አዲስ አበባ፡- በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የተማሪ መታወቂያ በመያዝ ተማሪዎችን ማዕከል አድርገው ሰላማዊውን የመማር ማስተማር ሂደት ለማስተጓጎል የሚንቀሳቀሱ አካላት ችግር እየፈጠሩ መሆናቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስትር ዴዔታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ሰሞኑን በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በሌሎችም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እየተፈጠረ ያለውን አለመረጋጋት አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የተማሪ መታወቂያ በመያዝ፣ ህገወጥ መታወቂያ በሚሰጡ ኃይሎች፣በገንዘብ በመደገፍ ተማሪዎች ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ፣ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትም አንዲስተጓጎል በማድረግ ሁከትና ግርግር የሚፈጥሩ አካላት አሉ፡፡
እነዚህ አካላት በተደላደለ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ጭምብል አድርገው ድንጋይ በመወርወር ፣ተማሪዎች ሜዳ ላይ እንዲያድሩ፣በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ እንዲጠለሉ፣ ከትምህርት ቤታቸው ለቀው እንዲወጡ፣ ተቋማቱ የብጥብጥና የሁከት ቦታ እንዲሆኑ፣ተማሪው እንዳይረጋጋ ማድረጋቸውን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴዔታው፣ ‹‹በየአካባቢያችሁ መማር ትችላላችሁ›› የሚል ቅስቀሳም በማድረግ ወላጆችንም እያሸበሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ ተማሪዎችን ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱ አካላት ይህን በማድረጋቸው የሚያገኙት ትርፍ እንደሌለ ተገንዝበው እጃቸውን ከተማሪዎች ላይ እንዲያነሱ አሳስበዋል፡፡
ተማሪዎች ያሉባቸውን ችግሮች በትምህርት ቤቶቻቸው ውስጥ ሆነው በመጠየቅ መፍትሄ የሚያገኙ መሆኑን እንዲገነዘቡና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴዔታው፣ በችግር ፈጣሪዎች ላይ የህግ አካላት ከሚወስዱት እርምጃ በተጨማሪ የትምህርት ተቋማትም እጃቸውን ያስገቡ ተማሪዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው አስታውቀዋል፡፡ የመማር ማስተማሩ ሂደት በተስተጓጎለባቸው አካባቢዎች ከተማሪዎች፣ ከትምህርት ማህበረሰቡ፣ ከአካባቢው መስተዳድር እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ትምህርት የተቋረጠባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ወልዲያ፣መቱ፣ጅማ፣ኦዳቡልቲ፣መደወላቡ መሆናቸው በመግለጫው የተመለከተ ሲሆን፤ በሃይማኖት ተቋማት ተጠልለው የሚገኙ ተማሪዎችም በሃይማኖት አባቶች የማረጋጋት ሥራ በመሰራቱ ወደ ትምህርት ተቋማቱ እንደሚመለሱ ተጠቁሟል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅም4/2012
ለምለም መንግስቱ