው ጀግና ሁሉ ከጦራቸው ጋር ተሰልፎ መስዋዕትነት ለመክፈል ወደእርሳቸው መጉረፍ ጀመረ።
በግንቦት ወር 1932 ዓ.ም የፋሺስት ጦር 24ኛ ብርጌድ አዛዥና የሶዶና ወሊሶ አካባቢ ገዥ ሆኖ የተሾመው ኮሎኔል ካዛባሳ ጦሩን ይዞ ከአዲስ አበባ ወደ ጎጌቲ ሲያልፍ የሻቃ በቀለ ወያ ጦር መንገድ ላይ ጠብቆ በመውጋት ለወሬ ነጋሪ እንኳ ሳያስተርፍ ደመሰሳቸው።
ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ ስለክስተቱ ሲገልፁ ‹‹ … በ18 ካሚዮን የነበሩትን ፋሽስቶች አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጨረሷቸው። ወዲያውኑ አስከሬናቸው በፍጥነት ወደነበሩበት ካሚዮን እንዲሰበሰብ ከተደረገ በኋላ ናፍጣ አርከፍክፈውና በዕሳት አቀጣጥለው ሌሊቱን እንደጧፍ ሲነድ አደረ … ›› በማለት ጽፈዋል።
የሻቃ በቀለ ጦር የጠላትን ጦር ድል እየመታ ስለቀጠለ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ሻቃ በቀለ በነበሩበት አካባቢ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለወራት ያህል ለማቋረጥ ተገዶ ነበር። ከደጃዝማች ገብረማርያም ሞት በኋላ ሻቃ በቀለ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን አርበኞች ጋር ኅብረት ፈጥረው ጠላትን በጋራ ተፋልመዋል። ለአብነት ያህል ከራስ አበበ አረጋይ እና ከደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ጋር የፈጠሩት ወዳጅነትና ኅብረት ተጠቃሽ ነበር። የፋሺስት ጦርም ሻቃ በቀለና ጦራቸው ከፍተኛ መስዋዕትነት እንዲከፍሉ ያደረጋቸውን የበቀል እርምጃ ወስዶባቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ የበቀል እርምጃ ሻቃ በቀለን ከነፃነት ተጋድሏቸው ሊያሰናክላቸው አልቻለም።
በመጨረሻም ወራሪው የፋሺስት ጦር በሻቃ በቀለና በሌሎች ኢትዮጵያውያን አርበኞች እልህ አስጨራሽ ትግል ከኢትዮጵያ ምድር ተባረረ። ንጉሠ ነገሥቱ ከስደት ከተመለሱ በኋላ ሻቃ በቀለ የደጃዝማችነት ማዕረግ ተሰጣቸው። ከ1933 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች አገረ ገዥ በመሆን ተሹመው አገልግለዋል። የክብረ መንግሥት የወርቅ ማዕድን ኃላፊና የሁለተኛ ሬዥማን አዛዥ ሆነውም አገልግለዋል። ፋንታሁን እንግዳ ‹‹ታሪካዊ መዝገበ ሰብ›› በተባለው መጽሐፋቸው በ1936 ዓ.ም. ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ከጎጃም ተይዘው መጥተው እስር በተፈረደባቸው ጊዜ ወደ አዲስ አበባ እስኪዛወሩ ድረስ ለተወሰኑ ወራት የቆዩት በደጃዝማች በቀለ እጅ እንደነበር ጠቅሰዋል።
ለሀገራቸው ነፃነት በዋጋ የማይተመን አስተዋጽኦ ያበረከቱትና በሥራ ገበታቸው ላይ ሆነው በቅንነት ሲያገለግሉ የነበሩት ደጃዝማች በቀለ ወያ፣ ባጋጣማቸው ሕመም ምክንያት በሀገር ውስጥ ሲታከሙ ቢቆዩም ስላልተሻላቸው ወደ ስዊዘርላንድ ሄደው ሊታከሙ በጉዞ ላይ ሳሉ ሚያዝያ 6 ቀን 1946 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። አስከሬናቸውም ሚያዝያ 10 ቀን 1946 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ሥርዓተ ቀብራቸው የመንግሥት ሹማምትንና የአርበኞች ማኅበር አባላትን ጨምሮ በርካታ ሕዝብ በተገኘበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።
በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ሕዝቡ የሻቃ በቀለ ወያን ጀግንነት ለመግለጽ እንዲህ በማለት ገጥሞ ነበር።
አላስኬድም አለኝ ጣልያን በመንገዱ፣
ያ ሻቃ በቀለ ና ወንዱ ና ወንዱ!
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/2012
አንተነህ ቸሬ