‹‹ውቢቷ›› የሚለው ቃል ከስሟ ቀድሞ የሚገባ ቅጽል ነው። በንግግርም ይሁን በጽሑፍ ስሟ ሲጠራ ‹‹ውቢቷ›› የሚለውን በማስቀደም ነው። የባህርዳር ከተማ። ‹‹ውቢቷ ባህር ዳር›› የተባለችውም በጣና ገነት በዓባይ መቀነት የተከበበች ስለሆነች ነው። ባህር ዳር ተፈጥሮ ያደላት ሌላም ውበት አላት። በየመስመሩ ግራና ቀኝ ያሉ ዘንባባዎቿ የባህር ዳር ከተማ መለያዎች ናቸው። ‹‹የዘንባባ ምድር›› የሚል ሌላ ቅጽል ስም እንዲፈጠርላት አድርገዋታል። ‹‹ውቢቷ ባህር ዳር›› የተባለችውም እነዚህን የተፈጥሮ ፀጋዎች ስለያዘች ነው።
የባህር ዳር ከተማን ድንቅ ውበት የሚፈታተን ሰው ሰራሽ ችግር ግን እየተፈጠረ ነው። በከተማዋ ውስጥ አፍንጫ ተይዞ የሚታለፍባቸው አካባቢዎች እየበዙ ነው። ምንም እንኳን ይሄ የብዙ የኢትዮጵያ ከተሞች መለያ ቢሆንም፤ እንደ ባህር ዳር ካሉ በውበት ስመጥር ከሆኑ ከተሞች ግን አይጠበቅም ነበር። የከተማዋ የውበት ግርማ ሞገስ የሆነው የጣና ዳር እንኳን ሳይቀር ለአፍንጫ የሚከብዱ ሽታዎች እየተከሰቱ ነው። ከማንጎ መናፈሻ ተነስተው ጣናን ለመዞር በምዕራብ አቅጣጫ ሲዞሩ መጥፎ ሽታ ያጋጥማል። ይሄ የሐይቁ ወይም የደንገሉ ወይም የቄጤማው ሳይሆን የሰዎች ጽዳጅ ነው። በሰዎች የተጣሉ የቆሻሻ ዕቃዎችና ጥቅም ላይ የዋሉ ውዳቂ ነገሮች ናቸው።
በከተማዋ አንዳንድ ቦታዎች ላይም ለዓይን ማራኪ ሆነው አጠገባቸው ሲቀመጡ ግን መጥፎ ሽታ ያላቸው ቦታዎች አሉ። እነዚህን ቦታዎች ከርቀት ያየ ሰው ንጹህ አየር ለመቀበልና መንፈስን ለማደስ ሰፍ ብሎ አጠገባቸው ይሄዳል፤ ከቦታው ሲደርስ ግን የሚረብሽ ሽታ ያጋጥመዋል። ወጣት ቁምላቸው አማረ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ነው። እንደ ቁምላቸው አስተያየት፤ ለደረቅም ሆነ ፍሳሽ ቆሻሻዎች ምክንያቱ የአወጋገድ ሥርዓቱ ነው። በተለይም የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች ይዘጋጋሉ፤ ፈጣን ቁጥጥር ካልተደረገባቸው መጥፎ ሽታ ይፈጥራሉ። ችግሩ የመንግሥት አካላት ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡም ነው። ህብረተሰቡ ከተማዋን እንደ ስሟ ውብ ለማድረግ ከመጣር ይልቅ በግዴለሽነት በየቦታው ቆሻሻ ይደፋል።
‹‹የከተማዋን ውበት ለመጠበቅ ህብረተሰቡ የባለቤትነት ኃላፊነት ሊሰማው ይገባል›› የሚለው ቁምላቸው፤ በተለይም ወጣቶች ፕሮግራም አውጥተው ሊያጸዱ እንደሚገባ ያሳስባል። በመንግስት አካላት ታዝዞ ከሚሰራ ሥራ ይልቅ ወጣቶች በባለቤትነት በራሳቸው ተነሳሽነት ቢሳተፉ ከተማዋን የውበት ምሳሌ ማድረግ እንደሚቻል ነው የተናገረው።
ሌላኛው ወጣት ኢዮብ ውበት እንደሚለው፤ በከተማዋ የተፈጠረው የጽዳትና ውበት መጓደል ሰው ሰራሽ ናቸው ፤እነዚህን ችግሮች መቅረፍ የሚቻለውም በሰዎች ጥንቃቄ ነው። ለዚህም የከተማ አስተዳደሩና ወጣቶች በጋራ ሊሰሩ ይገባል። የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ወጣቶች ደግሞ በራሳቸው ተነሳሽነት በመሳተፍ የከተማቸውን ውበት ማስጠበቅ ይገባቸዋል። ለዚህ መልካም ተግባር ደግሞ ራሱም ዝግጁ እንደሆነ ነው ኢዮብ የተናገረው።
‹‹ቆሻሻ ሆኖ መታየቱ ለቆሻሻ መጣያነት እንዲውል ያደርገዋል›› የሚለው ወጣት ባዘዘው አገኘሁ ነው። እንደ ባዘዘው አስተያየት፤ ሰዎች የሚጸዳዱት ቆሽሾ ያዩበት ቦታ ላይ ነው፤ ንጹህ ከሆነ ማንም እዚያ ቦታ ላይ ደፍሮ ቆሻሻ አይጥልም። ሰዎች ሽንት የሚሸኑት አጥሩ ወይም የአስፋልቱ ዳር መጥፎ ሽታ ካለው ነው። ቀላሉን ሶፍትና ወረቀት እንኳን የሚጥሉት የቆሸሸ ቦታ ላይ ነው። ሁሉም አካባቢ ንጹህ ቢሆን ለማቆሸሽም የሚጀምር አይኖርም። አንድ ጊዜ የተበላሸ አካባቢ ካለ በዚያው ይቀጥላል።
ይህንን ለማስቀረት አንድ ጊዜ ሙሉ የጽዳት ዘመቻ እንደሚያስፈልግና ከዚያ በኋላ ተከታታይ ጽዳት መደረግ እንዳለበት ያሳስባል ወጣት ባዘዘው። ብዙ ጊዜ ትኩረት የሚደረገው በዋና ዋና የአስፋልት መንገዶችና ሆቴሎች ዙሪያ ብቻ ነው። ከዋና መስመሮች ገባ ሲባል መጥፎ ሽታ ያጋጥማል። ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያሳስባል። በየቦታው የቆሻሻ መጣያዎች መዘጋጀት አለባቸው። ‹‹ውቢቷ ባህርዳር›› የሚለውን ስም ለማስጠበቅ ለህብረተሰቡም የግንዛቤ ማስጨበጫ መሰጠት እንዳለበት ነው ባዘዘው የተናገረው።
የባህርዳር ከተማ የአካባቢ ጥበቃ፣ ጽዳትና ውበት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘላለም ጌታሁን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ የሚሰሩ አምስት ማህበራትና አንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አሉ። እነዚህ ማህበራት በጽሕፈት ቤቱ መኪና እየቀረበላቸው ይሰራሉ። ከእያንዳንዱ ግለሰብ በር ላይም እየሄዱ ያነሳሉ።
የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችም እንደሚሰሩ ነው አቶ ዘላለም የተናገሩት። የከተማዋ ጽዳትና ውበት መጓደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም አሁንም ክፍተት አለ። በክፍለ ከተማ ደረጃ ባለሙያዎች ተዘጋጅተው የግንዛቤ ማስጨበጫ ለመስጠት በዝግጅት ላይ ናቸው። ቆሻሻ እንዳይጣል በከተማዋ ዳርና ዳር ጥበቃ እየተደረገ ነው። ቆሻሻ እንዳይጣል ብቻ ሳይሆን ዛፍ እና አትክልት በመትከል ውብና ማራኪ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው። ችግሩም በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚቀረፍ እምነት አለኝ ሲሉ ሃሳባቸውን ደምድመዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ህዳር 6/2012
ዋለልኝ አየለ